የኢትዮጵያ ባንኮች ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ መገንባታቸው ምን ያህል አዋጭ ነው?

የፎቶው ባለመብት, ADUGENET.COM
ከሰማይም ይሁን ከምድር ከፍ ብለው ከሚታዩ ዘመናዊ የአዲስ አበባ ረጃጅምና አዳዲስ ሕንፃዎች መካከል አብዛኛዎቹ ንብረትነታቸው የባንኮች ነው።
በዚህም ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ ብሔራዊ ቴአትር ድረስ ያለው ኮሜርስ ተብሎ በሚታወቀው እንዲሁም በስቴዲየም አቅራቢያ ባሉ ተቀራራቢ ስፍራዎች በአገሪቱ ያሉ ባንኮች ባስገነቧቸውና እያስገነቧቸው ባሉ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ደምቋል።
በከተማዋ አራቱም አቅጣጫዎች ቢሆኑ ጎልተው ከሚታዩት መካከል አዲሱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ፣ ጥቂት ዓመታት ያስቆጠረውን የአዋሽ ባንክንና የወጋገን ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ረጃጅም ህንጻዎችን መጥቀስ ይቻላል።
አዳዲሶቹ የዳሸን ባንክ፣ ዘመን ባንክና ንብ ባንክ ሕንፃዎችም አንገታቸውን አርዝመው ከሚታዩት መካከል ናቸው።
በቅርቡ ሥራ የሚጀምሩ የባንክ ሕንፃዎች
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ 2 ቢሊዮን ብር ያወጣበትን የዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ግንባታ ተጠናቅቋል።
ላለፉት 4 ዓመት ሲገነባ የቆየውና ንብ አና የንብ እንጀራ ቅርፅ እንዲኖረው ተደርጎ የተሠራው ህንፃ ወዲያው ወደ ሥራ እንደሚገባ ተሰምቷል።
37 ፎቆች ያሉት ይህ ሕንፃ የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ሆኖ ከማገልገል አልፎ የተለያዩ ቢሮዎች፣ ሱቆች፣ የህፃናት መዋያ፣ የስፖርት ማዘወተሪያ፣ 500 ሰው የሚይዝ አዳራሽና ለሌሎች አገልገሎት የሚውሉ ክፍሎች አንዳሉት ተነግሯል።
የህንፃው ወጪ ሲጀመር በ1.67 ቢሊየን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም የዲዛይን ለወጥ በመደረጉ ወጪው 2 ቢሊዮን መድረሱን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ገነነ ሩጋ አሳወቀዋል።
በአዲስ አበባ ራስ አበበ አረጋይ ጎዳና ንግድ ስራ ት/ቤት ( ኮሜርስ) ፊት ለፊት የተገነባው የባንኩ ህንፃ አብዛኛው ክፍሎቹ ለባንኩ አገልግሎት ሲውሉ ቀሪዎቹ ቢሮዎች ይከራያሉ ተብሏል።
አዲሱ ህንፃ ባንኩ በዓመት ለዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ኪራይ የሚያወጣውን 30 ሚሊዮን ብር እንደሚያስቀርለትም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር የሚጠበቀው ግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ከመሆን አልፎ የተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚሰጥ ይታመናል።
የአልማዝ ቅርፅ ያለው ባለ48 ፎቁ ሕንፃ 210 ሜትር ገደማ ወደላይ ይመዘዛል። ሕንፃው ከ1500 በላይ መኪናዎችን ማቆየት እንደሚችል ባንኩ በፌስቡክ ገፁ ይፋ አድርጓል።
ንግድ ባንክ አዲሱን ዋና መሥሪያ ቤት ሙሉ ለሙሉ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ እንደሚያወጣ ይፋ አድጎ ነበር።
ባንኮች ረዣዥም ሕንፃ መሥራታቸው ያዋጣል?
