የአፍጋን ቀውስ፡ ሩሲያ በአዲሱ የታሊባን አገዛዝ ዘመን ምን አቀደች?

በዚህ ሳምንት የአሜሪካ እና የአውሮፓ መንግሥታት ዜጎቻቸውንና ሠራተኞቻቸውን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ሲዋከቡ፤ የታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠር ብዙም ካላስበረገጋቸው ጥቂት አገራት መካከል ሩሲያ አንዷ ናት።

የሩሲያ ዲፕሎማቶች ካቡል የገቡትን የታሊባን ሰዎች "ሠላማዊ ናቸው" ሲሉ መዲናዋ ቀድሞ ከነበረው ጊዜ አሁን ሠላም እንደሆነች ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን አርብ ዕለት የታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠር እውን እንደነበርና ከእነርሱ ጋር አብረው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በርካታ ሩሲያውያን በ1980ዎቹ (እአአ) የነበረውን የአፍጋኒስታን የኮሚዩኒስት መንግሥት በመደገፍ በአገሪቱ ውስጥ ለዘጠኝ ዓመታት የተሳተፉበትን ጦርነት ያስታውሱታል።

የታሊባንን ልብ ያሞቀው ቃል

ከሌሎች የውጭ አገራት ኤምባሲዎች በተለየ ሩሲያ በአፍጋኒስታን ያላት ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ክፍት እንደሚሆን አስታውቃለች። ይህም ለአዲሱ አስተዳደር ልብ የሚያሞቅ ውሳኔ ሆኗል።

አምባሳደር ዲሚትሪ ዢርኖቭ ታሊባኖች አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠሩ በኋላ በ48 ሰዓታት ውስጥ ከታሊባን ተወካይ ጋር ተገናኝተዋል።

አምባሳደሩ በወቅቱ በታሊባን የተወሰደ አንዳችም "የአጸፋ እርምጃም ወይም ጥቃትን የሚያሳይ ምልክት አላየሁም" ብለዋል።

የሞስኮ የተባበሩት መንግሥታት ተወካይ ቫሲሊይ ንቤንዚያ ስለብሔራዊ እርቅ የወደፊት ተስፋ ተናግረው፤ ሕግና መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ለዓመታት የዘለቀውን ደም መፋሰስ ማቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፕሬዚደንት ፑቲን የአፍጋኒስታን ልዩ መልዕክተኛ ዛሚር ካቡሎቭ በበኩላቸው ቀድሞ ከነበረውና ከተሰደዱት የፕሬዚደንት አሽራፍ ጋኒ 'አሻንጉሊት' መንግሥት ጋር ለመደራደር ታሊባኖች ቀላል ነበሩ ብለዋል።

ሞስኮ በስደት ላይ ካሉት ፕሬዚደንት ጋኒ ጋር የነበራት የግንኙነት ጊዜ ትንሽ ነበር፤ ይሁን እንጂ በዚህ ሳምንት ዲፕሎማቶቿ ፕሬዚደንቱ በአራት መኪኖችና በሄሊኮፕተር ሙሉ ጥሬ ገንዘብ ጭነው ነው የሄዱት ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

ፕሬዚደንት ጋኒም የቀረበባቸውን ውንጀላ ሐሰት ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

እየተሻሻለ የመጣው የሩሲያ ግንኙነት

ሩሲያ ታሊባኖችን የአፍጋኒስታን መሪዎች እንደሆኑ ለመናገር አልተጣደፈችም፤ ነገር ግን ንግግሯን እያለሳለሰች ነው። የአገሪቷ የዜና ወኪል ታስ በዚህ ሳምንት ስለታሊባን ሲዘግብ 'ሽብርተኛ' የሚለውን ስያሜ 'አክራሪ' በሚለው ተክቶታል።

ምንም እንኳን ታሊባን ከ2003 ጀምሮ በሩሲያ የሽብር ቡድንና ከታገዱ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ ቢኖርም፣ ሞስኮ ለተወሰነ ጊዜ ከታሊባን ጋር ግንኙነት ነበራት።

