አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ በኢትዮጵያ ጉብኝት ጀመሩ

የፎቶው ባለመብት, OCHA
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማስተባበሪያ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የስድስት ቀናት ጉብኝት ዛሬ ጀምረዋል።
ግሪፊትስ ይህንን ኃላፊነት ቦታ እንዲይዙ የተሾሙት ባለፈው ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ሲሆን በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝትም የመንግሥታቱን ድርጅት ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ የመጀመሪያቸው ነው።
"የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ሆኜ የመጀመሪያውን ይፋዊ ተልዕኮዬን ለማከናወን ወደ ኢትዮጵያ መሄዴ ለእኔ ወሳኝ ተግባር ነው" ብለዋል።
ማርቲን ግሪፊትስ ለቀናት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከረድኤት ተቋማት ተወካዮችና ከለጋሾች ድርጅቶች ማኅበረሰብ ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኃላፊው በጉዟቸው ወደ ትግራይ ክልል በመጓዝ በግጭቱ የተጎዱ ሰላማዊ ሰዎችን እንደሚያነጋግሩና የሰብአዊ እርዳታ በማቅረብ ላይ የተሰማሩ አካላት የገጠማቸውን ተግዳሮት በስፍራው ተገኝተው ለመመልከት አቅደዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው በክልሉ ካለው ነዋሪ 5.2 ሚሊዮን ወይም 90 ከመቶ የሚሆኑት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ያስፈልጋቸዋል።
አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ከትግራይ በተጨማሪ ወደ አማራ ክልል በማቅናት ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር የመወያየት ዕቅድ አላቸው ተብሏል።
"የሰብአዊ እርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ለተከሰተው ችግር ምላሽ ለመስጠት ከመንግሥትና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኞች ናቸው" ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።
ኃላፊው በዚህ ጉዟቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና አጋሮች ጋር የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያን ሕዝብ በተሻለ መልኩ እንዴት ሊያገለግል እንደሚችል ውይይት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
"በመላው አገሪቱ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ለማሻሻል የሚያስችል ገንቢ ውይይት አደርጋለሁ" ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ90 በላይ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ከሌሎች ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን በሰብአዊ እርደታ አቅርቦት ላይ ተሰማርተዋል።
የዩናይት ኪንግደም ዜግነት ያላቸው ማርቲን ግሪፊትስ ማርክ ሎውኮክን በመተካት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማስተባበሪያ ኃላፊነትን የተረከቡት ባለፈው ግንቦት አጋማሽ ላይ ነበር።















