የአፍጋኒስታን ሴቶች በወንዶች ብቻ የተመሰረተውን የታሊባንን መንግሥት ተቃወሙ

በካቡል የተደረገው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በካቡል እና በሰሜን ምሥራቃዊ አፍጋኒስታን የባዳክሻን ግዛት በደርዘን የሚቆጠሩ ሴቶች በወንዶች ብቻ የተመሰረተውን ጊዜያዊ የታሊባን መንግሥት ምሥረታን ተቃውመዋል።

ተቃዋሚዎቹ ሴት ሚኒስትሮች የሌሉበትን መንግሥት አንቀበልም ሲሉ ተናግረዋል።

ተቃውሞው ከመበተኑ በፊት አንዳንድ ሴቶች ተደብድበዋል ተብሏል።

ኢቲላትሮዝ የተባለው የአገር ውስጥ የዜና ድርጅት አንዳንድ ጋዜጠኞቹ ሰልፉን በመዘገባቸው መታሰራቸውንና መደብደባቸውን ገልጿል።

ለቀረበው ክስ ምላሽ ያልሰጠው ታሊባን እንዲህ ዓይነት ተቃውሞዎች ሕገወጥ ናቸው ሲል አስጠንቅቋል።

ተቃዋሚዎች ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ ያስፈልጋቸዋል ያለ ሲሆን ለሚጠቀሙት ቃላትም መጠንቀቅ አለባቸው ብሏል።

ማክሰኞ በምዕራባዊቷ ሄራት ከተማ በተደረገ ሰልፍ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።

የአውሮፓ ሕብረት እስላማዊው ቡድን መንግሥቱን "አካታች እና ሁሉንም የሚወክል" ለማድረግ የገባውን ቃል እንዳላከበረ ገልጿል።

አሜሪካም በበኩሏ ጊዜያዊው መንግሥት በአሜሪካ ላይ ከተፈጸሙት ጥቃቶች ጋር የተዛመዱ ሰዎችን ያካተተ ነው ስትል ስጋቷን ገልጻለች።

ረቡዕ ከ20 የምዕራባውያን አገራት ጋር በበይነ መረብ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የታሊባን መንግሥት "በእርግጥ የአካታችነትን ፈተና አያሟላም። በተጨማሪም መጥፎ ነጥብ ያላቸውን ሰዎችም ያካተተ ነው" ብለዋል።

"ታሊባን ዓለም አቀፍ ሕጋዊነትን እና ድጋፍን ይፈልጋል። ማንኛውም ሕጋዊነት እና ድጋፍን ደግሞ በሥራው ማግኘት አለበት" ብለዋል።

ቻይና በተቃራኒው የአፍጋኒስታን 'የሦስት ሳምንት አለመረጋጋት' ብላ የጠራችውን ጊዜ ማብቃቱን በደስታ እንደምትቀበል በመግለጽ 31 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለመስጠት ቃል ገብታለች።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጊዜያዊ መንግሥት መመሥረቱ "ሥርዓትን ለመመለስ እና አገሪቱን ለመገንባት አስፈላጊ እርምጃ" ብለውታል።

ጸረ-ታሊባን የሆነው ናሽናል ሬዚስታንስ ፍሮንት ኦፍ አፍጋኒስታን (ኤንአርኤፍ) ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለአዲሱ መንግሥት ዕውቅና እንዳይሰጥ ጠይቋል።

ካቢኔውን 'ሕገ-ወጥ' ያለ ሲሆን ቡድኑ ከአፍጋኒስታን ሕዝብ ጋር ያለውን ጠላትነት በግልጽ የሚያሳይ ብሎታል።

በአህመድ ማሱድ የሚመራው ኤንአርኤፍ የጸረ-ታሊባን ምሽግ በሆነችውና ከካቡል በስተሰሜን በፓንጅሺር ሸለቆ የታሊባን ታጣቂዎችን እየተዋጋ ሲሆን አካባቢው የጸረ-ታሊባን ጠንካራው ይዞታ ነው።

