በመጪዎቹ ዓመታት በኢትዮጵያ ተፈላጊ የሚሆኑ የሥራ ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?

የተለያዩ አገራት ባለሙያዎች እየሄዱበት ያለውን የእድገት ጎዳና እንዲሁም በቅርብ ዓመታት ሊደርሱበት የሚችሉትን የእድገት ደረጃ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተስፋ የተጣለባቸውን ሥራዎችና የሥራ ፈጠራ ዘርፎች መዘርዘር የተለመደ ነው።

ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ወጣት ዜጎቿ የሥራ እድልን ለመፍጠርና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ለመመደብ ያስችለኛል የምትላቸውን ወሳኝ ዘርፎች ቢያንስ በየአምስት ዓመቱ ትለያለች።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚቀጥሉት ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት የሚያገኙትና በርካታ ወጣቶች የሥራ ባለቤት ሊያደርጉ የሚችሉት ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?

አቶ አዲስ አለማየሁ የአፍሮ ኤፍ ኤም፣ የቃና ቴሌቪዥን፣ የ251 ኮሚንኬሽን እና የበርካታ ስኬታማ ድርጅቶች መስራች እና ባለድርሻ ነው።

በተጨማሪም አዲስ ቁጥራቸው በበረከተ የተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ በመሰማርተ ዘርፈ ብዙ ዕውቀትና ልምድን አዳብሯል። በተለይ በሥራ ፈጠራ በኩል እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉና በርካቶችን ሊያሳትፉ የሚችሉ የሥራ ዕድሎችን በቅርበት ይከታተላል።

"በእኔ ዕይታ መንግሥት ትኩረት ያደረገባቸው ዘርፎች አሉ። በተለይ ደግሞ አሁን መንግሥት የተወሰኑ ዘርፎችን እንደ አዲስ ማነቃቃት አለብኝ ብሎ እየተንቀሳቀሰ ነው" ይላል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሥራ የሚፈልጉ ወጣቶች ባሉባት ኢትዮጵያ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ያለና በርካቶችን ሊያሳትፉ ከሚችሉ የሥራ ዘርፎች መካከል የተወሰኑትን አዲስ አለማየሁ ለቢቢሲ እንደሚከተለው ዘርዝሯል።

የቱሪዝም ዘርፍ

"መንግሥት አዲስ አይነት ፖሊሲዎችና አዲስ አይነት ማበረታቻዎችን በመጠቀም የቱሪዝም ዘርፉ እንዲነቃቃ እየሰራ ነው። በዚህ ዘርፍ በጣም በርካታ እድሎችና አማራጮች አሉ ብዬ አምናለሁ።"

አቶ አዲስ እንደሚለው አሁን አገሪቱ ያለችበት ነገር በጊዜ ተቀርፎ ነገሮች የሚረጋጉ ከሆነ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይህ ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። በዚህ ዙሪያም ኢትዮጵያ ከብዙ አገራት የተሻለ አቅም እንዳላት ያስባል።

"መርሳት የሌለብን ነገር ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ነው። አየር መንገዱ ከ100 በላይ በሚሆኑ አገራት በራረዎችን ያደርጋል። ከእነዚህ ሁሉ አገራት ጎብኚዎችን ይዘን መምጣት እንችላለን" ይላል።

"በሌላ በኩል እስከ 11 ሚሊየን የሚደርስ ተጓዥ በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በኩል ያልፋል። እነዚህን ተጓዦች እንደምንም ብለን አሳምነን አንድ ወይም ሁለት ተጨማሪ ቀን እንዲያድሩ ማድረግ ብንችል ኢትዯጵያ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው የሥራ እድል ከፍተኛ ነው።"

"ከአስተናጋጅ ጀምሮ፣ አስጊብኚዎች፣ ሹፌሮች እንዲሁም ባህላዊና የስጦታ እቃዎችን የሚሸጡ ሰዎች ምን ያክል የሥራ እድል ሊከፈትላቸው እንደሚችል ማሰብ ቀላል ነው።"

"አንድ ቱሪስት ደግሞ ሆቴል ውስጥ ብቻ እንዲቀመጥ አይታሰብም። ይዞራል፣ ያያል፣ ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይዝናናል፣ ይገዛል። በዚህ መሀል ብዙ የሥራ እድሎች ይፈጠራሉ ብዬ አምናለው።"

የግብርና ዘርፍ

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው ግብርና 27.5 ቢሊዮን ዶላር ወይም 34.1 በመቶ የጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ ይዟል።

በተጨማሪም 79 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች መተዳደሪያ ከመሆኑም በላይ በተመሳሳይ 79 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ንግድ ገቢ የሚሸፍነውም ይሄው ዘርፍ ነው።