የቡድኑ ተወካይ እአአ ከ2018 ጀምሮ ለንግግር ወደ ሞስኮ ያቀኑ ነበር።

በምዕራባውያን የሚደገፈው የቀድሞው የአፍጋኒስታን መንግሥት "ታሊባንን በግልፅ ይደግፋል። ለሦስት ዓመታት በተካሄደው የሞስኮ ውይይት ላይ መንግሥትን አግልሏል" ሲል የሩሲያን ፕሬዚደንት መልዕክተኛ ከስሶ ነበር።

መልዕክተኛው ካቡሎቭ ግን ክሱን አስተባብለው "ምስጋና ቢስነት ነው" ብለዋል።

ይሁን እንጂ እስከ 2015 ድረስ እስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) ጂሃዲስቶችን ለመዋጋት የሩሲያ ፍላጎት ከታሊባን ጋር ተገጣጥሞ እንደነበር ካብሎቭ ተናግረዋል።

ይህ ለዋሽንግተንም የተደበቀ አልነበረም።

በ2017 ነሐሴ ወር ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ሩሲያ ለታሊባን የጦር መሣሪያዎችን ታቀርባለች ሲሉ ከሰው ነበር። ይህንን ግን ሞስኮ አልተቀበለችውም። "ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት የሚከብድ" ስትል ነበር ክሱን የገለጸችው።

የሞስኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "የአሜሪካ ባልደረቦቻችንን ማስረጃ እንዲያቀርቡ ጠይቀናቸው ነበር ነገር ግን የቀረበ ነገር የለም" ሲሉ ለታሊባን ያደረጉት ምንም ድጋፍ እንደሌለ አስረድተዋል።

በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ የሩሲያ መልዕከተኛ የሆኑት ካቡሎቭ በዶሃ በተደረገው ድርድር ካቡል "እንቅፋት ሆናብናለች" ሲሉ ታሊባኖች ደግሞ ለስምምነቱ የሚጠበቅባቸውን 'እንከን በማይወጣለት መልኩ' አሟልተዋል ሲሉ በማሞገሳቸው የአፍጋን መንግሥትን አስቆጥተው ነበር።

ቀጠናዊ ደንነት

ሞስኮ ምንም እንኳን ከታሊባን ጋር የቅርብ ግንኙነት ቢኖራትም ነገሮችን በጥንቃቄ እያጤነች፣ ሁኔታዎችን እያየች ያለው ቡድኑን ገና ከሽብር ቡድን ዝርዝሯ ውስጥ ሳታስወግድ ነው።

ፕሬዚደንት ፑቲን ታሊባኖችን ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ ቃል ሲገቡ መልካም ነገር እንደሚሰሩ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

"በአጎራባች አገሮች ሽብርተኞች ሰርገው እንዳይገቡ አለመፍቀድ ወሳኝ ጉዳይ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

የሩሲያን ፖሊሲን የሚቀርፁት ቁልፍ ምክንያቶችም ቀጠናዊ መረጋጋት እና በአፍጋኒስታን ያለው ሁኔታ ነው።

ሩሲያ ከማዕከላዊ እስያ ጋር የሚያገናኛት ድንበር ደኅነንትን ማስጠበቅ እንዲሁም የሽብርተኝነት መዛመት እንዲሁም የዕፅ ዝውውርን መከላከል ትፈልጋለች።

አሜሪካ ከመስከረም 11ዱ ጥቃት በኋላ ታሊባንን ኢላማ ስታደረግ እና በቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት አገራት ውስጥ ወታደራዊ ካምፖችን ስትገነባ መጀመሪያ ላይ ሩስያ ውሳኔውን ተቀብላው ነበር። ነገር ግን ግንኙነታቸው ወዲያውኑ ነበር የሻከረው።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሩሲያ በኡዝቤኪስታንና ታጃኪስታን ወታደራዊ ልምምድ አካሂዳለች። ወታደራዊ ልምምዱ የመካከለኛው እስያ አገራትን ደኅንነት የመጠበቅ ዓላማ ያለው ሲሆን፤ የተወሰኑት አገራት ከሞስኮ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ያላቸው ናቸው።

