የኢትዮጵያዊ ቤተሰብን የትምህርት ጉዞ የሚያሳይ ፎቶ በ'ኧርዝ ፎቶ' ውድድር አሸናፊ ሆነ

በኢትዮጵያ አንድ ቤተሰብ በትምህርት የደረሰበትን ጉዞ የሚያሳይ ፕሮጀክት የዘንድሮው 'ኧርዝ ፎቶ' ውድድር አሸናፊ ሆኗል።

ሮዚ ሃላም የተባለችው የፎቶ ባለሙያ በአንድ ፍሬም ላይ ሶስት ፎቶዎችን በማሳየት የመማር መብትን ታስቃኛለች።

በፎቶው ላይ የትምህርት መመዝገቢያ ዕድሜዋ ካለፈ በኋላ ትምህርት ቤት የገባችው ሰላማው በዋነኝነት ትታያለች።

ትምህርት ቤት በመግባት ለወላጆቿ መሰለችና ማርቆስ የመጀመሪያዋ ናት።

ቤተሰቡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ኑሮም ነው የሚተዳደሩት።

እነዚህ ፎቶዎች 'ፒፕል' (ሰዎች) በተሰኘው ዘርፍም አሸናፊ ሆነዋል።

'የፆታ እኩልነት'

ሃላም "ትምህርት መሠረታዊ የሰው ልጅ መብት እና ብልህ ኢንቨስትመንት ነው" ትላለች።

"ለልማት ወሳኝ እና ለማህበራዊ ደህንነት ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ደህንነት ፣ ለጾታ እኩልነት እና ለሰላም መሠረቶችን ለመጣል ይረዳል።" በማለትም ታስረዳለች

የእንግሊዝ ፎረስትሪ ድርጅትና ሮያል ጂኦግራፊካል ሶሳይቲ 55 ፎቶግራፎች እና ከአራት ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ በስድስት ምድቦች አሸናፊዎቹን መርጠዋል።

ውድድሩ ዓላማው

· በአካባቢያዊ የእይታ ሚዲያ ውስጥ ምርጡን ማሳየት

· ስለ ዓለም እና ስለ ነዋሪዎቿ ውይይቶችን ማበረታታት

ኤድዋርድ ባትማን በበረዶ የተሸፈነ ግማሽ ጉልላትን በሚያሳየው ፎቶው 'ዘ ፕሌስ' በተሰኘው ዘርፍ አሸናፊ ሆኗል።

በኮቪድ የጉዞ ገደቦች ምክንያት ወደ ባህራዊ ፓርክ መጓዝ ያልቻለው የፎቶ ባለሙያው ይህንን ትዕይንት በማዕድ ቤት ጠረጴዛው ላይ ከአሜሪካ የጂኦግራፊ ዳሰሳ ጥናት (ዩኤስጂኤስ) በተገኘ በ3ዲ የታተመ የመሬት ገፅታና የጭጋግ ማሽንን በመጠቀም ነው የፈጠረው ተብሏል።

በአይስላንድ ብዙም ሰው በማይኖርበት የደጋ ሜዳ ላይ የተደበቀ ፍልውሃን በሚያሳይ ፎቶው የማርከስ ቫን ሀውተን 'ብሉ ፑል' (ሰማያዊ ገንዳ) የተሰኘው ስራው በ' ኔቸር' (ተፈጥሮ) ምድብ አሸንፏል።

በስፔን ውስጥ ለምለም የደን ተዳፋት ከሰው ሰራሽ የወይን እርሻዎች ላይ ተቀናጅቶ በተነሳው የአየር ላይ ምስል ሮቤርቶ ፎረስት 'ጋርደን ቸንጂንግ ፎረስት' ካታጎሪ ምድብ አሸንፏል።

የአንቶኒዮ ፔሬዝ በምዕራብ አፍሪካ በባሕር ዳርቻ መሸርሸር የተጎዱ ግለሰቦችን የሚያሳየው ተከታታይ 'ዘ ሲ ሙቭስ አስ፣ ፉቩሜህ ጋና' በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ አሸንፏል።

እንዲሁም በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የተደረው የኑውክሌር ሙከራ ወንጀልን የሚያጋልጠውና በሰዎችና በአካባቢዎች ላይ የደረሰውን ጫና የሚዳስሰው የፒርፓኦሎ ሚቲካ አጭር ፊልም ሴሚፓላቲንስክ ፖሊጎን በቪዲዮ ምድብ ማሸነፍ ችሏል።

በዚህ ውድድር ላይ ዕጩ የሆኑት ፎቶዎች በኧርዝ ፎቶ አውደ ርዕይ ለሁለት ሳምንታት ያህል ለንደን በሚገኘው ሮያል ጂኦግራፊካል ሶሳይቲ ፓቭልዮን ውስጥ ለዕይታ ይቀርባሉ።

እንዲሁም የተመረጡ ፎቶዎች በእንግሊዝ ፎረስትሪና ፎረስትስ ለዕይታ እንደሚቀርቡ ተገልጿል።