ትግራይና አማራ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ከባድ ውጊያ መካሄዱ ተነገረ

ትግራይ ውስጥ ቀደም ሲል በተደረጉ ውጊያዎች ወደሙ ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ትግራይ ውስጥ ቀደም ሲል በተደረጉ ውጊያዎች ወደሙ ተሽከርካሪዎች

የአማራ ክልልን ከትግራይ ጋር በሚያዋስኑት አካባቢዎች በሦስት ግንባሮች ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ቃል አቀባይ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገለጹ።

የአማራ ክልል የመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ረቡዕ እለት በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት በተለያዩ ግንባሮች በኩል ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተው አንዳንዶቹም ከባድ እንደነበሩ ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም በውጊያው ውስጥ ከክልሉ ኃይሎች በተጨማሪ ከህወሓት ኃይሎች ጋር በተደረገው ውጊያ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት መሳተፉን አመልክተዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ያስወጣ ቢሆንም የህወሓት ኃይሎች ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ የተኩስ አቁሙን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች የትግራይ ክልል በሚዋሰንባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ውስጥ በመግባት ጥቃት በመፈጸማቸው በተለያዩ ስፍራዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ እንደሆነ ይነገራል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቃል አቀባይ የሆኑት ቢልለኔ ስዩም ረቡዕ እለት አዲስ አበባ ውስጥ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት መንግሥት ያወጀው የተናጠል የተኩስ አቁም እንዳልተነሳ ገልጸዋል።

የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ጌታቸው ረዳ ግን የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊቱን ማሰማራት በመቀጠል ግጭቱን እያባባሰ ነው ሲሉ ከሰዋል።

በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለውን ግጭት ለማስቆም የተለያዩ ወገኖች ጦርነት እንዲቆምና ንግግር እንዲጀምር ጥሪ እያቀረቡ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጦርነቱ እየተበናባሰ መሆኑ ይነገራል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ግጭቱ የተስፋፋባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ርዕሰ መስተዳደሮች በህወሓት ኃይሎች ተከፈተብን ያሉትን ወረራ ለመከላከል የክልላቸው ነዋሪ እንዲነሳ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥም ከሠራዊቱ ጋር የሚሰለፉ ወጣቶች እየተመለመሉ ወደማሰልጣና እየገቡ መሆናቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በተከታታይ እየዘገቡ ይገኛሉ።

ቀደም ሲል የአገሪቱ ክልሎች በጦርነቱ ድጋፍ የሚሰጡ የልዩ ኃይል አባሎቻቸውን ወደ ጦር ግንባሮች መላካቸው ይታወሳል።