ታሊባን፡ በአፍጋኒስታን ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ሴቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታሊባን ወንድ ተማሪዎችና መምህራን ትምህርት እንዲጀምሩ ማዘዙን ተከትሎ ሴት ተማሪዎች ከአፍጋኒስታን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መገለላቸው ተነገረ።
እስላማዊው ቡድን በአገሪቱ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንደሚጀመር ባሳወቀበት መግለጫ ላይ ስለልጃገረዶችም ሆነ ስለሴቶች ያለው ነገር የለም።
አንዲት አፍጋናዊ ተማሪ ውሳኔውን በተመለከተ ለቢቢሲ እንደተናገረችው በጣም አዝናለች። "ሁሉም ነገር በጣም ጨለማ ሆኗል" ብላለች።
ምንም እንኳን ታሊባን ተስፋ የሰጠ ቢሆንም ሴት ተማሪዎችን በተመለከተ የወሰደው እርምጃ አፍጋኒስታን ወደ ቀደመው አስከፊ የታሊባን አስተዳደር እየተመለሰች መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው።
በሌላ ዜና ታሊባን አርብ ዕለት የአገሪቱን የሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴርን በመዝጋት ቀደም ሲል ጥብቅ ሐይማኖታዊ አስተምህሮዎችን በሚያስፈጽም መሥሪያ ቤት እንዲተካ አድርጓል።
መሥሪያ ቤቱ ከአውሮፓውያኑ ከ1996 እስከ 2001 ድረስ በነበረው ጊዜ እስላማዊው የሸሪዓ ሐይማኖታዊ ሕጎችና ግዴታዎችን በጥብቅ ተግባራዊ እንዲደረግ የሚቆጣጠር የሞራል ፖሊስን በየጎዳናው ያሰማራ ነበር።
የትምህርት ቤቶች መልሶ መከፈትን በተመለከተ ዛሬ ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ ላይ "ሁሉም ወንድ መምህራንና ተማሪዎች በየትምህርት ተቋሞቻቸው በመገኘት ትምህርት እንዲጀምሩ" አዟል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው እድሜያቸው በ13 እና 18 መካከል የሚገኙ ተማሪዎች የሚማሩበት ነው።
በአፍጋኒስታን የሚገኙ ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች በጾታ የተለያዩ መሆናቸው ታሊባን የልጃገረዶችን ትምህርት ቤቶች ለመዝጋት ቀላል አድርጎለታል።
ልጃገረድ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ትምህርትን በተመለከተ የወደፊት ተስፋቸው ተስፋ ሰጪ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ጠበቃ ለመሆን የምትፈልገው አፍጋናዊ ተማሪ "ስለወደፊቱ ተስፋዬ በጣሙን ተጨንቄያለሁ" ብላለች።
"ሁሉም ነገር የጨለመ ይመስላል። በየዕለቱ ከእንቅልፌ ስነቃ የወደፊት ሕይወቴ ያሳስበኛል። ቤት ተዘግቼ በመቀመጥ በሬን አንኳኩቶ እንዳገባው የሚፈለግን ወንድ መጠበቅ አለብኝ? ይህ ነው ወይ ሴት የመሆን ዕጣ?" ስትል በተስፋ መቁረጥ ጠይቃለች።
አባቷም "እናቴ አልተማረችም ነበር፤ አባቴ ዘወትር ደደብ እያለ ያሸማቅቃት ነበር። ሴት ልጄ የእናቴ አይነት ዕጣ እንዲገጥማት አልፈልግም" ብለዋል።
ካቡል ውስጥ ነዋሪ የሆነች ሌላ የ16 ዓመት ተማሪ ደግሞ "አሳዛኝ ቀን ነው" ስትል ገልጸዋልች።
"ዶክተር መሆን እፈልግ ነበር። ይህ ህልሜ አሁን ተሰናክሏል። ወደ ትምህርት ቤት እንድንመለስ የሚፈቅዱልን አይመስለኝም። ሴቶች እንዲማሩ አይፈልጉም" ብላለች።
ከቀናት በፊት ታሊባን ሴቶች በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንዲማሩ እንደሚፈቀድ፤ ነገር ግን ከወንዶች ተለይተውና የተለየ የአለባበስ ሥርዓት እንደሚከተሉ አሳውቆ ነበር።
ዩኒቨርስቲዎች ለሴቶች የተለየ የትምህርት ክፍል የማዘጋጀት አቅም ስለሌላቸው ይህ ውሳኔ ሴቶችን ከትምህርት ውጪ ሊያደርጋቸው እንደሚችል አንዳንዶች ተናግረዋል።
ከ20 ዓመት በፊት ታሊባኖች ከአፍጋኒስታን የመንግሥት ሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ላይ ከፍተኛ መሻሻል ተመዝግቧል።
በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ በመላዋ አፍጋኒስታን የሚገኙ የሴት ተማሪዎች ቁጥር ዜሮ ከሚባልበት ደረጃ ወደ 2.5 ሚሊዮን ከፍ ያለ ሲሆን፣ በአስር ዓመት ውስጥ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ የሴቶች ቁጥር ደግሞ በእጥፍ ጨምሮ ወደ 30 በመቶ ደርሷል። አብዛኛው ይህ ለውጥ የተመዘገበው በከተሞች አካባቢ በሚኖሩ ሴቶች ዙሪያ ነበር።
ታሊባን ወደ ሥልጣን መመለሱን ተከትሎ "በእስላማዊ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ" በአገሪቱ የሴቶች መብት ይከበራል ብሎ ነበር።
















