ተጨማሪ ሁለት ፓርቲዎች በሶማሌ ክልል ከሚደረገው ምርጫ እራሳቸውን አገለሉ

የፎቶው ባለመብት, NEBE
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ በሶማሌ ክልል ተሳታፊ የነበሩ ሁለት ተጨማሪ ፓርቲዎች እራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን አስታወቁ።
በሶማሌ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት እጩዎችን አቅርበው የነበሩት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) እና የነፃነትና የእኩልነት ፓርቲ (ነዕፓ) ከመጪው ምርጫ እራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል።
ከሁለቱ ፓርቲዎች በተጨማሪ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) መስከረም 20 ሊካሄድ በታቀደው ምርጫ እንደማይሳተፍ ማስታወቁ ይታወሳል።
ኦብነግ በምርጫው አልሳተፍም ያለው፤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባና ሌሎች ችግሮችን በተመለከተ አቅርቦት የነበረው አቤቱታ መፍትሄ ባለማግኘቱ እንደሆነ፣ የኦብነግ የአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ አብዱላሂ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ኢዜማ እና ነዕፓ በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል በተካሄደው የመራጮች ምዝገባ ሂደት እንዲሁም ከአጠቃላይ የምርጫ ሕግ እና ሥርዓት ጋር በተያያዘ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረብናቸው ቅሬታዎች ሊፈቱ ባለመቻላቸው እራሳችንን ከምርጫው አግልለናል ብለዋል።
ሁለቱ ፓርቲዎች፤ ከዚህ በፊት ተሰርቆ የነበረው የምርጫ ቁሳቁስ በአዲስ እንዲተካ የጠየቅን ቢሆንም አሁን ግን ቀድሞ ተዘርፎ በነበረው ካርድ ወደ ምርጫ በመገባቱ ምርጫው ተዓማኒነት አይኖረውም" ብለዋል በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ።
ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲዎቹ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መዋቅር ከመንግሥት መዋቅር ጋር የተዋሀደ በመሆኑ የምርጫውን ፍትሀዊነት እና ተዓማኒነት ያሳጣል የሚሉ እና ሌሎች ምክንያቶችን በመዘርዘር ከምርጫው እራሳቸውን ማግለላቸውን ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ መስከረም 20 የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ ትናንት ለጋዜጠኞች ማብራሪያ በሰጠበት ወቅት ምርጫ ባልተደረገበት የሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ለቦርዱ አቤቱታ ቀርቦ እንደነበር ቦርዱ አስታውሷል።
ይህን ተከትሎም በክልሉ በሰባት ምርጫ ክልሎች በድጋሚ የመራጮች ምዝገባ ተከናውኗል ብሏል ቦርዱ።
የመራጮች ምዝገባ የተካሄደውም ቦርዱ ባሰማራው አጣሪ ቡድን ውሳኔ ላይ መስረት በማድረግ መሆኑም ተገልጿል።

መስከረም 20 2014 ዓ.ም. በሶማሌ፣ በሐረሪ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ምርጫ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዚሁ ዕለትም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመሆን ሕዝበ ውሳኔ ይካሄዳል።
በዚህ ምርጫ እና ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ለመስጠት 7.6 ሚሊዮን ሕዝብ መመዝገቡን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቋል።
በፀጥታ ችግር፣ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ በታዩ ግድፈቶች፣ በመራጮች ምዝገባ ላይ የቀረቡ አቤቱታዎችን ለማጣራት ጊዜ በማስፈለጉ የድምፅ መስጫው ቀን በአንዳንድ ክልሎች የምርጫ ክልሎች እንዲራዘም መወሰኑ ይታወቃል።












