አቶ እስክንድር ነጋ 'ለደኅንነታቸው ስጋት እንዳላቸው' ለኢሰመኮ ገለጹ

በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ሊቀ መንበር አቶ እስክንድር ነጋ በማረሚያ ቤት ከደኅንነታቸው ጋር በተያያዘ ቀጣይ ስጋት እንዳላቸው እንደተናገሩ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

ባለፈው ሐሙስ ባሉበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ ከአንድ ታራሚ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ከተገለጸ በኋላ ኢሰመኮ ጉዳዩን ማጣራቱን አመልክቶ አቶ እስክንድር በዚሁ ሳቢያ አካላዊ ጉዳት እንዳጋጠማቸው አረጋግጧል።

በዚህም ሳቢያ አቶ እስክንድር ነጋ በቀረበባቸው ክስ ላይ ምስክሮችን ለመስማት ባለፈው ሐሙስ በነበራቸው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ ሳይገኙ በመቅረታቸው ችሎቱ ለሌላ ቀን መዘዋወሩን ከጠበቆቻቸው መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ በዕለቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አቶ እስክንድር በዕለቱ ፍርድ ቤት ያልተገኙት ክስተቱ በፈጠረባቸው ስሜት ምክንያት በወሰዱት የግል ውሳኔ እንደሆነና፣ "አሁንም ከደኅንነታቸው ጋር በተያያዘ ቀጣይ ስጋት እንዳላቸው" መናገራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ጨምረውም የተፈጠረው ክስተት "ተራ ጠብ ነው ብለው እንደማያምኑና በፍርድ ቤት የምስክር ማሰማት ሂደት እያነሷቸው ባሉ መስቀለኛ ጥያቄዎችና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዘ እንደሆነ" እንደሚያምኑ ለኮሚሽኑ መናገራቸውን ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም አቶ እስክንድር ነጋ በሚገኙበት የቂሊንጦ ጊዜያዊ ማረፊያ የሚመለከታቸውን ግለሰቦች በማናገር ማጣራት ማድረጉን አመልክቷል።

በዚህም መሠረት አቶ እስክንድር የፍርድ ቤት ቀጠሮ በነበራቸው ሐሙስ ጥቀምት 11/2014 ዓ.ም. ጠዋት በሚገኙበት ዞን ውስጥ የስፖርት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እያሉ ከሌላ እስረኛ ጋር የተነሳው የቃላት ልውውጥ ወደ አካላዊ ግጭት መሸጋገሩንና ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል።

በክስተቱ አቶ እስክንድር በግራ እግር አውራ ጣታቸው ላይ እብጠት፣ በሁለቱም ጉልበቶቻቸው ላይ የመላላጥና በቀኝ ቅንድባቸው ላይ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፣ በሌላኛው እስረኛ ላይም በቀኝ እጅ ጣቶቻቸው ላይ የመፋፋቅ ጉዳት እንደደረሰባቸው መመልከቱን ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

ጨምሮም በአቶ እስክንድር እና በእስረኛው መካከል ከዚህ ቀደም አለመግባባት እንደነበረና እስረኛው ከተዘዋወሩበት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በቅርቡ የተመለሱ መሆኑንም ኮሚሽኑ መገንዘብ እንደቻለ አመልክቷል።

ሁለቱም ታሳሪዎች በግጭቱ በደረሰባቸው ጉዳት ተገቢው የማጣራት እና የሕክምና ድጋፍ ከማረሚያ ቤቱ እንደተደረገላቸው እና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ክስ ለመመስረት ፍላጎት እንደሌላቸው ኮሚሽኑ ገልጿል።

በማረሚያ ቤቱ ካጋጠመው ከዚህ ክስተት በኋላ የታሳሪዎችን ደኅንነት ስለማረጋገጥ እንዲሁም በእስረኞች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችና ፀቦችን መከላከልና በሚከሰቱበት ጊዜ ፈጣን እርምጃዎችን መውሰድን በተመለከተ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ኢሰመኮ ምክር መስጠቱን ጠቅሷል።

ከረዥም የፍርድ ቤት ሂደት በኋላ በአቶ እስክንድር እና በሌሎች ተከሳሾች ላይ በቀረበው የክስ መዝገብ ምስክሮች መሰማት የጀመሩት ረቡዕ ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም አቶ እስክንድር በነጋታው ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት ችሎቱ አለመቀጠሉንና ለሰኞ ጥቅምት 15/2014 ዓ.ም. ሌላ ቀጠሮ መያዙን ጠበቃዎቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ እስክንድር ነጋና ሌሎች የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት በ2012 ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ በታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ከተቀሰቀሰው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ ይገኛሉ።