የሄይቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ከፕሬዝዳንቱ ግድያ ጋር በተያያዘ ከሀገር እንዳይወጡ ታገዱ

የሄይቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆቬኔል ሞሴ በተፈጸመባቸው ግድያ ተሳትፈዋል ተባለው ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ ከሀገር እንዳይወጡ ታግደዋል።

ዓቃቤ ሕግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግድያው ዋና ተጠርጣሪ ከሆነው ከጆሴፍ ፊሊክስ ባዲዮ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያብራሩ የጠየቀ ሲሆን እርሳቸው ላይም ክስ ለመመስረት እቅድ እንዳለው ተሰምቷል።

የፕሬዝዳንቱ ገደይ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድያው ከተፈጸመ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ማድረጋቸውን ማስረጃዎችን በመጠቀስ ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል።

ፕሬዝዳንቱ ከአንድ ወር በፊት በኃይል የታጠቁ በርካታ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን ሰብረው ከገቡ በኋላ በከፈቱት ተኩስ የተገደሉ ሲሆን የፕሬዝደንቱ ሞት በሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ አስከትሏል።

ባለፈው ሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ የሀገሪቱ ዋና አቃቤ ሕግ ቤድ ፎርድ ክላውድን "ከባድ የአስተዳደር ጥፋት" ፈጽመዋል በሚል አሰናብተው በምትካቸውም ሌላ አቃቤ ህግ ሾመው ነበር።

ሆኖም ማክሰኞ ተሻሩ የተባሉት አቃቤ ህግ ግድያውን ለሚመረምሩት ዳኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በጉዳዩ ላይ ባላቸው "አጠራጣሪ" ተሳትፎ ክስ እንዲመሰርትባቸው ጠይቀዋል።

ምንጮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓቃቤ ሕግን የማባረር ስልጣን እንደሌላቸው ይናገራሉ።

በሌላ በኩል የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስትር አቃቤ ህግ ክላውድ ላይ የሚደረሰውን በርካታ ማስፈራሪያ ተከትሎ ተጨማሪ የፖሊስ ጥበቃ እንዲመደቡላቸው አዟል።

አቃቤ ሕግ ከስልክ ኦፕሬተር የተገኙ መረጃዎችን መሰረት አድርገው እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድያውን እቅድ በማውጣት ከተከሰሱት ግለሰብ ጋር ፕሬዝዳንት ሞሴ ከተገደሉ ብዙም ሳይቆይ ሁለት ጊዜ ተደዋውለዋል።

ጠቅላይ ሚንሰትሩ የሚቀርብባቸውን ክስ ባይቀበሉም ከግድያው ምርመራ ጋር በተያያዘ ከሀገር እንዳይወጡ እግድ ተጥሎባቸዋል።

ጠቅላይ ሚንሰትሩ ከዚህ ቀደም ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን፤ ዋና ተጠርጣሪ ባይዲዮን እንደሚያውቁት እና ወንጀሉን ፈጽሟል ብለው እንደማያምኑ ተናግረው ነበር።

ፖሊስ በአሁኑ ወቅት ከፕሬዝደንቱ ግድያ ጋር በተያያዘ 44 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ጡረታ የወጡ 18 የኮሎምፒያ ጦር አባላት ይገኙበታል።