ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን የማደራደር ጥያቄዋ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ከኢትዮጵያ አምባሳደሯን መጥራቷ ተነገረ
ሱዳን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አምባሳደሯን በዛሬው ዕለት ነሐሴ 2፣ 2013 ዓ.ም መጥራቷን ሮይተርስ ዘግቧል።
ለዚህም እንደ ምክንያትነት የተጠቀሰው በትግራይ በቀጠለው ጦርነት ለማደራደር ያቀረበችው ሃሳብ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ነው።
ኢትዮጵያ ሱዳን ላይ እምነት መጣል የምትችልበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ሱዳንን እንደ ታማኝ አደራዳሪ ለመቀበል እንደሚያስቸግር የጠቅላይ ሚንስትር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ከሰሞኑ መናገራቸው ይታወሳል።
"ኢትዮጵያ ሱዳን ማድረግ የምትችለውን ካሰበች አቋሟን ታሻሽላለች።..... ሙሉ በሙሉ ጥረቷን ውድቅ ከማድረግ ይልቅ" በማለት የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች መዛመቱን እንዲሁም በትግራይ ክልል እያሽቆለቆለ ስለመጣው የሰብዓዊ ሁኔታ በተመለከተ ያላቸውን ስጋት አንስተው ከሰሞኑ ተወያይተዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ረቡዕ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ ባለሥልጣናቱ ከዚህም በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ስለሚሉ ሪፖርቶችና በቀጠናው መረጋጋት ላይ ስለሚያሳድረው ተፅእኖ መክረዋል መባላቸው የሚታወስ ነው።
በትግራይ ጦርነት የተነሳ ከ53 ሺህ በላይ ስደተኞችን ሱዳን የተቀበለች ሲሆን፤ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ለማደራደር የተነሱትም በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ሊቀ መንበርነት ማዕቀፍ መሆኑንም መግለጫውን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ በዘገባው አስነብቧል።
ኢጋድ ኬንያ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ኡጋንዳ ፣ ጅቡቲ ፣ ሱዳን ፣ ኡጋንዳ እና ሶማሊያን ያካተተ ቡድን ነው።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ አቀባዮች ሱዳን አምባሳደሯን መጥራቷን አስመልክቶ ከሮይተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
ነገር ግን ከሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢልለኔ ስዩም "ሱዳንን በአደራዳሪነት ለመውሰድ በቅድሚያ መተማመን ጉዳይ ላይ በጥልቀት መኬድ አለበት ብለን እናምናለን" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በተለይም የሱዳን ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት እንደሻከረ እና በበላይ አመራሮች ዘንድ እምነት እንደተሸረሸረ ቢልለኔ ጠቁመዋል።
ሱዳን እና ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ለም በሆነው ለእርሻ ተስማሚው አልፋሽቃ የድንበር አካባቢ ይገባኛል በሚል ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ ከገቡ ወራት ተቆጥረዋል።
ሱዳን በትግራይ ግጭት በተነሳበት ወቅት በአካባቢው የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም ግዛቶቹን ተቆጣጥራለች።
ሁለቱ አገራት ተፋጥጠው በሚገኙበት በዚህ የድንበር ይገባኛል ምክንያት ወደ ጦርነት መግባት እንደማይፈልጉ ቢገልፁም የሁለቱ አገራት ሠራዊት ግን በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይሰማል።
ሱዳን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1902 የተፈረመው የአንግሎ-ኢትዮጵያ የካርታ ላይ ምልከታ ስምምነት አልፋሽቃ የእኔ መሆኑን በእርግጠኝነት ያሳያል ስትል ትገልጻለች።
አክላም በርካታ ኪሎ ሜትሮች የሚረዝመው የሁለቱ አገራት የድንበር አካባቢ በአግባቡ ባለመካለሉ ከ1980ዎቹ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ድንበሩን ዘልቀው ይገባሉ ስትል ትከስሳለች።
ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳያቸውን ለመፍታት ከተደረጉት ሁሉ የተሻለው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተደረገው ውል ወይም ስምምነት እንደሆነ ይነገራል።
በዚህ ስምምነትም መሰረት አገራቱ በይዞታቸው ስር ያላቸውን ግዛቶች ይዘው እንዲቆዩና የአገራቱ መንግሥታት ድንበራቸውን በተመለከተ ጥናት ተደርጎ የድንበር ጉዳይ በሰላም እንዲካለል ለማድረግ ተስማምተዋል።