አፍጋኒስታን፡ ታሊባን 'በቀል አይኖርም' ቢልም ለቀድሞው መንግሥትና ለውጭ ኃይሎች የሠሩትን እያደነ ነው

ታሊባኖች ሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት-ኔቶ ወይም ለቀድሞው የአፍጋኒስታን መንግሥት የሠሩ ሰዎችን ማደን ቀጥለዋል ሲል የተባበሩት መንግሥታት አስጠነቀቀ።

ታጣቂዎቹ ሰዎቹን ለማግኘት ቤት ለቤት እየዞሩ እየፈለጉና ቤተሰቦቻቸውን ማስፈራራታቸውን ተመድ በሰነዱ አስፍሯል።

አክራሪው እስላማዊ ቡድን ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ አፍጋኒስታኖችን ለማረጋጋት "የበቀል እርምጃ አይኖርም" በማለት ቃል ገብቶ ነበር።

ታሊባኖች ጭካኔ ከተሞላው የ1990ዎቹ ቡድን ወዲህ ብዙም አልተለወጠም የሚል ስጋት አለ።

ቡድኑ "ተባባሪዎች" ላይ ማነጣጠሩን ለተባበሩት መንግሥታት የደህንነት መረጃ የሚሰጠው ሪፍቶ የኖርዌይ ዓለም አቀፍ ትንታኔዎች ምስጢራዊ ሰነድ ይፋ አድርጓል።

ከሪፖርቱ በስተጀርባ ያለውን ቡድን የሚመሩት ክርስቲያን ኔልማን ለቢቢሲ "ታሊባን ዒላማው ውስጥ ያስገባቸው ግለሰቦች ቁጥር ከፍተኛ ነው። ዛቻው በጣም ግልፅ ነው" ብለዋል።

"ራሳቸውን አሳልፈው እስካልሰጡ ድረስ ታሊባኖች በግለሰቦቹ ስም የቤተሰብ አባሎቻቸውን በቁጥጥር ስር ያውሏቸዋል፣ ይጠይቋቸዋል እንዲሁም ይቀጣሉ።" ብሏል ሰነዱ።

በታሊባን የጥቁር መዝገብ ዝርዝር ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ከፍተኛ አደጋ ላይ መሆኑን እና የጅምላ ግድያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።

የውጭ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ከአፍጋኒስታን የማስወጣት ጥረታቸውን ቀጥለዋል።

የኔቶ ባለሥልጣን አርብ እንዳስታወቁት ባለፉት አምስት ቀናት ከካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ከ18,000 በላይ ሰዎች እንዲወጡ ተደርጓል።

ከእነዚህ ውስጥ 6,000 የሚሆኑትና የቀድሞ የውጭ አገራት ጦር ኃይሎች አስተርጓሚዎችን የያዘውን ቡድንም ለማስወጣት ዝግጅት ተደርጓል።

እንደ ባለሥልጣኑ ከሆነ ዓላማው በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ካቡልን የሚለቁ ሰዎችን በእጥፍ ማሳደግ ነው ብለዋል።

ከአውሮፕላን ማረፊያው ውጭ ያለው ምስቅልቅል እንደቀጠለ ነው። አፍጋኒስታኖች እንዳይሸሹ ታሊባኖች አግደዋል። በአንድ ቪዲዮ ላይ ደግሞ አንድ ሕፃን ለአሜሪካ ወታደር ሲሰጥ ታይቷል።

ታሊባን የውጭ ኃይሎች መውጣታቸውን ተከትሎ ባሳለፍነው እሁድ ካቡልን በቁጥጥሩ ሥር አድርጓል።

በአሜሪካ መር ወረራ ድላቸውን የተነጠቁት ታሊባኖች ከ 20 ዓመታት በኋላ ሥልጣን አግኝተዋል።

ቡድኑ ቀደም ሲል በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በሕዝብ ፊት ቅጣት ማከናወንን እና ሴቶችን ከሥራ ቦታ ማገድን ጨምሮ ሰፊ በደሎች ታይተዋል።

ቡድኑ አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ በኋላ በሰጠው የመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫ የሴቶች መብት "በእስልምና ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ" እንደሚከበር በሚያስታርቅ ሃሳብ ቃል ገብቷል።

ታሊባን ሴቶች ቡርቃ (ፊትን እና አካልን የሚሸፍን ልብስ ) እንዲለብሱ እንደማያስገድዱ ቃል መግባታቸው ተነግሯል። ሂጃብ ወይም የጸጉር መሸፈኛ ደግሞ አስገዳጅ ይሆናል።

በተጨማሪም "ማንኛውም የውስጥ ወይም የውጭ ጠላቶች" እንደማይፈልጉ እና ለቀድሞው የጸጥታ ኃይሎች አባላት እና ከውጭ ኃይሎች ጋር ለሠሩ ሰዎች ምህረት እንደሚያደረጉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ኃይሎች እና ብዙ የአፍጋኒስታን ዜጎች ግን ጥርጣሬ አላቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዳሉት ድርጅቱ ታሊባን ላይ ያለው ብቸኛ አቅም ታጣቂው ለዓለም አቀፋዊ እውቅና ያለው ፍላጎት ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ታሊባን ተቀይሯል ብለው ሲጠየቁ አለመቀየሩን አስታውቀው ቡድኑ እውቅና የማግኘት "ህልውናዊ" ምርጫ ገጥሞታል ብለዋል።