የንግድ አማካሪውና ሎውረንዱ አሶሲዬትስ የተሰኘው የአማካሪዎች ስብስብ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት በርናር ሎውረንዱ ባንኮች የሚገነቧቸውን ሕንፃዎች በአግባቡ እየተጠቀሙበት አይደለም ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ይጽፋሉ።
በርናር እየፈካ ያለው የጀማሪ ቢዝነሶች ማበብና የባንኮች አካሄድ እየተጣጣመ አይደለም ባይ ናቸው።
ባለሙያው ባንኮች አዳዲስ ሕንፃ በሚገነቡበት ወቅት የት ነው መገንባት ያለብን፤ እንዴት ማዘመን እንችላለን፣ እንዴትስ ከአዳዲስ ቢዝነሶች ጋር መሥራት እንችላለን የሚለውን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው ይላሉ።
ለንደን የሚገኙት በኦዲት፣ አካውንቲንግና በማማከር የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው አብዱልመናን መሐመድ በበኩላቸው ባንኮች በተለያዩ ቢዝነሶች ላይ እንዳይሰማሩ ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠባቸው ገደብ አለ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ለምሳሌ ሪል ስቴት ላይ ለመሠማራት ከ10 በመቶ በላይ የተጣራ ገቢያቸውን እንጂ ከዚያ በላይ መጠቀም አይችሉም። ነገር ግን ለራሳቸው ለመጠቀም መገንባት ይችላሉ። ይህን ብሔራዊ ባንክ ይፈቅዳል።"

የባንኮች ሕንፃ ግንባታ ለምን?
"ባንኮች በብዛት ሕንፃ እየገነቡ ያሉበትን ምክንያት በሁለት አቅጣጫ ልናየው እንችላለን" ይላሉ አብዱልመናን።
"አንደኛ አሁን ባለው የኑሮ ውድነት [ኢንፍሌሽን] ምክንያት የአክሲዮን ባለቤቶች ገንዘብ እየተበላ እንዳይመጣ ለመጠበቅ ነው ብለን ልናየው እንቸላለን። ምክንያቱም ቋሚ ንብረት ላይ የዋለ ስለሆነ። ሁለተኛ የብሔራዊ ባንክ ድጋፍ ያለበት ሳይሆን አይቀርም።"
አብዱልመናን ባንኮች ሕንፃ የሚገነቡት ካላቸው አጠቃላይ ሀብት ምን ያክሉን ተጠቅመው ነው ብለን ብንል ከ2 በመቶ አይበልጥም ይላሉ።
"አማካይ የኢንዱስትሪው ቁጥር ብናይ ባንኮች ከአጠቃላይ ካፒታላቸው አንድ አራተኛውን ይሆናል፤ ሕንፃዎች ላይ እያፈሰሱ ያሉት። በዚህ መልኩ ሲታይ ከባድ ገንዘብ የሚባል አይደለም።"
ባለሙያው አክለው ባንኮች ዋና መሥሪያ ቤት ያስፈልጋቸዋል፤ አሊያ ወደ መከራየት ሊሄዱ ነው ሲሉ ቋሚ ንብረት መገንባቱ አስፈላጊ ነው የሚለውን ነጥባቸው ያጠናክራሉ።
በርናር ባንኮች ሕንፃ ሠርተው ሠራተኞቻቸው ከማስገባት ይልቅ ለደንበኞቻቸው ሊዝ ቢያደርጉትና እንደ ሪል ስቴት ተቋም ቢያዩት ሲሉ ይመክራሉ።
አብዱልመናን ደግሞ እንደውም አንዳንድ ባንኮች መቶ በመቶ እየተጠቁመባቸው ነው ባይ ናቸው።
"እኔ እስከማውቀው አዋሽ ባንክ የሠራው ሕንፃ አልበቃ ብሎት ሌላ ሕንፃ ለመሥራት እያሰበ ነው። ዳሸን ባንክም ለማስፋፋት እያሰበ ነው። ነገር ግን እንደ ባንኩ አቅም ይለያያል። አንዳንድ ባንኮች ብዙ ሠራተኛና ዲፓርትመንት ስላላቸው ላይበቃቸው ይችላል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ያላቸው ባንኮች ግን በአግባቡ ላይጠቀሙበት ይችላሉ።"
