በአፍሪካ ወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣ እያንሰራራ ይሆን?

የጊኒ ወታደሮች በመዲናዋ ኮናክሪ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የጊኒ ወታደሮች በመዲናዋ ኮናክሪ

በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ቅንበር ነፃ መውጣታቸውን ተከትሎ ባሉት አስርት ዓመታት መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ የተለመደ ክስተት ነበር።

ከሳምንት በፊት ፕሬዚዳንቷ አልፋ ኮንዴን በኃይል ከሥልጣን የተገረሰሱባት ጊኒ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባት የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ነው።

አጎራባቿ ማሊም አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጦር ሠራዊቱ በአገሪቱ መንግሥት ውስጥ ሁለት ጊዜ ጣልቃ ገብቶ ነገሮችን አስተካክላለሁ ያለ ሲሆን የመጨረሻው የተከሰተው በግንቦት ወር ውስጥ ነው።

በኒጀርም በመጋቢት ወር የፕሬዚዳንቷ በዓለ ሲመት ቀናት ሲቀሩት መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮ ተሰናክሏል።

ይህም ሁኔታ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶች በአህጉሪቱ ላይ የተለመዱ ክስተቶች ይሆኑ ወይ? የሚል ጥያቄን አጭሯል።

መፈንቅለ መንግሥት የሚባለው መቼ ነው?

ለመፈንቅለ መንግሥት ትርጓሜ ጥቅም ላይ ሲውል የሚታየው በጦሩም ይሁን በሲቪል ባለሥልጣናት አመራሮችን በኃይልና በሕገ ወጥ መንገድ ለማውረድ የሚደረግ ግልፅ ሙከራ ነው።

ዮናታን ፓውል እና ክላይተን ታይን በተባሉ ሁለት የአሜሪካ ተመራማሪዎች ጥናት መሠረት ከአውሮፓውያኑ 1950 ጀምሮ በአፍሪካ ውስጥ ከ200 በላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተደርገዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ተሳክተዋል፤ ለዚህም የመንግሥት ግልበጣዎቹ ተሳኩ ለማለት ከሰባት ቀናት በላይ መቆየት አለባቸው።

የምዕራብ አፍሪካዊቷ ቡርኪና ፋሶ የተሳኩ ሰባት መፈንቅለ መንግሥቶች የተካሄዱባት ሲሆን አንዱ ብቻ ከሽፏል።

አንዳንድ ጊዜ በእንደዚህ ዓይነት መንገድ በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ሥራ ላይ ጣልቃ በመግባት የሚሳተፉ አካላት ድርጊቱን መፈንቅለ መንግሥት መሆኑን ይክዳሉ።

በአውሮፓውያኑ 2017 በዚምባብዌ ውስጥ ወታደራዊ ኃይል ስልጣኑን በኃይል መቆጣጠሩን ተከትሎ ለ37 ዓመታት የዘለቀው የሮበርት ሙጋቤ አገዛዝ እንዲያከትም አድርጎታል።

በዚህ ድርጊት ውስጥ መሪ ከሆኑት አንዱ አንዱ ሜጀር ጄኔራል ሲቡሲሶ ሞዮ በወቅቱ በቴሌቪዥን ብቅ ብለው በሥልጣን የላይ ያለው መንግሥት በኃይል ተገርስሷል የሚለውን በግልጽ አስተባብለዋል።

ባለፈው ዓመት በሚያዝያ ወር የቻድ መሪ ኢድሪስ ዴቢ መሞታቸውን ተከትሎ ጦሩ ልጃቸውን የወታደራዊው ምክር ቤት የሽግግር ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አድርጎ ሾሟል። ተቃዋሚዎቻቸውም ይህንን ሁኔታ "ሥርወ መንግሥታዊ መፈንቅለ መንግሥት" ሲሉ ጠርተውታል።

"የመፈንቅለ መንግሥት መሪዎች አብዛኛውን ጊዜ መፈንቅለ መንግሥት አላደረግንም ሲሉ ይክዳሉ ይህም ሕጋዊ ለመምሰል ከመሞከር ጋር ተያይዞ ነው" ሲሉ ጆናታን ፓውል ይናገራሉ።

የዚምባብዌ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዚምባብዌ ወታደሮች

በአፍሪካ ውስጥ የሚደረጉ መፈንቅለ መንግሥቶች ቁጥር ቀንሶ ይሆን?

