የ13 ወራት ባለፀጋዋ ኢትዮጵያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በከፍተኛ የዋጋ ግሸበት በርካታ የከተማ ነዋሪዎች እሮሮ እያሰሙ ባሉበት ሁኔታ እንዲሁም በትግራይና አካባቢው በርካቶች በረሃብ አፋፍ ባሉበት ሁኔታ የዘንድሮው አዲስ ዓመት ተከብሯል።
በርካታ ኢትዮጵያውያንም ያለቻቸውን ሸማምተው ድግስ ደግሰው ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድና ከጎረቤቶቻቸው ጋር አክብረውታል። ለየት ያለ የቀን አቆጣጠር፣ ታሪክና ባህላዊ እሴቶች ስላሏት ኢትዮጵያ በጥቂቱ ሲል የቢቢሲ እንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት የሚከተለውን ለዓለም አቅርቧል።
የ13 ወራት ባለፀጋ
የኢትዮጵያ አቆጣጠር 13 ወራት ስላሉት ብቻ አይደለም ከምዕራባውያን አቆጣጠር ለየት የሚለው፤ በተጨማሪ ሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ልዩነትም አለው። በዚህም ቅዳሜ ዕለት መስከረም አንድ ብላ ኢትዮጵያ አዲስ ዓመቷን ጀምራለች።
የልዩነቱም መነሻ ኢትዮጵያ የእየሱስን ክርስቶስ ልደት በተለየ መንገድ ስለምታሰላው ነው። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስሌቷን ክክርስቶስ ልደት በኋላ በ500 ዓመተ ምህረት ብታሻሽልም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን በዚያው ቀጥላለች።
በምዕራባውያኑ አቆጣጠርም አዲሱ የኢትዮጵያ ዓመት መስከረም 11 ወይ 12 በፀደይ መጀመሪያ ወቅት ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የምዕራባውያኑን የቀን አቆጣጠር ከሚከተሉ ልጆች በተቃራኒ የኢትዮጵያ ህፃናት በየወሩ ስንት ቀናት እንዳሏቸው ለማስታወስ ግጥሞችን መማር ብዙም አያስፈልጋቸውም።
ኢትዮጵያ ቀናቶቿና ወራቶቿ የተከፋፈሉበት መንገድ ቀላል ነው። አስራ ሁለቱ ወራት በ30 ቀናት የተከፋፈሉ ሲሆን የመጨረሻዋ ወር አምስት ወይም ስድስት ቀናት አሏት።
በቀኑ ውስጥ ያለው የጊዜ አቆጣጠር ይለያል። ቀኑ ከጥዋቱ 12 ሰዓት የሚጀምር ሲሆን እኩለ ቀን ላይ እኩለ ሌሊት ላይ ስድስት ሰዓት ይሆናል።
ስለዚህ አንድ ሰው አዲስ አበባ ላይ ቆንጆ ቡና ለመጠጣት ጠዋት 4 ሰዓት ለመገናኘት ፈልጋችሁ በምዕራባውያኑ አቆጣጠር 10 ሰዓት እንገናኝ ብትባባሉ ከሰዓት 10 ሰዓት እንደሚመጡ አትጠራጠሩ።
በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሃገር
የአውሮፓ ኃያላን አገራት የአፍሪካ አህጉርን ሲቀራመቱ ጣልያንም ኢትዮጵያን በአውሮፓውያኑ 1895 ለመውረር ሞክራ ነበር ነገር ግን አሳፋሪ ሽንፈት ገጠማት።
ሆኖም አንድ ጣሊያናዊ የመርከብ ኩባንያ የአሰብን የቀይ ባሕር ወደብ ከገዛ በኋላ ጣሊያን ጎረቤቷን ኤርትራን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ችላለች።
በአውሮፓውያኑ 1889 የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ዮሐንስ ሞትን ተከትሎ በነበረው ግራ መጋባት ጣሊያን የባሕር ዳርቻዎችንና ሌሎችንም ስፍራዎች እንዲቆጣጠር መንገድ ከፈተ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ የበለጠ ለመግፋት ስትሞክር በአድዋ ጦርነት ተሸነፈች። የጣሊያን አራት ክፍለ ጦር ወታደሮች በሰዓታት ውስጥ በአፄ ምኒልክ የካቲት 23 ቀን 1888 ድል ተነሱ።
ጣሊያን በወቅቱም የኢትዮጵያን ነፃነት እውቅና በመስጠት ውል ለመፈረም ተገደደች። ሆኖም ከአሥርት ዓመታት በኋላ የፋሺስት መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒ ይህንን ውል ጥሶ በመግባት አገሪቱን ለአምስት ዓመታት ተቆጣጠረ።
