ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአፍጋኒስታን ስደተኞችን የትኞቹ አገራት ሊቀበሉ ተስማሙ?
ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠሩን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአገሪቱ ሸሽተው ለመውጣት ሲሽቀዳደሙ ቆይተዋል።
አፍጋኒስታን በታሊባን ቁጥጥር ስር ከወደቀች በኋላ 2.2 ሚሊየን ሰዎች ወደ ጎረቤት አገራት የሸሹ ሲሆን 3.5 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በአገሪቱ ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በድንበር አካባቢዎች ላይ ይገኛሉ።
ታሊባን የአፍጋኒስታንን አብዛኛ የድንበር አካባቢዎች የተቆጣጠረ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም አፍጋኒስታናውያን አገሪቱን ለቅቀው እንዳይሄዱ ቁጥጥር ማድረግ ጀምሯል። አንዳንድ ምንጮች እንደገለጹት ነጋዴዎችና ፍቃድ ያላቸው ተጓዦች ብቻ ናቸው እንዲወጡ የሚፈቀድላቸው።
''አብዛኛዎቹ አፍጋኒስታናውያን ይፋዊ መንገዶችን ተጠቅመው ከአገር መውጣት አይችሉም'' ብለዋል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ኮሚሽነር ቃል አቀባይ።
የአፍጋኒስታን ጎረቤት የሆኑት ፓኪስታን እና ኢራን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አፍጋኒስታናውያንን ያስተናገዱ አገራት ሆነዋል።
ዩኤንኤችሲአር እንደሚለው 1.5 ሚሊየን አፍጋኒስታናውያን ፓኪስታን ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ኢራን ደግሞ 780 ሺህ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞችን ተቀብላለች።
ከዚህ በተጨማሪ ጀርመን 180 ሺህ ሰዎችን መቀበሏን ገልጻለች። ሌላኛው በርካታ አፍጋንስታናውያንን የተቀበለች አገር ደግሞ ቱርክ ስትሆን እስካሁን 130 ሺህ ሰዎችን ተቀብላለች።
እነዚህ አገራት ከተቀበሏቸው አፍጋኒስታናውያን በተጨማሪ በቱርክ 125 ሺህ፣ በጀርመን 33 ሺህ እና ግሪክ ውስጥ ደግሞ 20 ሺህ አፍጋኒስታናውያን በእነዚህ አገራት ጥገኝነት ጠይቀው ፈቃድ እየጠበቁ ነው።
ሌሎች አገራት በጉዳዩ ለመርዳት ምን እያደረጉ ነው?
ኢራን
ኢራን ከአፍጋኒስታን ጋር በሚያዋስናት የድንበር አካባቢ የድንገተኛ መጠለያ ቤቶችን እየሰራች ነው። ነገር ግን አንዳንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚሉት በአፍጋኒስታን ያለው ሁኔታ ሲስተካከል እነዚህ ስደተኞች ወደመጡበት እንዲመለሱ ይደረጋል።
የተባበሩት መንግስታት እንደሚለው ኢራን በአጠቃላይ እስከ 3.5 ሚሊየን የሚደርሱ አፍጋኒስታናውያንን እያስተናገደች ነው።
ፓኪስታን
ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ክሃን ሰኔ ወር ላይ ታሊባን አፍጋኒስታንን የሚቆጣጠር ከሆነ የድንበር አዋሳኝ ቦታዎችን እንደሚዘጉ ተናግረው ነበር። ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋናውያን እስካሁን በድንበር በኩል የገቡ ሲሆን ቢያንስ አንድ የድንበር መሻገሪያ ክፍት እንደሆነ ተለግጿል።
ታጂኪስታን
ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ ምን ያክል አፍጋኒስታናውያን በአገሪቱ እንደሚገኙ በግልጽ ባይታወቅም ቢያንስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚገኙ ይገመታል። ባለፈው ወር ታጂኪስታን እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ የአፍጋን ስደተኞችን እንደምትቀበል ገልጻ ነበር።
