የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም እያከበረ እንደሚገኝ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, PM Office
የፌደራሉ መንግሥት ከአንድ ወር በፊት በትግራይ ክልል ያወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም በአሁኑ ወቅት እያከበረ እንደሚገኝ ተገለጸ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የፌደራል ሠራዊቱ ጥቃት እየሰነዘረ አይደለም ብለዋል።
ቢልለኔ ይህንን ምላሽ የሰጡት የፌደራል መከላከያ ሰራዊት አሁንም በተናጠል የተኩስ አቁም ላይ ነው? የሚል ጥያቄ በትናንትናው ዕለት በጋዜጠኞች መቅረቡን ተከትሎ ነው።
ሆኖም የፌደራል ሠራዊት ከተወሰኑ ከተሞች ለቆ ከወጣ በኋላ የህወሓት ኃይሎች የተኩስ አቁሙን በመጣስ በተለያዩ አካካቢዎች በጦርነቱን እየገፋና መከላከያ ሠራዊቱንም ሆነ ሌሎች ደጋፊ ኃይሎችን እየተነኮሱ ይገኛል ብለዋል።
ትንኮሳው የትግራይ ክልልን አቋርጦ ወደ አጎራባች ሁለት ክልሎች አማራና አፋር መግባቱንም ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሆኖም በዚህ ረገድ አሁንም የመከላከያ ሠራዊት የሰብዓዊ ተኩስ አቁሙ ላይ ቢሆንም ራሱን መከላከል እንዳለበትም አስምረዋል።
"ማናቸውም ወረራ በዚህ ቡድን የሚቀጥል ከሆነ ለአገሪቱም ስጋት ነው" ቢሉም መከላከያ በአሁኑ አቋሙ ማጥቃት ሳይሆን መከላከል መሆኑንም አስረድተዋል ።
በኢትዮጵያ የአማራ ክልል ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ ነው በትግራይ ያለው ጦርነት ወደ አጎራባች ክልሎች እየተዛመተ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር አሁን ባለው ጦርነት የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ልዩ ኃይሎች በጥምረት በመሆን አማፂውን ህወሓት ጋር እየተዋጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በተለያዩ ግንባሮች እያሸነፉ መሆናቸውን ገልፀው ሁሉም የጦርነት መረጃዎች ስለማይነገሩ ሕዝቡ በትዕግሥት እንዲጠብቅ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ መናገራቸው ይታወሳል።
የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት የትግራይ ኃይሎች እያሸነፉ እንደሆነ ገልፀው "በቆቦ እና በአዲ አርቃይና ጨው በር የነበሩት የመጨረሻዎቹ ጠንካራ ምሽጎች ተሰብረዋል" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የክልል ኃይሎች ህወሓትን ለመዋጋት ኃይሎቻቸውን እያሰባሰቡ ይገኛሉ።
ይህ እንዳለ ሆኖ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ባለፈው ወር ይፋ የተደረገው የአንድ ወገን የተኩስ አቁም እንደተከበረ ነው ብለዋል።
የፌደራሉ መንግሥት የተኩስ አቁሙን ከማወጁ በፊት በመጀመሪያው ዙርና በሁለተኛው ዙር ለ4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የክልሉ ነዋሪ እንደተደረገ እንዲሁም በሦስተኛው ዙርም እንዲሁ ለ4.9 ሚሊዮን ሕዝብ የክልሉ ነዋሪ እርዳታ ደርሷል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የተኩስ አቁም ከመደረጉ በፊት 580 ሺህ 136 ኩንታል ማዳበሪያ እንደተገዛና ከዚህም ውስጥ 536 ሺህ 879 ኩንታል በመቀለ ተከማችቶ የሚገኝና በአስር የግብርና ማኅበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሮች መከፋፈሉ ተገልጿል።
መከላከያ ከመቀለ በወጣበት ወቅት ከ400 ሺህ በላይ ኩንታል ስንዴ፣ 2.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለተቸገሩ ሰዎች እንዲከፋፈል በማከማቻዎች ውስጥ እንዲሁም ከዚህም በተጨማሪ 14 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅም በዲፖ ውስጥ እንደነበር ተገልጿል።
በነዚህ ማከማቻዎች ውስጥ የተቀመጡ የምግብ እርዳታዎችንም ህወሃት ለመመልመል እየተጠቀማባቸው እንደሆነም ሪፖርቶችን ዋቢ አድርገው ቃለ አቀባይዋ ተናግረዋል።
መንግሥት የተኩስ አቁሙን ያደረገው ለሰብዓዊ እርዳታ ቢሆንም ህወሃት ይህንን በመጣስ ህዝቡን ወደከፋ ችግር ውስጥ እየከተተው ይገኛል ብለዋል።
"ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የክልሉን አርሶ አደርና በችግር ላይ ያለውን ህዝብ ከመርዳት ይልቅ ህወሃት ነዋሪውን እንደ ሰብዓዊ ጋሻ እየተጠቀመው ነው" በአማራና በትግራይ ክልል የሚኖረውንም ማህበረሰብ እየተነኮሱት እንደሆነም ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የአማራ ክልል አርሶ እደርና የአፋር ክልል አርብቶ አደር "አሸባሪ" ብለው በጠሩት ህወሃት ኃይሎች እየተበጠበጠ ነው ብለዋል።
በክልሎቹ ሰላማዊ ዜጎች እየተገደሉም እንደሆነ ሪፖርቶች ደርሰውናል በማለትም አፅንኦት ሰጥተዋል።
በትግራይ ክልልም እንዲሁ የመንግሥት ደጋፊ ናቸው የተባሉ ተጋሩዎች እየተገደሉ እንደሆነ በመጥቀስም ይህም ከህዝቡ ጎን እቆማለሁ ከሚለው ተፃራሪ መሆኑን ያመላከተ እንደሆነም ተጠቅሷል።
ከዚህም በተጨማሪ እስካሁን ድረስ ስድስት የኤርትራ ስደተኞች መገደላቸውን ጠቁመው በስደተኞች ላይ ህወሃት ዘርፈ ሰፊ ጥቃቶችን እየፈፀመ እንደሆነም ቃለ አቀባይዋ ተናግረዋል።
ከዚህም ውስጥ በአስገዳጅ ሁኔታ ለህወሃት ኃይሎች ገንዘብ ማዋጣትን ጨምሮ ወዳልታወቀ ቦታዎች መውሰድ ስደተኞቹ ከሚደርስባቸው መካከል እንደሆነም በዚሁ አጋጣሚ ገልፀዋል።
ህወሓት በበኩሉ በክልሉ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችን በመተለከተ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ላይ በትግራይ ያሉ ስደተኞች መፈናቀል እና ተፈጽመዋል የተባሉ ጥቃቶች እጅጉን አሳስቦኛል ብሎ ነበር።
በዚሁ መግለጫ በተባበሩት መንግሥታት የሚመራ ገለልተኛ አካል በሲቪል ሰዎች እና በስደተኞቹ ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ በደሎችን እንዲያጣራ ጠይቋል።
ህወሓት የትግራይ ሕዝብ እና መንግሥት ለዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞችን ተቀብሎ ሲያኖር መቆየቱን ገልጾ፤ በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት "በወራሪ ኃይሎች ጉዳት የደረሰባቸውን ስደተኞችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነን" ብሏል።
ከስምንት ወራት በፊት በትግራይ የተከሰተው ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች የተዛመተ ሲሆን 2 ሚሊዮን የሚሆን ነዋሪ ከክልሉ የተፈናቀለ ሲሆን 400 ሺህ የሚሆኑ ደግሞ ለረሃብ መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት መግለጹ ይታወሳል።
በአፋር ክልልም ከሰሞኑ በተነሳው ግጭት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል።
መንግሥትም ሆነ ህወሓት ግጭቶች እንዲባባሱ አድርገዋል በማለት እየተወነጃጀሉ ይገኛሉ።
የፌደራል መንግሥቱና ህወሓት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች ተገድለዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ወታደሮቹን ከመዲናዋ መቀለ እንዳስወጣ የገለፀ ሲሆን፤ ህወሓት በበኩሉ መቀለንና ሌሎች የትግራይ ግዛቶችን እንደተቆጣጠረ ተናግሯል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በኩል ኢትዮጵያ የተኩስ አቁሙን ለማወጅ የወሰነችበት ሁኔታም መገለፁ የሚታወስ ነው።
ከዚህም መካከል አብዛኛዎቹ የህወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች በመገደላቸውና በመታሰራቸው እንዲሁም የቀሩትን ጥቂት የህወሓት አመራሮች ለመያዝ ሲባል ጦርነቱን መቀጠል አስፈላጊ ባለመሆኑ ነው ተብሏል።
በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች የግብርና ወቅታቸውን እንዳይስተጓጎል፣ የረድዔት ድርጅቶች የበርካቶችን ህይወት እንዲያድኑ እድል ለመስጠት እንዲሁም የግጭቱ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የትግራይ ሕዝብ ሰላም የሚያስፈልገው በመሆኑ እና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ከጠቀሷቸው ምክንያቶች ናቸው።
ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።