ባለፈው ወር ሩሲያ ማንም አፍጋናዊ ለቀጠናዊ ግንኙነቱ ስጋት እንደማይሆንና የአይኤስ ታጣቂዎችን መዋጋት እንደሚቀጥሉ ከታሊባን ማረጋገጫ አግኝታለች።

የሩሲያ መራሩ የጦርነት ትውስታ

ሩሲያ ወደ አፍጋኒስታን ጦሯን የመላክ ፍላጎት እንደሌላት በአፅንኦት ገልጻለች።

ይህ ለምን እንደሆነ ለማየት ግን ከባድ አይደለም። ምክንያቱም ሩሲያ በ1980ዎቹ በሶቭየት ሕብረት መጨረሻ ወቅት ደም አፋሳሽ የሆነ እና ብዙዎች 'ትርጉም አልባ' የሚሉት ጦርነት ነው።

ይህ ጦርነት በ1979 ተጀምሮ ለዘጠኝ ዓመታት ተካሂዶ 15 ሺህ የሶቭየት ወታደሮችን ሕይወት ቀጥፏል።

ጦርነቱ የሶቭየት ሶሻሊስት ሪፐብሊክ ላይ ዓለም አቀፍ ውግዘትን ያስከተለ ክስተት ነበር። በርካታ አገራት የ1980ው የሞስኮ ኦሊምፒክ ላይ አድማ መትተዋል። ይህም እየፈራረሰ በነበረው የሶቭየት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫናን አሳድሯል።

ሶቭየት ሕብረት በካቡል ባብራክ ራርማል የሚመራ መንግሥት ስታቋቁም አሜሪካ፣ ፓኪስታን፣ ቻይና፣ ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ የሶቭየት ወታደሮችንና የአፍጋን አጋሮቻቸውን ለታገሉት ሙጃሂዶች የገንዘብና የጦር ድጋፍ ሰጥተዋል።

በዚህ ጦርነት የተገደሉት በሶቭየት የተመለመሉ ታዳጊ ወታደሮች ነበሩ። ጦርነቱ የሶቭየት ባለሥልጣናት ለራሳቸው ሰዎች ምን ያህል ግድ እንደማይሰጣቸው ያመላከተ ነበር ተብሏል።

ጦርነቱ የሶቭየት ሕብረት ፍጻሜን እንዳፋጠነ በሰፊው ይታሰባል፤ ነገር ግን ጦርነቱ በ1989 የካቲት ወር ላይ 'አሳፋሪ' በተባለ የጦር ማስወጣት ተጠናቋል።

የወደፊት ስጋት

ሩሲያ ለታሊባን የሥልጣን ሽግግር ዝግጁ መሆኗን ሳታሳይ አትቀርም።

አንዳንድ ባለሙያዎች ግን ሞስኮ እንደ ሌሎቹ ሁሉ አሁንም በለውጡ ድንጋጤ እንደተዋጠች ናት ብለዋል።

የሩስያ ዘመናዊ የአፍጋኒስታን ጥናት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት አንድሪይ ስሬንኮ "ስለሞስኮ ምንም ዓይነት ስትራቴጂ ማውራት አንችልም" በማለት ሞስኮ የቀጠናውን ሁኔታ ለማስተካከል ዘግይታለች ብለዋል።

ሌሎች ደግሞ የታሊባን አስተዳደር ምን ይዞ ይመጣ ይሆን በሚል ሰግተዋል።

የሩሲያ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምክር ቤት ኃላፊ አንድሬ ኮርቱኖቭ ታሊባን አገሪቷን በሙሉ ለመቆጣጠር ይታገላል የሚል እምነት አላቸው። ይህ ደግሞ በተለይም ለሩሲያና ጎረቤቶቿ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ኃላፊው ተናግረዋል።

"ምን አልባት የአልቃይዳ ህዋሶች፣ ምን አልባትም መቀመጫውን አፍጋኒስታን ያደረገው አይሲስ በማዕከላዊ እስያ የሽብር ድርጊት እንዲፈፀም ሊያነሳሱ ይችላሉ" ብለዋል አንድሬ።

አንድሬ በአፍጋኒስታን ተጨማሪ አለመረጋጋትን የሚያስከትል ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችልም ስጋት አላቸው።