"ያው ባንኮች ወደፊት ማደጋቸው አይቀርም። እሱንም ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይችላል። ሌላው ደግሞ ቅድም እንዳልኩት አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ገንዘቡ እንዳይበላ ቋሚ ንብረት ላይ ማዋሉ ይበጃል። እኔ ባንኮች ሕንፃ መገንበታቸው ትክክለኛ ያልሆነ መዋለ ፈሰስ [ኢንቨስትመንት] ነው የሚል እምነት የለኝም።"
ለአዳዲስ ቢዝነሶች ማከራየት
የቢዝነስ አማካሪው በርናር ትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ሐሳብ ዋነኛ ትኩረታቸውን አዳዲስና አዳጊ ቢዝነሶች ላይ አድርገዋል።
አብዱልመናንም በከተማዋ ብዙ የሚከራዩ ሕንፃዎች እየተገነቡ ስለሆነ የተከራይ እጦት ካልሆነ በቀር ማከራየቱ ተገቢ ነው ሲሉ ከበርናር ሐሳብ ጋር ይስማማሉ።
"ክፍለ አገር አካባቢ ሕንፃዎች ያሏቸው ባንኮች አከራይተው ብዙ ገቢ እንደሚያገኙ ይታወቃል። ትርፍ ቦታ እስካላቸው ድረስ ያንን ቦታ አከራይቶ ገቢ ማግኘት ተገቢም ነው፤ አስፈላጊም ነው።"
በርናር ባንኮች የፊት፣ የመሃልና የኋላ ቢሮዎቻቸውን ማዘመን [ዲጂታይዝ] ማድረግ ይገባቸዋል ይላሉ። አልፎም ቅድሚያ የማይሰጣቸውን ሂደቶች ለውጭ ድርጅቶች መስጠት ተገቢ ነው ባይ ናቸው።
ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ግን ባንኮች በሮቻቸውን ለአዳዲስና አዳጊ ቢዝነሶች [ስታርታፕ] ክፍት ማድረጋቸው እንደሆነ ያሰምሩበታል።
በርናር አክለው አዳዲሶቹ ቢዝነሶች ባንኮች በራሳቸው ላይወጧቸው የሚችሉ ዘርፎች ላይ ቢሰማሩ በጋራ መሥራት ይችላሉ ይላሉ።
የሌሎች አገራት ተሞክሮ
አብዱልመናን ያደጉት አገራት የሕንፃ አጠቃቀም ላይ ላቅ ያለ ልምድ ያላቸው ናቸው ሲሉ ልምዳቸውን ያካፍላሉ።
"እኔ ያለሁበት ለንደን እንኳ ባንኮች 'ፋይናንሻል ሴንተር' [የንግድ ማዕከል] ላይ ነው ያሉት። ሊቨርፑል ስትሪት የሚባል አለ ለንደን ውስጥ። ትልቅ የንግድ ማዕከል ስለሆነ ኪራይ በጣም ውድ ነው። ስለዚህ ሕንፃ አጠቃቀም ላይ በጣም ብቁ ናቸው።"
አልፎም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው በጣም ያደገ ስለሆነ አንዳንድ ቢሮዎቻቸው ሌሎች አገራትም ሊያደርጉት ይችላሉ እንጂ አንድ ቦታ የተጠራቀሙ አይደሉም ይላሉ ተንታኙ።
"አሁን አሁን እየተለመደ የመጣው አንዳንድ አገልግሎት ከሕንድ ነው የሚሰጠው። እንደውም አሁን ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ከቤት የመሥራት ልምድ ስለመጣ የተወሰኑ ፎቆችን እያከራዩ ነው። የእኛም ባንኮች ወደፊት ቴክኖሎጂው እየተጠናከረ ሲመጣ የግድ አንድ ቦታ ተጠራቅሞ መሥራት ላይጠበቅባቸው ይችላል።"
በአጠቃላይ ሕንፃዎች ከዋጋ ንረቱ አንፃር ትላልቅ ሕንፃዎች መገንባታቸው ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል ይላሉ ባለሙያው።
"ነገር ግን መመዘኛው ይህ ብቻ ነው እያልኩ አይደለም። መከራየት ያዋጣል ወይስ መገንባት እንዲሁም ሌሎች መመዘኛዎችን አስቀምጠው ነው መወሰን ያለባቸው። በተጨማሪ የብሔራዊ ባንክ ግፊት እንዳለበትም መዘነጋት የለበት።"














