"የሦስት ዓመቱ ልጄ አሁን ተረት የሚያወራው ስላጣው እግሩ ነው" አባት ካሣው ጥጋቤ

ለቀናት በአካባቢው የሚሰማው የከባድ መሣሪያ ተኩስ እንቅልፍ ከመንሳት ባሻገር ከባድ ስጋትን ፈጥሯል። ተኩሱ እረፍት አልነበረውም። መውጣት መግባት አይቻልም ነበር። መንቀሳቀስም እንዲሁ።

ነሐሴ ወር ውስጥ ለአራት ቀናት ያህል በህወሓት አማጺያን ሥር በነበረችው የደቡብ ጎንደሯ ጋሳይ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሣው ጥጋቤ፤ ይሻል እንደሁ ብለው ቤተሰባቸውን ሰብስበው ሕጻናት ልጆቻቸውን እያረጋጉ ቤት መሆንን መርጠዋል።

"ሌላው ቀርቶ ዕቃ ለመዝረፍና ለማውጣት ቤት ሲያፈርሱ የሚሰማው ድምጽ ከጥይት በላይ ነበር የሚጮኸው" ይላሉ።

ለሦስት ቀናት በዚህ መልኩ ነው ያሳለፉት።

አቶ ካሣው ነሐሴ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. አካባቢው እንዴት ውሎ እንዳደረ ለማየት ማለዳ ነበር ጎናቸውን ካሳረፉበት የተነሱት። አያት፣ አክስት፣ እናትና ሁለት ሕጻናት ልጆችም አብረው ተነስተዋል።

ሳሎን ቤት ተቀምጠው ስለ ውሎ አዳራቸው ወግ ያዙ።

ሩጦ ያልጠገበው የሦስት ዓመት ልጃቸው ዮናስ ካሣውም በመካከላቸው ወለሉ ላይ ከወዲህ ወዲያ እያለ እያጫወታቸው ነበር።

በዚህ መሃል ግን ድንገት የተተኮሰ ከባድ መሣሪያ ቤታቸው ላይ አረፈ። ማንም ስለማንም ሁኔታ ለማወቅ መረጋጋት አልነበረም።

"እንደምንም ሁሉንም እየተጣራሁ ደኅንነታቸውን ጠየቅኩ" ይላሉ አቶ ካሣው።

"ደህና ነን። ተርፈናል" የሚል መልስ አገኙ። ሕጻኑ ልጃቸውንም "ዮናስ!" ብለው ተጣሩ።

"አቤት" አላቸው በሚኮላተፍ አንደበቱ። በዚህ ጊዜ ልባቸው ትንሽ ፋታ አገኘ።

አቶ ካሣው እንደሚሉት ቤቱ በተኩሱ ምክንያት በተፈጠረው አቧራና ጭስ ታፍኖ ስለነበር አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር ለመተያየትም አዳጋች ነበር።

ሕጻኑን ልጃቸውን ይጫወት ከነበረበት ቦታ ሄደው አነሱት። በአቧራ ተሸፍኖ ነበር ያገኙት።

ደኅንነቱን ለማረጋገጥ ወደ ደጅ ይዘውት ወጡ።

ፊቱ እና ከወገቡ በላይ ያለው አካሉ ደህና ነው። "ተመስገን!" አሉ። በድንጋጤ ሙሉ አካሉን ልብ አላሉትም ነበር።

"ድንገት ዓይኔን ከፊቱ ላይ ሸርተት ሳደርግ ግራ እግሩ የለም" ይላሉ አባት ሳግ ድምጻቸውን እየታገለው። የሚያደርጉት ጠፋቸው፤ የሚይዙት የሚጨብጡትን አጡ።

በተኩስ እሩምታው ላለመጠለፍ ቤታቸውን ዘግተው ከእነቤተሰባቸው የተቀመጡት እኝህ አባት የልጃቸው ደም እየፈሰሰ ለማየት ግን አልቻሉም።

"ከሞትንም አብረን እንሙት፤ ዓይኔ እያየ አይሞትም አልኩና አጋዥ በሌለበት የሦስት ዓመት ልጄን አቅፌ ወደ ሕክምና ሮጥኩ" ይላሉ ሁኔታውን ሲያስታውሱ።

እናትም ዓይኖቿ በእምባ እየታጠቡ ተከተሉ።

ትራንስፖርት የለ። ፈረስና በቅሎ መጫን የለ- ጦርነት ነው። ሌላው ቀርቶ በትክክለኛና ከዚህ ቀደም በሚያውቁት መንገድ መጓዝም አስፈሪ ነበር ይላሉ አቶ ካሣው።

የነበራቸው ብቸኛ አማራጭ ጦርነት በሌለበት በበረሃ፣ በየጥሻው እያቆራረጡ መጓዝ ነው።

እርሳቸው እንደሚሉት የስምንት ሰዓት የእግር መንገድ ተጉዘው እስቴ ከተማ ደረሱ። ይህን ሁሉ መንገድ ሲጓዙ ህጻኑ ደም እየፈሰሰው ነበር።

"ከእኛ መካከል እርሱ መመታቱ፤ ይህን ያህል ደም ፈሶት በሕይወት መትረፉ እኔን ብቻ ሳይሆን ያየ የተመለከተውን ሁሉ ያስደንቃል፤ የፈጣሪ ሥራ ነው" ይላሉ አቶ ካሣው።

በንብረት ላይ ካልሆነ በስተቀር በሌሎቹ የቤተሰባቸው አባል ላይ የደረሰ ጉዳትም የለም።

አቶ ካሣው ረዥሙን የእግር መንገድ የጨረሱት ልጃቸውን አቅፈው ብቻ አልነበረም። "በምንስ ገንዘብ ታክሞ ይተርፋል" በሚለው ሃሳብ እየናወዙ እንጂ።

"በወቅቱ ኪሴ ውስጥ የነበረው 2 ሺህ ብር ብቻ ነበር" ይላሉ አቶ ካሣው።

ይሁን እንጂ "አሁን ሰው እየተዛዘነ ነው" የሚሉት አቶ ካሣው፤ እስቴ ከተማ ሲደርሱ ከሚያውቋቸው ሰዎች ተበዳድረው ኮንትራት መኪና ይዘው ባሕር ዳር ከተማ ደረሱ።

ቀያቸው በመከላከያና በአማራ ልዩ ኃይል ቁጥጥር ሥር መዋሉን የሰሙትም እርሳቸው ልጃቸውን ወደ ሕክምና ይዘው እየሄዱ ሳሉ ነበር። "ትንሽ ብትታገስ መኪና ታገኝ ነበር" ከሚሉ አስተያየት ሰጪዎች።

"የህወሓት ኃይሎች ጥቃቱን የፈፀሙት ተሸንፈው ሊወጡ ሲሉ ነው፤ እኔ ይህንን አላወቅኩም ነበር" ይላሉ።

በከባድ መሣሪያ ጥቃቱ ግራ እግሩን ከጉልበቱ በታች ያጣው ዮናስ፤ በመጨረሻም በባሕር ዳር ሕክምና አገኘ።

"አንድ ልጅ ነበር እና እየተጫወተ ሳለ . . ." የዮናስ ተረት

አባቱ አቶ ካሣው እንደሚሉት ልጃቸው ዮናስ የሦስት ዓመት ልጅ ይሁን እንጂ ቀልጣፋ፣ ተጨዋች፣ በሳል እና አስተዋይ ነው።

"የሆነውን ሁሉ አይረሳም" ይላሉ።

ለማረሳሳት ቢሞክሩም አልቻሉም። የሆነውን ሁሉ በተረት መልክ ማውራት እንደጀመረም ይናገራሉ።

"'አንድ ልጅ ነበረ እና ሲጫወት የሆነ ነገር ፈንድቶ እግሩ የለም. . .' ይላል" በማለት በተሰበረ ድምጽ ልጃቸው በእራሱ ላይ የደረሰውን በጨቅላ አንደበቱ እንደተረት መልሶ እንደሚተርክ አባት ይገልጻሉ።

"አይ! እንደዚህ ዓይነት ተረት የለም" በማለት በሌላ ተረት ለማረሳሳት ሲሞክሩም እንደገና "አንድ ልጅ ነበረ እና ሲጫወት የሆነ ነገር ፈንድቶ እጁ የለም. . ." በሚል እንደሚተካው አባቱ አቶ ካሣው ተናግረዋል።

"እንደሱ የሚባል ተረት የለም" ሲሉትም ተረቱን በማጽናናት ይተካዋል። "ይችኛዋ እግሬ ግን አለችልኝ" ይላል ዮናስ ቀኝ እግሩን እየነካካ።

አባቱ አቶ ካሣው እንደሚሉት ለሆስፒታል የአልጋና መድኃኒት የሚያወጡትን ወጪ መሸፈን ባለመቻላቸው አሁን ላይ ዮናስ ከሆስፒታል ወጥቶ በተመላላሽ ሕክምናውን እየተከታተለ ነው።

የተፈፀመው ጥቃት በታላቅ ሴት ልጃቸውም ሆነ በመላ ቤተሰቡ ላይ ያደረሰው ተጽዕኖው ቀላል አይደለም ያሉት አቶ ካሣው አሁንም መረጋጋት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

አሁን የሚያሳስባቸው ጥቃቱ በቤተሰባቸው ላይ ያስከተው መረበሽ እንዲሁም ሮጦ ያልጠገበው ታዳጊ ልጃቸው የደረሰው ጉዳት በሥነ ልቦናው ላይ ሊያሳድር የሚችለው ቀውስ ነው።

አቶ ካሣው ፋርጣ ወረዳ በህወሓት ቁጥጥር ሥር በነበረበት ቀናት በከተማው 12 ሰዎች እንደተገደሉና በዙሪያው ባሉ ቀበሌዎች በርካታ ሰዎች እንደተገደሉ መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የግለሰብና የመንግሥት ንብረት መዘረፉንና መውደሙንም አቶ ካሣው ገልጸዋል።

የህወሓት አማጺያን ይዘዋቸው በነበሩ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃቶችን በመፈፀም ይከሰሳሉ።

ከዚህ ቀደም ደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ በሚገኙት ደብረ ታቦርና ነፋስ መውጫ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሰዎች በከባድ መሣሪያ ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል።

በሰሜን ወሎ ቆቦና አጋምሳ፣ በደቡብ ወሎ ወረባቦ፣ በሰሜን ጎንደር ጭና፣ በዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በአፋር ክልል ጋሊኮማ በርካታ ንጹሃን ሰዎች በህወሓት አማጺያን ጥቃት መገደላቸው ተዘግቧል።

የህወሓት ኃይሎች ግን እነዚህን ጥቃቶች ስለመፈፀማቸው በተደጋጋሚ ያስተባበሉ ሲሆን በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ ጠይቀዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የህወሓት ኃይሎች በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞትና በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩት መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

ከወራት በፊት የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ጦሩን ከትግራይ ካስወጣ በኋላ የህወሓት አማጺያን ወደ አጎራባች አፋርና አማራ ክልሎች በመግባት ጦርነት ከፍተዋል።

በአማራ ክልል ብቻ ከ1.5 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ክልሉ ያስታወቀ ሲሆን በአፋር ክልልም ከ75 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ክልሉ ገልጿል።