ምንም እንኳን መንግሥት በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ ቢሆንም አሁንም ግብርናው ከኋላ ቀር አስተራረስና ከዝናብ ጥገኝነት አልተላቀቀም። ስለዚህም ግብርናን ከማዘመንና የተሻሻሉ ምርቶችንና እንስሳትን ማቅረብ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ወጣቶች ይህ ዘርፍ ትልቅ አቅም አለው።

አቶ አዲስ አንደሚለው የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ግብርና ላይ የተመሰረት መሆኑን መዘንጋት የለበትም። "ስለዚህ ይህ ዘርፍ በርካታ የሥራ እድሎችን እና የሥራ ፈጣሪዎችን እንደሚያስተናግድ እምነቱ አለኝ።"

"ከግብርናው ጋር ተያይዞ ያለው የገበያ ሰንሰለት በጣም የተበጣጠሰና አምራቾቹን የማይጠቅም አይነት መሆኑ ዘርፉ ብዙ የሚቀሩት ነገሮች ሰለመኖራቸው ትልቅ ማሳያ ነው። በዚህ በኩል ደግሞ ይህንን ችግር በመቅረፍ ትልቅ የሥራ እድል መፍጠር ይቻላል።"

የዲጂታልና የአይሲቲ ዘርፍ

በርካታ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከፍተኛ ትኩረት እያገኘና በቅርብ ዓመታት በርካታ የሥራ እድሎችን ሊከፍት የሚችለውና ሥራ ፈጣሪዎችን ሊያፈራ የሚችልው ዲጂታል እና የአይሲቲው ዘርፍ ነው።

"እንደ ትልቅ ማሳያ እንኳን በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ጥምረት መሰረተ ልማቶቹን መዘርጋት ሲጀምር የኢንተርኔት ፍጥነት ይጨምራል፤ ዋጋው ደግሞ ይቀንሳል። ይህን ተከትሎ ደግሞ በጣም ብዙ የአገልግሎት አይነቶች ወደ ዲጂታል ይዞራሉ ማለት ነው።"

"በዚህ ምክንያት በርካታ ወጣቶች በዚህ ዘርፍ ላይ መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። በተጨማሪም እነዚህ ድርጅቶች ሥራቸውን ለማስጀመርና መሰረተ ልማታቸውን ለመትከል ከፍተኛ የሰው ኃይል ይፈልጋሉ" ይላል አቶ አዲስ።

"ለምሳሌ በኬንያ ትልቁ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢው ሳፋሪኮም በስሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አገልግሎት ሰጪዎችን እየጠቀመ ነው። ድርጅቱ በሚያቀርበው 'ኤምፔሳ' በተሰኘው የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ውስጥ በርካታ ወጣቶችና ሥራ ፈጣሪዎች በወኪልነት ይሰራሉ። ይሄ የእኛም አገር እውነታ የመሆኑ ነገር አያጠራጥርም።"

ይህ የቴሌኮም አቅራቢዎች ጥምረት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ እስከ 1.5 ሚሊዮን የሚደርሱ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር የሚጠበቅ ሲሆን እስከ 8.5 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ መዋዕለ ነዋይን ወደ አገሪቱ እንደሚያስገባ ይታመናል።

የማዕድን ዘርፍ

"መንግሥት አሁን ትልቅ ትኩረት እየሰጠው የሚገኘው ዘርፍ የማዕድን ዘርፉ ነው። የውጭ ንግዱም ቢሆን በጣም እየጨመረ ሲሆን ከቡና በላይ በኤክስፖርት ከፍተኛ ገቢ የሚገኘው ከወርቅ ነው። በዓመት 600 ሚሊየን ዶላር ከወርቅ ይገኛል።"

በዚህ ምክንያት በርካታ ኢንቨስተሮች ወደዚህ ዘርፍ እየገቡ ነው። ከማዕድን ማውጫዎች ግንባታ፣ ማጓጓዣና ማቀነባበሪያዎች ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የተማረ የሰው ኃይል ይፈልጋሉ። ይህ ዘርፍ በሚቀጥሉት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የሥራ እድል እንደሚፈጥር እንደሚሆን ይናገራል።

የሎጂስቲክስና የንግድ መጋዘን አገልግሎት

ማንኛውም አይነት ምርት ከተመረተ በኋላ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለማከፋፈል ትልልቅና ዘመናዊ መጋዘኖች ያስፈልጋሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችና ማኅበራት መፈጠራቸው ግድ ነው።

