በቻይና ጥንዶች እስከ 3 ልጆች እንዲወልዱ ተፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና የሶስት ልጆች ፓሊሲ በተሰኘ ማዕቀፍ ባለትዳሮች እስከ ሦስት ልጆች እንዲኖራቸውው በመፍቀድ የወሊድ ምጣኔንን የተመለከተውን የቀድሞ ደንቧን አሻሽላለች።
አዲሱ ደንብ ባለፈው አርብ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሕግ አውጭዎች በብሔራዊ ህዝባዊ ኮንግረስ ጉባኤ ላይ ከጸደቁ በርካታ ህጎች አንዱ ነው። እናም ይህንን ደንብ ዘግይቶ የተሻሻለ ሲሉ ነበር የሆንግ ኮንግ ሚዲያዎች የዘገቡት።
የሶስት ልጆች ፖሊሲ ምንድነው?
ቻይና መሰረታዊ የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ባለትዳሮች እስከ ሦስት ልጆች እንዲወልዱ እንደምትፈቅድ በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነበር ያሳወቀችው።
ታዲያ አርብ'ለት የግንቦቱ ውሳኔ የወሊድ ምጣኔን ከፍ ለማድረግ እና ልጅን ለማሳደግ ያለውን "ሸክሙን ለመቀነስ" በማለም መደበኛ በሆነው የህግ ስርዓት መጽደቁን ዢንዋ የዜና ወኪል ዘግቧል።
አዲሱ ህግ "የማህበራዊ ዋስትና ክፍያ" መሰረዝንና ባለትዳሮች ከገደብ በላይ ለሚወለዱት ልጅ ይጣል የነበረ የገንዘብ ቅጣትን ማንሳት ጨምሮ የአከባቢ መስተዳድሮች የወላጅነት ዕረፍትን እንዲደጡ ማበረታታት ፣ የሴቶች የቅጥር መብቶችን ማሳደግ እና የሕፃናት እንክብካቤ መሠረተ ልማት ማሻሻልን ያካትታል።
በቻይና በቅርብ በተከናወነ የሕዝብ ቆጠራ መረጃዎች መሰረት በሀገሪቱ የወሊድ ምጣኔ ላይ ከፍተኛ ማሽቆልቆልን መታየቱ ተዘግቧል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ 2016 ሀገሪቱ ጥንዶች አንድ ልጅ ብቻ እንዲያፈሩ የሚያስገድደውንና ለአስርተ ዓመታት የቆየውን የአንድ ልጅ ፖሊስን በመሻር የሁለት ልጆች ፖሊስን ብታጸድቅም የወሊድ ምጣኔውን ዘላቂ በሆነ መንገድ ሊጨምረው አልቻለም።
በከተሞች ህጻናት ለማሳደግ ያለው ከፍተኛ ወጪ ጥንዶች ልጆችን ከማፍራት እንዲቆጠቡ ምክንያት እንደሆነም ነው የተጠቀሰው።












