አገር ጥለው የሸሹት የቀድሞው የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት ህዝቡን ይቅርታ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታሊባን የአፍጋኒስታንን መዲና ካቡልን መክበቡን ተከትሎ አገር ጥለው ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የተሰደዱት የቀድሞው የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ ህዝቡን ይቅርታ ጠየቁ።
"ካቡልን ለቅቆ መውጣት በሕይወቴ ውስጥ በጣም ከባድ ውሳኔ ነበር።" በማለት የተናገሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከዚህ በተለየ መልኩ ባለማድረጋቸውም ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
የታሊባን ታጣቂዎች ነሐሴ መጀመሪያ ላይ መዲናዋን ካቡልን መክበባቸውን ተከትሎ ነው አሽራፍ ጋኒ በድንገት ሃገር ጥለው የሸሹት።
ህዝቡን ለመተው ሃሳባቸው እንዳልነበር የተናገሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት "ብቸኛው መንገድ ነው" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም 169 ሚሊዮን ዶላር ይዘው ነው ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የተጓዙት የሚለውን "መሠረተ ቢስ" ውንጀላ በሚል በድጋሚ አስተባለዋል።
ረቡዕ ዕለት በትዊተር ላይ በተጋራ መግለጫ እንደተጠቀሰው የቀድሞው ፕሬዚዳንት በአገሪቱ ሁከት እንዳይፈጠር አገሪቱን ለቅቆ ከመውጣት ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ተናግረዋል።
"በ 1990ዎቹ የእርስ በእርስ ጦርነትና የከተማ ላይ ውጊያ ካቡል ከደረሰባት ተመሳሳይ አደጋ ላይ እንዳትወድቅ በቤተ መንግሥቴ ደህንነት የተሰጠኝን ምክር በመስማት ነው የወጣሁት። ካቡልን እና ስድስት ሚሊዮን ዜጎቿን ለማዳን" በማለትም አስፍረዋል።
አፍጋኒስታንን "ዲሞክራሲያዊ ፣ የበለፀገች እና ሉዓላዊ መንግሥት" እንድትሆን ለመርዳት ለ20 ዓመታት መስራታቸውንም ጠቅሰዋል።
አክለውም "የኔ የስልጣን ምዕራፍ ከቀዳሚዎቼ ጋር ተመሳሳይ በሆነ በአሳዛኝ ሁኔታ መቋጨቱ ጥልቅ ጸጸት አሳድሮብኛል" ብለዋል።
አገሪቱን ለቀው በመውጣታቸው ከአፍጋኒስታን ፖለቲከኞች ከፍተኛ ትችትን ያስተናገዱት የ 72 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት "እኔ ከመውጣቴ በፊት የነበሩትን ክስተቶች" በተመለከተ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በፌስ ቡክ በቀጥታ በተላለፈ መልዕክታቸው አሽራፍ በደህንነት ቡድናቸው ከአገር ለመውጣት እንደተገደዱ ተናግረዋል። ምክንያቱንም ሲያስረዱ "ተይዤ የመገደሌ ሁኔታ ከፍተኛ ነበር" ብለዋል።
የታሊባን ታጣቂዎች በካቡል ወደሚገኘው የፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ካቀኑ በኋላ "ከክፍል ወደ ክፍል እየተዟዟሩ እኔን መፈለግ ጀመሩ" በማለትም አስረድተዋል።
አገሪቱን ለቅቀው ሲወጡ ከፍተኛ ገንዘብ ወስደዋል የሚለውን ክስ በተመለከተም "ሸበጥ ጫማዬን እንኳ አውልቄ ደህና ጫማ እንዳደርግ አልተፈቀደልኝም" ብለዋል።












