የዓለም ምግብ ፕሮግራም አውሮፕላን ምሥራቅ ሐረርጌ ውስጥ ወደቀ

ኮምቦልቻ ወረዳ ኮሚኒኬሸን ጽ/ቤት

የፎቶው ባለመብት, ኮምቦልቻ ወረዳ ኮሚኒኬሸን ጽ/ቤት

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አውሮፕላን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ መውደቁ ተገለጸ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የእርዳታ ሠራተኞችን ጭኖ ከጅግጅጋ ወደ ድሬዳዋ እየበረረ ሳለ አውሮፕላኑ መውደቁን አረጋግጧል።

ድርጅቱ እንዳለው በአውሮፕላኑ ሁለት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ሠራተኞች እና ሁለት የበረራ ቡድን አባላት በአጠቃላይ አራት ሰዎች ተሳፍረው የነበረ ሲሆን በተሳፋሪዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት አለመድረሱን አረጋግጧል።

ድርጅቱ ጨምሮም አራቱም ተሳፋሪዎች የህክምና ምርመራ እንዲደረግላቸው ወደ ድሬዳዋ ሆስፒታል ተወስደዋል ብሏል።

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ ኮምዩኒኬሸን ጽህፈት ቤት አውሮፕላኑ በወረዳዋ ቄረንሳ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ መውደቁን አስታውቋል።

ኮምዩኒኬሸን ጽህፈት ቤቱ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው ዘገባው የወደቀውን አውሮፕላን ምስል አያይዞ ያቀረበ ሲሆን፤ በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩ አራት ሰዎች መሆናቸውን እና በአንዱ ላይ ብቻ አነስተኛ ጉዳት ሲያጋጥም በተቀሩት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም ብሏል።

ድርጅቱ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ አየር አገልግሎት በረራ እና ንብረትነቱ የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎቶች የሆነው አውሮፕላን የወደቀበት ምንክያት እየተጣራ ነው ብሏል ትናንት አመሻሻ ባወጣው ዘገባ።

አቢሲኒያ የበረራ አገልግሎቶች፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአቪዬሽን ባለስልጣናት የአደጋውን ዝርዝር ሁኔታ ይመረምራሉ ብሏል ድርጅቱ።