አል-በሽር ከ30 ዓመት በፊት በፈጸሙት መፈንቅለ መንግሥት ተከሰው ፍርድ ቤት ቀረቡ

ችሎት

የፎቶው ባለመብት, AFP

ኦማር ሐሰን አል-በሽር ከሦስት አስርታት ዓመት በፊት ወደ ስልጣን ለመጡበት መፈንቅለ መንግሥት ፍርድ ቤት ቀረቡ።

በመዲናዋ ካርቱም በሚገኘው ፍርድ ቤት የቀረቡት የ76 ዓመቱ ኦማር አል-በሽር፤ እአአ 1989 ላይ ወደ ስልጣን ባመጣቸው መፈንቅለ መንግሥት ላይ በነበራቸው ተሳትፎ ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ከሆነ የሞት ፍርድ ሊበየንባቸው ይችላል ተብሏል።

አል-በሽር ከዚህ ቀደም የሙስና ክስን ጨምሮ ከስልጣን ከመባረራቸው በፊት መንግሥታቸውን ለመቃወም በወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በደረሰው ጉዳትም ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ከአል-በሽር ጋር ከ20 በላይ የቀድሞ የአገሪቱ ባለስልጣናት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ሱዳናውያን እአአ 2018 ማገባደጃ ላይ የቀሰቀሱት ሕዝባዊ አብዮት በወራት ልዩነት የረዥም ጊዜ መሪያቸውን ከስልጣን ማባረራቸው ይታወሳል።

አል-በሽር ከስልጣን ከተነሱ በኋላ ከጦር መኮንኖች እና ከሲቪሎች የተወጣጣ ቡድን አገሪቱን በሽግግር መንግሥት እያስተዳድረ ይገኛል።

ኦማር አል-በሽር እአአ 1989 ላይ በመፈንቅለ መንግሥት ነበር ወደ ስልጣን የመጡት።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ኦማር አል-በሽር እአአ 1989 ላይ በመፈንቅለ መንግሥት ነበር ወደ ስልጣን የመጡት።

አል-በሽር በሱዳኗ ዳርፉር ግዛት በተፈጸሙ የሰብአዊ መበት ጥሰቶች፣ የዘር ማጥፋት እና የጦር ወንጀሎች በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ይፈለጋሉ።

የሱዳን የሽግግር መንግሥት ከወራት በፊት የቀድሞ መሪውን ለፍርድ ቤቱ አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

ዛሬ ከ30 ዓመታት በፊት ለተፈጸመው መፈንቅለ መንግሥት ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል የቀድሞው ምክትል ፕሬዝደንት አሊ ኦስማን ጣሃ እና ካክሪ ሃሰን ሳሌህ ይገኙበታል።

የፍርድ ቤቱ ዳኝ፤ ሁሉም ተከሳሾች መከላከያዎቻቸውን እንዲያቀርቡ እድል እንሰጣለን ማለታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የአል-በሽር ምክትሎች መካከል አንዱ የነበሩት አሊ ኦስማን ታሃ ፍርድ ቤት ቀርበው ሳለ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የአል-በሽር ምክትሎች መካከል አንዱ የነበሩት አሊ ኦስማን ታሃ ፍርድ ቤት ቀርበው ሳለ

ከአል በሽር ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ሃሺም አል-ጋሊ ተከሳሾች እየተከላከሉ ያሉት "የፖለቲካ የፍርድ ሂደትን ነው" ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

እአአ 1989 ላይ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጣውን የጠቅላይ ሚንስትር ሳዲቅ አል-ማሃዲ መንግሥትን በመፈንቅለ አል-በሽር ስልጣን መያዛቸው ይታወሳል።

አል-በሽር አሁን የቀረበባቸው ክስ ከ30 ዓመታት በፊት የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ከሌሎች ጋር አሲረዋል፣ የአገሪቱ ዋና ምክር ቤት እንዲበተን አድርገዋል እንዲሁም ዋነኛውን አየር ማረፊያ አዘግተው በሬዲዮ መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙን አውጀዋል የሚል ይገኝበታል።