በኢኳዶር ማረሚያ ቤት በተነሳ ጸብ 116 ታራሚዎች ተገደሉ

የኢኳዶር ማረሚያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, EPA

በኢኳዶር ታሪክ አሰቃቂ በተባለለት የእስር ቤት ጸብ እስካሁን ድረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 116 መሻገሩን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

በማረሚያው ውስጥ ባሉ ተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል በተነሳው በዚህ ፍልሚያ ማክሰኞ ዕለት ብቻ አምስት ሰዎች አንገታቸው የተቀላ ሲሆን ቀሪዎቹ በጥይት ተገድለዋል።

የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ፋዉስቶ ቡኔናዎ እንዳሉት እስረኞቹ ቦንቦችንም ተወራውረዋል። ማረሚያ ቤቱን መልሶ ለመቆጣጠርም 400 አካባቢ ፖሊሶች ተሰማርተዋል።

በዚህ ማረሚያ ውስጥ በርካታ አለማቀፍ ሰንሰለት ያላቸው የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን አባላት ይታሰሩበታል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ግጭቱ በአንድ ከፍተኛ አቅም አለው በተባለ እና በኢኳዶር ውስጥ በሚንቀሳቀስ የሜክሲኮ የዕጽ አዘዋዋሪ የወንበዴ ቡድን ትዕዛዝ የተከሰተ ነው።

የኢኳዶር ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሃላፊ ለአንድ አገር ውስጥ የራዲዮ ጣቢያ ሁኔታውን «የሚረብሽ» ሲሉ ገልጸውታል።

«ማክሰኞ ከቀኑ 8 ሰአት አካባቢ ማረሚያውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ችለን የነበረ ቢሆንም፣ ምሽት ላይ ግን የተኩስ እና የፍንዳታ ድምጾች መሰማተቸው ይታወቃል። ዛሬ ጠዋት ግን ማረሚያውን በድጋሚ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አስገብተናል። ግጭቱ ወደነበረባቸው ክፍሎች ስንገባም በርካታ አስከሬኖችን አግኝተናል» ሲሉ የማረሚያው ሃላፊ ተናግረዋል።

ፖሊስ እንዳለው እስረኞች ከአንደኛው የማረሚያው ክንፍ ወደ ሌላኛው ክንፍ ለመሄድ በተቦረቦረ ቱቦ ውስጥ መሄድን መርጠዋል። በፍልሚያው ከተገደሉት በተጨማሪ 80 እስረኞች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ፖሊስ ስድስት የምግብ አብሳዮች መውጫ በማጣት ከተደበቁበት ለማውጣት መቻሉን ገልጿል።

የኢኳዶር ፕሬዘዳንት በአገሪቷ የማረሚያ ቤት ስርአት ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጀዋል።

ማረሚያ ቤቱ በኤኳዶር የሚንቀሳቀሰው ብሎም ሲናሎአ ከተሰኘው ከታዋቂው የሜክሲኮ የዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን ጋር ግንኙነት ያለው ሎስ ቾኔሮስ የተሰኘው ቡድን አባላት የሚታሰሩበት ነው።

ነገር ግን ጃሊስኮ ኒው ጄኔሬሽን የተሰኘው ሌላ የሚክስኮ የወንበዴዎች ቡድን ከኢኳዶር የወንበዴዎች ቡድኑ ጋር ጥምረት ለመፍጠር እና ከኢኳዶር ወደ ማዕከላዊ አሜሪካ መረቡእን ለመዘርጋት ጥረት እያረገ መሆኑ ተነግሯል።

የኢኳዶሩ ፕሬዘዳንት ባለፈው ሰኔ ላይ እንዳሉት የአገሪቱ የማረሚያ ቤቶች ስርአት መሸከም ከሚችለው ሰው 30 በመቶ በላይ ተሸክሟል።

ይህንን ለመፍታትም በትንንሽ ወንጀሎች የታሰሩ ሰዎችን እንዲሁም ከተፈረደባቸው አመታት አብዛኛውን የጨረሱ ታራሚዎችን ለመፍታት ሂድት መጀመራቸውን አስታውቀው ነበር።