ኡዝቤኪስታን
እስከ 1 ሺህ 500 የሚደርሱ አፍጋኒስታናውያን ወደ ኡዝቤኪስታን ድንበር እንደተሻገሩ የተገለጸ ሲሆን ስደተኞቹም ጊዜያዊ መጠለያዎችንም ሰርተዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም
ዩኬ ቢያንስ እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ የአፍጋኒስታን ስደተኞችን እንደምትቀበል ገልጻለች። የእንግሊዝ መንግሥት እንዳስታወቀው በመጀመሪያው ዓመት እስከ 5 ሺህ የሚደርሱ አፍጋኒስታናውያን ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ለማኖር ታቅዷል። በዚህም መሠረት ህጻናትና ሴቶች እንዲሁም በሃይማኖት እና በማንነታቸው ጫና ሊደርስባቸው የሚችሉ ሰዎች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ተብሏል።
አሜሪካ
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አፍጋኒስታን ውስጥ ባለው ሁኔታ ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰዎች እና ተፈናቃዮች የሚውል 500 ሚሊየን ዶላር ፈቅደዋል። ነገር ግን አሜሪካ ምን ያክል ስደተኞችን እንደምትቀበል በግልጽ አላስታወቀችም።
ካናዳ
ካናዳ ታሊባን አፍጋኒስታናውያን ላይ የሚያደርሰውን ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን እንደምትቀበል ያስታወቀች ሲሆን የመንግሥት ሰራተኞችና ሴት መሪዎችንም እንደምትቀበል ገልጻለች።
ኡጋንዳ
ኡጋንዳ እስካሁን 2 ሺህ አፍጋኒእስታናውያን ስደተኞችን ለመቀበል ተስማምታለች። ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ እስካሁን ከየትኛውም የአፍሪካ አገር ከፍተኛውን የስደተኞች ቁጥር የምታስተናግድ ሲሆን ከዓለም ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የአውሮፓ ሕብረት
ጀርመን ከዚህ በኋላ አፍጋኒስታናውያንን እንደምትቀበል ብትገልጽም ምን ያክል እንደሆነ ግን አልገለጸችም። ቻንሰለር አንጌላ መርክል በአውሮፓውያኑ 2015 በርካታ ስደተኞችን በመቀበላቸው ከፍተኛ ትችት አስተናግደው የነበረ ሲሆን በአፍጋኒስታን ሁኔታ ግን ስደተኞች በጎረቤት አገራት ድጋፍ እንዲያገኙ እያደረጉ ነው።
ፈረንሳይ ደግሞ በፕሬዝዳንቷ ኢማኑኤል ማክሮን በኩል ባስተላለፈችው መልእክት አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የስደተኞችን ቁጥር እንዳያስጨንቃቸው እራሳቸውን እንዲከላከሉ አስጠንቅቃለች።
''ፈረንሳይ እራሷን ከማንኛውም አይነት አደጋ ትከላከላለች። የአውሮፓ አገራት ብቻ የዚህን ቀውስ መዘዝ መጋፈጥ የለባቸውም'' ብለዋል።
ኦስትሪያ ምንም አይነት የአፍጋኒስታን ስደተኞችን እንደማትቀበል አስታውቃለች። ስዊዘርላንድ በበኩሏ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአፍጋኒስታን ስደተⶉችን እንደማትቀበል የገለጸች ሲሆን ቱርክ ደግሞ ከፓኪስታን ጋር በመተባበር ስደተኞችን ለመርዳት እንደምትሞክር ገልጻለች።
የቱርክ መንግስት ከኢራን ጋር በመተባበር ስደተኞችን እዛው ለማስቀረት ግንብ ለመገንባት ስራዎችን አጠናክሮ እያስቀጠለ እንደሆነ ገልጿል።
ሰሜን ሜቄዶኒያ እና አልባኒያ ደግሞ ከአሜሪካ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት እያንዳንዳቸው 450 እና 300 ስደተኞችን ለመቀበል ተስማምተዋል።