"ሌላው ቀረቶ እንደ ድሮው አስፈላጊ የሆኑት እነ ሽሮ፣ በርበሬና ሌሎችም መሬት ላይ አስጥቶ፣ አዘጋጅቶና አስፈጭቶ መጠቀም እየቀረ ነው። እነዚህን አስፈላጊ ግብአቶች በትክክል አዘጋጅቶ ማከፋፈል እየተጀመ ነው። ዘመናዊ መጋዘኖችና ማቀነባበሪያዎች በጣም አስፈላጊ እየሆኑ ነው የሚመጡት።"

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሰዎች ሁሉም ነገር ጣጣውን ጨርሶ በቤታቸው ደጃፍ ላይ እንዲቀርብላቸው መጠየቅ ይጀምራሉ። አብሮት ደግሞ የቤት ለቤት አገልግሎቶች ይስፋፋሉ።

አቶ አዲስ ይህ ዘርፍ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሥራ ፈጣሪዎችን እንደሚያፈራና ለበርካቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ትልቅ እምነት አላቸው።

የወጣቶች ትኩረትና ተስፋ

እንደ ዓለም ባንክ ጥናት ከሆነ አነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ለመጀመር የሚያስፈልጉ ምዝገባዎችንና ፍቃድ የማውጣት ሂደትን ለማከናወን በኢትዮጵያ 152 ዶላር (6,640 ብር) ያስፈልጋል ።

ከአፍሪካ አገራት ሩዋንዳ ያለምንም ገንዘብ የራስ ሥራ ለመጀመር የሚቻልባት አገር ስትሆን ኢኳቶሪያ ጊኒ ደግሞ ከአፍሪካ ከፍተኛው ወጪ (2,321.99 የአሜሪካ ዶላር) ወጥቶ ሥራ የሚጀመርባት አገር ናት።

ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በኢትዮጵያ አነስተኛ ንግድ ለመጀመር ቀላል መሆኑን ማየት ይቻላል።

በርካታ ተማሪዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁበትና አዳዲስ ተማሪዎች ደግሞ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የሚቀላቀሉበት ወቅት እንደመሆኑ ወጣቶች ሥራ አጥ ላለመሆንና የራሳቸውን ሥራ ለመጀመር ምን አይነት ነገሮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው?

"አሁን ኢትዮጵያም እያለፈችብት የምትገኘው ያደጉትና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ያለፉበትን መንገድ ነው። እኔ ወጣት በነበርኩበት ጊዜ የነበረውና አሁን ላይ ያሉት ወጣቶች ያሉበት ጊዜ በጣም የተለያየ ነው። የአሁን ወጣቶች ሁሉም መረጃ በእጃቸው ነው የሚገኘው" ይላል አዲስ።

ለዚህ ደግሞ ወጣቶች የመንግሥት ፖሊሰ ምን ላይ ያተኩራል፣ የትምህርት ሚኒስቴር የትኞቹን ዘርፎች ያበረታታል የሚለውን ቀደም ብለው ማወቅና መወሰን መቻል አለባቸው።

"መንግሥት ሁሌም ቢሆን በአምስት ዓመታት ውስጥ በነዚህ በነዚህ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጌ፤ ይህን ያህል ገቢ ፈጥሬ፤ ይህን ያክል ሥራ ፈጥሬ እቅዴን አሳካለው ይላል። ወጣቱ ደግሞ ይህንን አይቶ ውሳኔዎቹን እና የትምህርት ምርጫዎቹን ከነዚህ ነጥቦች አኳያ ማድረግ አለበት" ሲል ይመክራል።

የትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ አስተማሪዎች የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶችን ለነዚህ ዘርፎች ሊጠቅሙ በሚችሉ መንገዶች ሊያዘጋጇቸው እንደሚገባ ያሳስባል።

"ፖሊሲዎችና ትምህርት እጅና ጓንት መሆነ መቻል አለባቸው። አንደኛው ያለአንደኛው የትም አይደርስም። መደጋገፍ መቻል አለባቸው" ይላል።

እንደ ምሳሌም የቱሪዝም ዘርፉ አንድ ኢንቨስተር ቱሪስቶችን የሚያስተናግድ ዘመናዊ ሆቴል ልክፈት ብሎ ቢነሳ ከጅምሩ አስተናጋጆች፣ የምግብ አብሳዮች፣ ሆቴል አስተዳደሮችና ሌሎች ሠራተኞችን መቅጠር አለበት።

"ስለዚህም በበቂ ሁኔታ ለዚህ ዘርፍ ተብሎ የሰለጠነ የሰው ኃይል መኖር አለበት" በማለት ለዘርፎቹ የሚሆኑ ባለሙያዎችን የማፍራት አስፈላጊነትን አጽንኦት ይሰጠዋል።