በአውሮፓውያኑ 1960 እና በ2000 መካከል ባሉት አራት አስርት ዓመታት ውስጥ በአጠቃላይ በአፍሪካ ውስጥ የሚደረጉ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች በሚያስደንቅ ሁኔታ በዓመት በአማካኝ አራት ነበር።

ከነፃነት በኋላ በነበሩት ዓመታት ውስጥ የአፍሪካ አገራት ካጋጠሟቸው አለመረጋጋት አንፃር ይህ የሚገርም እንዳልሆነ ጆናታን ፖል ያስረዳሉ።

"የአፍሪካ አገራት ለመፈንቅለ መንግሥት ምቹ የሆኑ እንደ ድህነት እና ደካማ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ ። በአንድ አገር አንድ መፈንቅለ መንግሥት ከተከናወነ ከዚያ በኋላ ሌሎች መፈንቅለ መንግሥቶች ሊካሄዱ እንደሚችሉ ምልክት ነው" ይላሉ።

ከአውሮፓውያኑ 2000 በኋለ እስከ 2019 ባሉት ሁለት አስርት ዓመታት በአህጉሪቱ ውስጥ የሚከሰተው የመፈንቅለ መንግሥት ቁጥር በዓመት በአማካኝ ወደ ሁለት ወርዷል። በአውሮፓውያኑ 2020 ሪፖርት የተደረገው አንድ መፈንቅለ መንግሥት ብቻ ነው።

ነገር ግን ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በዘንድሮው የተደረገው የኒጀር፣ ቻድ፣ ማሊ እና ጊኒ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከአማካኙ ቁጥር ከፍ ያለ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።የዓለም ታላላቅ ሰዎች በኢትዮጵያ የተኩስ አቁምና ድርድር እንዲደረግ ጠየቁ

ማሃማት እድሪስ ዴቢ የቻዱ ፕሬዚዳንት ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ማሃማት እድሪስ ዴቢ የቻዱ ፕሬዚዳንት ልጅ

የኩዋዙሉ ናታል ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ኑዱቡሲ ክርስቲያን አኒ እንደሚሉት ለረጅም ዓመታት በአምባገነኖች ላይ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ በአፍሪካ መፈንቅለ መንግሥት እንዲመለስ ዕድል ፈጥሯል።

"ሕዝባዊ አመፆች ሕጋዊ እና በሕዝብ የሚመሩ ቢሆንም፣ ስኬታማነቱ ብዙውን ጊዜ የሚወሰነው በወታደራዊው ኃይል ውሳኔ ነው" ይላሉ።

የትኞቹ የአፍሪካ አገራት በርካታ መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎባቸዋል?

በርካታ መፈንቅለ መንግሥቶች የተካሄዱባት አገር ሱዳን ስትሆን፤ ከተሞከሩት 15 መፈንቅለ መንግሥቶች አምስቱ የተሳኩ ነበሩ።

የቅርቡ ያጋጠመው በአውሮፓውያኑ 2019 የተደረገው ሲሆን ለወራት ያህል የተደረገውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኦማር አልበሽር የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር መሆን አክትሟል።

ኦማር አልበሽር እራሳቸው ወደ አገሪቱ የሥልጣን መንበር የመጡት በአውሮፓውያኑ 1989 በተካሄደ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ነበር።

ናይጄሪያም በተጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥት ከሚሞከርባቸው አገራት አንዷ ስትሆን ከነፃነት በኋላ በነበረው በአውሮፓውያኑ 1966 እና ጄኔራል ሳኒ አባቻ ስልጣን ከተቆጣጠሩባት አስከ 1993 ድረስ ባሉት ዓማት መካከል ስምንት መፈንቅለ መንግሥቶች ተደርገዋል።

ሆኖም በአፍሪካ ቀዳሚ የሕዝብ ቁጥር ያለባት ናይጄሪያ ከአውሮፓውያኑ 1999 ጀምሮ የስልጣን ሽግግር የሚደረገው በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ነው።

የቡሩንዲ ታሪክንም ስንመለከት በአብዛኛው በሁቱ እና በቱትሲ ማኅበረሰቦች መካከል በተፈጠረው ውጥረት ምክንያት አስራ አንድ መፈንቅለ መንግሥቶች ተደርጎባታል።

በሴራሊዮን ከአውሮፓውያኑ 1967 እስከ 1968 ባለው ጊዜ ሦስት መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደ ሲሆን፤ በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 1971 እና ከአውሮፓውያኑ 1992 እስከ 1997 ውስጥ አምስት ተጨማሪ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተካሂደውባታል።

በጋናም እንዲሁ በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ስምንት መፈንቅለ መንግሥቶች ተደርገዋል።

የመጀመሪያው በአውሮፓውያኑ 1966 የተካሄደው ሲሆን በዚህ ወቅትም ክዋሜ ንክሩማህ ከስልጣን ተወገዱ እና በቀጣዩ ዓመት በወጣት የጦር መኮንኖች ያልተሳካ ሙከራ ተደረገ።

በአጠቃላይ አፍሪካ ከማንኛውም አህጉር የበለጠ የመፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶባታል።