ዛሬ እየተካሄደ ያለው ሁለተኛው ዙር ምርጫና የሕዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ

የጂግጂጋ ምርጫ

ዛሬ መስከረም 20/2014 ዓ.ም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የስድተኛው አገር አቀፍ ምርጫና የሕዝበ ውሳኔ የሆኑ የድምጽ መስጠት ሂደቶች ይከናወናሉ።

እንዲሁም በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ቀጣይ የአደረጃጀት እጣፈንታቸውን በሚወስነው ሕዝበ ውሳኔ ላይ ይሳተፋሉ።

ምርጫው የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ቀድሞ ከተያዘለት ጊዜ ሦስት ጊዜ ተራዝሞ ዛሬ የሚካሄደው በአራተኛው ቀነ ቀጠሮ ነው።

በ2012 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በግንቦት 2013 በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ እንዲሁም ጳጉሜ 3 በተመሳሳይ በቦርዱ ውሳኔ የተራዘሙት እነዚህ የምርጫ እንቅስቃሴዎች ዛሬ በ4ተኛ ቀጠሯቸው ይካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሶማሌ እና የአፋር ክልሎች በአጠቃላይ እንዲሁም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም በደቡብ ብሤር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ደግሞ የተወሰኑ የምርጫ አካባቢዎች ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተሳታፊ አልነበሩም።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች የትግራይ ክልል ያሉትን 38 መቀመጫዎችን ጨምሮ በ102 መቀመጫዎች በሰኔው ምርጫ ሳይካተቱ ቀርተው ነበር።

በሶማሌ ክልል ሲካሄድ የነበረው ቅድመ ምርጫ ሂደት ኢዜማ እና የኦጋዴን ነጻነት ግንባር ባቀረቡት አቤቱታ ምክንያት ነበር ካለፈው ሰኔ እንዲራዘም የተደረገው። ፓርቲዎቹ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ምርጫውን ታአማኒነት የሚሸረሽር ነው ሲሉ ነበር አቤት ያሉት።

ለዚህም ተጠያቂ አድርገው የነበረው የገዢው ፓርቲ ብልጽግና ካድሬዎችን ሲሆን በተለይም የምርጫ ካርዶችን ለደጋፊዎቻቸው በገፍ አከፋፍለዋል የሚለው ዋናው ክሳቸው ነበር።

በተጨማሪም ሌሎች የመራጮች መመዝገቢያ ሰነዶች ያለአግባብ በገዢው ፓርቲ አመራሮች ቁጥጥር ስር ውለዋል ሲሉም ክሳቸውን አሳውቀው ነበር።

ይህንን ተከትሎ በቦርዱ አባል አቶ ውብሸት አየለ የሚመራ ልዑክ ወደ ሶማሌ ክልል ተጉዞ አቤቱታዎቹን ካጣራ በኋላ ቦርዱ የምርጫውን እንቅስቃሴዎች ለማቋረጥ እና እነዚህን ቅሬታዎችን ለመፍታት ነበር የወሰነው።

ከጳጉሜ አንድ ተገፍቶ ዛሬ እንዲደረግ ቦርዱ ያቀደው ይህ ምርጫ ግን የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅሬታ ቀጥሎ ምርጫውን ጥለው መውጣታቸውን ይፋ ካደረጉ ከሳምንት በላይ ሆኗቸዋል።

በክልሉ በአንድ ወቅት ምርጫ አሸንፎ የሚያውቀው እና ለዓመታት በትጥቅ ትግል ውስጥ የቆየው በአሸባሪነት ተፈርጆ የነበረው ኦብነግ በምርጫው መሳተፍ ፋይዳው ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል የሚሉ ግምቶች ነበሩ።

ግንባሩ ታጣቂዎቹን ወደ ሰላማዊ ኑሮ በመመለስ ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ማስገባቱን ከወራት በፊት ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ከክልሉ ምርጫ እራሱን አግልሏል።

በኢትዮጵያ በቆዳ ስፋቱም ሆነ በሕዝብ ብዛቱ ትንሹ ክልል በሐረሪም ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በዚህኛው ዙር ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የሐረሪ ክልል ድምጽ የመስጠት ሂደት ለመዘግየቱ ምክንያት የሆነው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በሐረሪ ክልል መካከል የነበረው የፍርድ ቤት ክርክር አስፈላጊ የምርጫ ቁሳቁሶች ዝግጅት ላይ ባስከተለው ለውጥ ነው።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሐረሪ ብሔር ተወላጆች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል ሆነው ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ተወዳዳሪዎችን መምረጣቸው ሕገመንግስቱን ጨምሮ የተለየያዩ ሕግጋቶችን የሚጥስ ስለሆነ አሰራሩ እንዲቀር አስተዳደራዊ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

ነገር ግን ይህንን የቦርዱን አስተዳደራዊ ውሳኔ በመቃወም ፍርድ ቤት የወሰደው ጉባዔው ምርጫ ቦርድን በመርታት ቀደም ሲል የነበረው አሰራር ተግባራዊ እንዲሆን ተወስኖ ምርጫው ዘግይቶ እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል።

ሌላው በዛሬ ዕለት የሚካሄደው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ነው። ከሰኔው ምርጫ ጋር ይደረጋል ተብሎ የነበረው ይህ ሕዝበ ውሳኔ የፀጥታ ችግሮች በማጋጠማቸው ነበር ምርጫ ቦርድ እንዲራዘም የወሰነው።

የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ የዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በመውጣት አንድ የጋራ ክልል ይመስርቱ ወይስ በነባሩ ክልል ይቀጥሉ የሚለው በዚህ ሕዝበ ውሳኔ የሚለይ ይሆናል።

ዛሬ በሚካሄደው ምርጫና ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ለመስጠት 7.6 ሚሊዮን ሰዎች የተመዘገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል አስታወቋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጦርነት ቀውስ ውስጥ ያለውን የትግራይ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በፀጥታ ምክንያት ምርጫ አሁንም ማካሄድ ያልቻለባቸው አካባቢዎች አሉ።

ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ ከሚባል ጥቂት የጎደለውን አዲሱን ፓርላማ ይዞ በቀጣይ ሳምንት አዲስ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን አግኝቷል።