የኢትዮጵያና የቱርክ መሪዎች ውይይት በአንካራ

በትናንትናው ዕለት በቱርኳ መዲና አንካራ የተገናኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ፕሬዚዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶጋን የትግራይ ግጭት፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ የድንበር ውዝግብን በተመለከተ መክረዋል፤ እንዲሁም ወታደራዊ ስምምነቶችም ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል።

ሁለቱ አገራት ወታደራዊ የገንዘብ ስምምነትን ላይ መፈራረማቸው ቢገለፅም የስምምነቱ ዝርዝር አስካሁን ይፋ አልሆኑም።

ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን የትግራይን ጦርነት በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጠይቀው ግጭቱንም ለመፍታት አገራቸውም የምትችለውን ሁሉ ታደርጋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአስቸጋሪ ወቅት እያለፈች መሆኑንም አስታውሰው ለትግራይ ግጭት ለዘብተኛ መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባ ሃሳብ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገራት ውስጥ ቁልፍ ሚና የምትጫወት ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ "የግዛት አንድነቷ መጠበቅም ሆነ ሰላም ለእኛ ጠቃሚ ነው" በማለት አገሪቷ ያላትን ስፍራ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ግጭቱ በሰላም እንዲፈታም ከፍተኛ ትኩረት መንግሥታቸው መስጠቱን ጠቅሰው "ካለበለዚያ ግጭቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የቀጠናው አጎራባቾች አገራትም መጎዳታቸው አይቀርም" ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ኤርዶጋንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ረቡዕ ዕለት ነሐሴ 12/2013 ዓ.ም በአንካራ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው ይህንን የተናገሩት።

የሁለቱ አገራት መሪዎች በተገናኙበት ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል በአልፋሽቃ ያለውን የድንበር ውዝግብና ፍጥጫም አንስተዋል።

ግጭቱ በውይይት እንደሚቋጭ ተስፋ አድርገው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትናንትናው ዕለት እንዲሁም ከሱዳኑ ሽግግር ምክር ቤቱ ሊቀመንበር አብዱልፈታህ አልቡህራን ጋር ከሳምንት በፊት ውይይት ማድረጋቸውን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

"በሰላማዊ ሁኔታ እንዲቋጭም ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ነን። አደራዳሪነትንም ጨምሮ" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የሁለቱ አገራት መሪዎች ለዘመናት የዘለቀውን ግንኙነታቸውን በተመለከተ እንዲሁም በምጣኔ ሀብት፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት ያለው ትስስር በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የኢንቨስትመንት ግንኙነት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም በመሰረተ-ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በጨርቃ ጨርቅና በሌሎችም ዘርፎች ላይ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ዓመታዊ የንግድ ግንኙነትም 650 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን ፕሬዚዳንቱም አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሁለትዮሽ ንግድን እውን ለማድረግ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች መገምገማቸውን ተናግረዋል።

በርካታ የቱርክ ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው ከዚህም በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንንም እኚሁ ኩባንያዎች መቅጠር መቻላቸውንም አስታውሰዋል።

"በኢትዮጵያ ውስጥ የምናደርገው ይህ ኢንቨስትመንትም እንደሚጨምር ተስፋ አለን። በዚህ ረገድም አስፈላጊውን ድጋፍና እውቅና እንሰጣለን፤ ከዚህም ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት ኩባንያዎቻችንን እንደሚደግፍ እርግጠኞች ነን" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትም እንዲጠናከር አገራቸው አጥብቃ እንደምትሰራ የመንግሥታቸውን አቋም ገልፀዋል።

ለቱርክ ኢንቨስተሮችም ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን በማለትም ለፕሬዚዳንቱ መልሰዋል።

ሁለቱ አገራት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ጠቃሚ ያሉትን ስምምነቶችን መፈራረማቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህም ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ማኅበራዊ ትብብሮችን ስምምነቶችንም ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት የተመሰረተው "በመከባበር፣ በመተማመን እና በትብብር ላይ ነው" በማለት በዚህ አስፈላጊ ወቅትም ቱርክ አጋርነቷንና ወዳጅነቷን ማሳየቷን አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንንም በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው "የቱርክ መንግሥት እና ሕዝብ ያደረገልንን የወሳኝ ጊዜ ትብብር አገራችን ኢትዮጵያ መቼም አትረሳውም" በማለት አስፍረዋል።

ኢትዮጵያ የቱርክን አጋርነትና ወዳጅነት ዋጋ እንደምትሰጥ ገልፀው በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የቱርክ 'ኮኦፐሬሽንና ኮኦርዲኔሽን ኤጀንሲ' በአዲስ አበባ ምስረታንም በመጥቀስ ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሁለቱን አገራት ጥንታዊ ስልጣኔ ተመሳሳይነት አስታውሰው 16ኛው ክፍለ ዘመንም ወደኋላ ያስቆጠረ ነው ብለዋል። ቱርክ ለብዙዎች አርዓያ የሆነ የአገር ግንባታ እንዳካሄደች በዚሁ አጋጣሚ ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በተለይም አገሪቱ በለውጥ ጎዳና እየሄደች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውንም ለማጠናከር እየሰሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የሁለቱም አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የቀጠለ ነው እንዲሁም የቱርክ ፊልም ኢንዱስትሪ ለዚህም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በአውሮፓውያኑ 2015 ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰው "ኢትዮጵያ ምንጊዜም ቢሆን የመቻቻልና ልዩነቶች የሚከበሩባት ምድር ናት። ይህም የኢትዮጵያን የአገር ውስጥ እና የውጭ ግንኙነት መሰረት መንፈስን ያጠቃለለ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር በቱርክ ያደረጉትን የአንድ ቀን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ረቡዕ ምሽት ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው ተገልጿል።