በወቅቱ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያ ጣልያንን ድል ማድረጓን ምክንያት በማድረግ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲፈጠር ገፍተዋል። የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫው አዲስ አበባ ነው።
"ሁሉም አፍሪካውያን ነፃ እስካልሆኑ ድረስ ነፃነታችን ትርጉም የለሽ ነው" በማለትም አፄ ኃይለ ሥላሴ በርካታ የአፍሪካ አገራት በአውሮፓ ቁጥጥር ስር ባሉበትና በአውሮፓውያኑ 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ ተናገሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ 1962 በአፍሪካ ዙሪያ እንዲዘዋወር ያስቻላቸውን የደቡብ አፍሪካውን ኔልሰን ማንዴላን ፓስፖርት መስጠትን ጨምሮ በርካታ የቀኝ ግዛትን ትግል የሚመሩትን አመራሮች ለስልጠና ጋበዙ።
ማንዴላ በፃፉት መፅሃፍም ላይ ኢትዮጵያ በልባቸው ስላላት የተለየ ልዩ ቦታ ያሰፈሩ ሲሆን "አፍሪካዊ ያደረገኝን አመጣጤን ወደ ኋላ ተመልሶ የማየትና የራሴንም ታሪክ ከስር መሰረት የማወቅ ስሜት ተሰማኝ" በማለት አስፍረዋል።
ራስ ተፈሪያን አፄ ኃይለ ሥላሴን እንደ አምላክ ያዩዋቸዋል
ወደ አፍሪካ መመለስ የሚለውን እንቅስቃሴ በዋነኝነት ሲመራ የነበረው የጥቁሮች መብት ታጋይ ማርከስ ጋርቬይ በአውሮፓውያኑ 1920 ላይ "ነፃነት የመውጫ ቀን ቀርቧልና ወደ አፍሪካ ተመልከቱ ጥቁር ንጉሥም ይነግሳል" ብሎ ነበር።
ከአሥር ዓመት በኋላ የ38 ዓመቱ ራስ ተፈሪ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተብለው ሲነግሱ በጃማይካ ብዙዎች ይህንን ትንቢቱ እውን ሆኖ እንደሆነ አዩት የራስታፋሪያን እንቅስቃሴም ተወለደ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሬጌው ኮከብ ቦብ ማርሌይ የራስታን መልዕክት በማሰራጨት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። 'ዋር' የሚለው የእሱ ዘፈን ግጥም ንጉሠ ነገሥቱ በአውሮፓውያኑ 1963 ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በዓለም ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ ያቀረቡበት ንግግራቸው ነው።
"አንድ ዘር የበላይ ሆኖ ሌላኛው የበታች የሆነበት ፍልስፍና በመጨረሻ እና በቋሚነት እስሰኪያከትም ድረስ … እስከዚያ ቀን ድረስ የአፍሪካ አህጉር ሰላምን አያውቅም" ይላል የእሳቸው ንግግር እንዲሁም የቦብ ማርሌይ የዘፈን ግጥም።
በታይም መጽሔት የ20ኛው ክፍለ ዘመን አልበም ተብሎ የተሰየመው የማርሊ 'ኤክሰዶች' አልበም ከአትላንቲክ ውቅያኖስ የባሪያ ንግድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጋዛቸውንና ወደ አፍሪካ መመለስን የራስ ተፈሪያን ፅንሰ ሃሳብ ያንፀባርቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 225 ኪ.ሜ በሆነችው በሻሸመኔ ከተማ መመለስ ለሚፈልጉ ጥቁር ህዝቦች በአፄ ኃይለ ሥላሴ በተሰጠ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ አነስ ያሉ የራስታፋሪያን ማኅበረሰብ ይኖራሉ።
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ የሆኑት አፄ ኃይለ ሥላሴ የራስታ አማኝ አይደሉም ነገር ግን የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮች የይሁዳ አንበሳ ናቸው በማለት እንደ አምላክ ያዩዋቸዋል።
በራስ ተፈሪያንም ዘንድ ሆነ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው የይሁዳ አንበሳ የዘር ሐረግ ማጣቀሻው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ንጉሥ ሰለሞን ነው።
የፅዮን ታቦት መገኛ