በፓንሽሽር ያለውን ኤንአርኤፍን አሸንፈናል ብለው አጥብቀው ቢከራከሩም የኤን አር ኤፍ መሪዎች አሁንም እየተዋጋን ነው ይላሉ።

በካቡል የተደረገው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, EPA

አዲሱ መንግ

ማክሰኞ ታሊባን በሙላ መሐመድ ሐሳን አኩንድ የሚመራውን ጊዜያዊ ካቢኔውን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አድርጓል።

ሐሳን አኩንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በኋላም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ታሊባን ለመጨረሻ ጊዜ አፍጋኒስታንን እእአ ከ1996 እስከ 2001 ባስተዳደረበት ወቅት ሠርተዋል።

እንደ ብዙዎቹ የአዲሱ የካቢኔ ሚኒስትሮች በቀድሞው መንግሥት በነበራቸው ቦታ በተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

ሐሳን አኩንድ ረቡዕ መቀመጫውን ኳታር ላደረገው አልጀዚራ እንደተናገሩት የቀድሞ የአፍጋኒስታን ባለስልጣናት ወደ አገራቸው መመለስ እንዳለባቸው፤ ደኅንነታቸው እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የታሊባን መሪዎች ከአፍጋኒስታን ሕዝብ ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠብቃቸው "ለዚህ ታሪካዊ ጊዜ ከባድ ኪሳራ ደርሶብናል እናም በአፍጋኒስታን የደም መፍሰስ ዘመን አብቅቷል" ሲሉ ገልጸዋል።

ሌላኛው አዲሱ ሚኒስትር ሲራጁዲን ሐቃኒ የታዋቂው የሐቃኒ ቡድን ኃላፊ ናቸው።

ሐቃኒ በአሜሪካ የውጭ ሽብርተኝነት ድርጅትነት (ኤፍቲኦ) ተሰይሟል። ከአልቃይዳ ጋርም የጠበቀ ግንኙነትን አለው።

ኤፍ ቢ አይ እንደሚለው ሐቃኒ በ20 ዓመቱ ጦርነት ከተፈጸሙት እጅግ አስከፊ ጥቃቶች በስተጀርባ ነበር። እአአ በ2017 በካቡል ከ150 በላይ ሰዎችን የገደለው የመኪና ፍንዳታ ከእነዚህ መካከል ይጠቀሳል።

እአአ በ2008 አንድ አሜሪካዊን በገደለው የሆቴል ላይ ጥቃት ምክንያትም ተፈላጊ ግለሰብ ናቸው።

ታሊባን አፍጋኒስታንን የተቆጣጠረው ከሦስት ሳምንታት በፊት ባደረገው ከፍተኛ ጥቃት ነው። በግጭቱ የተጎዳችውን አገር ኢኮኖሚውን ማረጋጋት እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘትን ጨምሮ ብዙ ከባድ ፈተናዎች ከፊታቸው ተጋርጧል።

ማክሰኞ ከታሊባኑ ከፍተኛ መሪ ማውላዊ ሂባቱላህ አኩንዱዛዳ የተሰጠ መግለጫ መንግሥት የሸሪዓ ሕግን እንደሚያስከብር ተናግሯል። ታሊባኖች ጠንካራ በሆነ የሸሪዓ ትርጓሜያቸው ይታወቃሉ።

ታሊባን ከሌሎች አገራት ጋር "ጠንካራ እና ጤናማ" ግንኙነትን ይፈልጋል። "እስላማዊ ሕግ እና የአገሪቱን ብሔራዊ እሴቶች" እስካልተቃረኑ ድረስ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና ስምምነቶችን ያከብራል ብሏል መግለጫው።

አዲሱ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሳን አኩንድ ከወታደራዊው ይልቅ በሐይማኖታዊ መስመር ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው።

በቅርቡ በለዘብተኛ እና በአክራሪ የታሊባን ታጋዮች መካከል ከተፈጠረው አለመግባባት በኋላ ሹመታቸው እንደ ስምምነት ሆኖ ይታያል።