በኦሮሚያ ክልል ከ400ሺህ ሕዝብ በላይ ለምግብ እጥረት መጋለጡ ተነገረ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ለረጅም ጊዜ በቆየ የዝናብ እጥረት ሳቢያ ከ400 ሺህ በላይ ሕዝብ ለምግብ እጥረት መጋለጡ ተነገረ።

የምግብ እጥረቱ ያጋጠመው በዞኑ በሚገኙት ሻላ፣ ሲራሮ፣ ሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌ እና ወንዶ ተብለው በሚጠሩ አምስት ወረዳዎች ውስጥ ነው።

የምዕራብ አርሲ ዞን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኃላፊ አቶ ያሲን ጋርጁ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በዞኑ የበጋ ወቅት በመርዘሙ እህል ሳይዘራ በመዘግየቱ የምግብ እጥረቱ ሊያጋጥም ችሏል።

"ከዚህ ቀደም የምግብ እጥረቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች እህል የሚዘራው በበልግ ወቅት ዝናብ ነበር። ይሁን እንጂ ዘንድሮ ከመስከረም እስከ ሰኔ ወር ድረስ ዝናብ አልነበረም። በዚህም ምክንያት የምግብ እጥረቱ ሊከሰት ችሏል" ብለዋል አቶ ያሲን።

ኃላፊው ከአምስቱ ወረዳዎች በሁለቱ ማለትም በሻላ እና ሲራሮ ከምግብ እጥረት በተጨማሪ የውሃ እጥረት መኖሩንም ተናግረዋል።

የምግብ እጥረት ካጋጠማቸው ሰዎች መካከል የተወሰኑት ከዚህ ቀደምም ድጋፍ ይደረግላቸው እንደነበር አስረድተዋል።

የሻላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ቃበቶ ቱፋ ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው እንደዚህ አይነት የከፋ የምግብ እጥረት አጋጥሞ እንደማያውቅ ተናግረዋል።

"አሁን ረሃብ አለ። ምንጩ ደግሞ የዝናብ እጥረት ነው። ውሃ ሙሉ ለሙሉ የለም። አላረስንም። ከዚህ ቀደም አይተነው የማናውቀው ነገር ነው የመጣብን" በማለት በአካባቢያቸው የተከሰተው የምግብ እጥረት የከፋ መሆኑን ይናገራሉ።

ነዋሪው እንደሚሉት ከሆነ በአሁኑ ወቅት በሌሎች አካባቢ ካሉ ነዋሪዎች ድጋፍ ባይቸራቸው ኖሮ ለከባድ ችግር ይጋለጡ የነበሩ ሰዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላኛው የሻላ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጋሪና ቦንያስ፤ አሁን ያለው የከፋ የምግብ እጥረት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።

"ቀድሞውንም ቢሆን ውሃ የለም። በዚያ ላይ ዝናብ ጠፋ። እኔ በረሃብ የሞተ አውቃለሁ። አቅሙ የተዳከመም አለ። በዚህ ሁኔታ ሁላችንም የምንተርፍ አይመስለኝም" በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የምዕራብ አርሲ ዞን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኃላፊው አቶ ያሲን ጋርጁ የምግብ እጥረቱ ይከሰት እንጂ በምግብ እጥረቱ ሳቢያ እስካሁን ሕይወቱ ያለፈ ሰው ስለመኖሩ ሪፖርት አለመደረጉን ይናገራሉ።

ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት እና በምግብ እጥረቱ የሰው ሕይወት እንዳያልፍ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር ከክልል እና ከፌደራል መንግሥት ጋር እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።