ለብዙ ኢትዮጵያውያን አምላክ ለሙሴ ሰጥቷቸው የነበሩት አስርቱ ትዕዛዛት ያረፉበት ጽላት አክሱም ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአክሱም ፅዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ማንም ሊያየው በማይፈቀድበት ቦታ ላይ ታቦቱ ጥብቅ ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል ትላለች።
አመጣጡም በታሪክ ፀሐፊዎች ክርክር የሚደረግበት ቢሆንም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን ተቀባይነት ያለው ከንግሥት ሳባ ጋር በተያያዘ ነው።
በርካቶችም በአውሮፓውያኑ 950 ዘመን ንግሥት ሳባ ስለ ንጉሥ ሰለሞን ጥበብ ለመረዳት ከአክሱም ወደ እየሩሳሌም መሄዷን ያምናሉ።
የጉዞዋና ንጉሡን የማማለሏ ታሪክ የነገሥታትን ታሪክ በሚዘክረውና በ14ኛው ክፍለ ዘመን በግዕዝ በተፃፈው ክብረ ነገሥት ላይ ሰፍሯል።
ንግሥተ ሳባ ወይም ማክዳ ምኒልክ የተባለ ወንድ ልጅ እንደወለደች እና ከዓመታት በኋላ አባቱን ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም እንዴት እንደሄደ ይተርካል።
ከተወሰኑ እስራኤላውያን ጭፍሮች ጋር የላከው ሲሆን አንደኛው አጃቢም የፅዮንን ታቦቱን በሐሰተኛ በመተካት ዋናውን ሰርቆ ወሰደ።
ምኒልክ የታቦቱን ነገር ሲረዳም የአምላክ ሥራ ነው በሚል በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቆይ ተስማማ። ለበርካታ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችም የተቀደሰ ሲሆን አሁንም ህይወታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው።
በኢትዮጵያ ሰሜናዊ የትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ተከትሎ ከኤርትራ የመጡ ወታደሮች አሰቃቂ ጭፍጨፋ ካካሄዱ በኋላ የአክሱም ፅዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ለመዝረፍ ሲሞክሩ ሕዝብ ያሳየው ፅናት ባለፈው ዓመት በግልጽ ታይቷል።
በከተማው ውስጥ ያለ አንድ የመንግሠት ሰራተኛ ለቢቢሲ እንደተናገረው ወጣቶች ታቦቱን ለመጠበቅ ወደ ስፍራው ሮጡ "ሁሉም ወንድና ሴት ተዋግቷቸዋል፣ ጠመንጃ ተኩሰው ጥቂቶቹን ገድለዋል፣ እኛ ግን ቅርሳችንን መጠበቅ በመቻላችን ደስተኞች ነን" ብሏል።
ከአረቢያ ውጭ የመጀመሪያ ሙስሊሞች መኖሪያ
ነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮቻቸው በ7 ኛው ክፍለ ዘመን በአሁኗ ሳዑዲ አረቢያ፣ መካ መሳደድ ሲያጋጥማቸው "ወደ አቢሲኒያ ብትሄዱ ግፍን የማይታገስ ንጉሥ ታገኛላችሁ" አሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ይህ ነብዩ ገና ስብከት በጀመሩበት ወቅት ነበር፣ ይህም በከተማው ሙስሊም ባልሆኑ ገዥዎች እንደ ማስፈራሪያ ተደርገው ይታዩበት ነበር።
አነስ ያለ ቡድንም ምክራቸውን ተቀብሎ ወደ አክሱም ግዛት አመራ። በዚያን ጊዜ የነበረው የአክሱም ግዛት የዛሬዋን ኢትዮጵያ እና ኤርትራን የሚሸፍን ሲሆን እንደተባለው በክርስቲያን ንጉሥ አርማህ አቀባበል ተደርጎላቸው ሐይማኖታቸውንም እንዲከተሉ ተፈቀደላቸው።
በአሁኑ ጊዜ ትግራይ በምትባለው የነጋሽ መንደር እነዚህ ስደተኞች በአፍሪካ አንጋፋ መስጊድ የገነቡበትና የሰፈሩበት ነው። ባለፈው ዓመት በትግራይ በተደረገው ውጊያ የአል ነጋሺ መስጊድ በከባድ መሳሪያ ተደብድቧል።
የአካባቢው ሙስሊሞችም 15 የነቢዩ ደቀ መዛሙርትም በነጋሽ ተቀብረዋል ብለው ያምናሉ።
በእስልምና ታሪክ ውስጥ ይህ ወደ አክሱም የሚደረግ ጉዞ የመጀመሪያው ሂጅራ ወይም ፍልሰት በመባል ይታወቃል።
ዛሬ ከ115 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ካላት ኢትዮጵያ 34 በመቶ የሚሆኑት የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው።












