ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተዋጊ የአሜሪካ ወታደሮች በታህሳስ መጨረሻ ኢራቅን ለቀው ይወጣሉ ተባለ
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ወታደሮች በኢራቅ የሚያካሂዱትን የውጊያ ተልእኮ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ላይ እንደሚያጠናቅቁ፤ ነገር ግን የኢራቅ ወታደሮችን በማሰልጠን እና በማማከር እንደሚቆዩ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ይፋ ያደረጉት ከኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጣፋ አል ካዲኢሚ ጋር በነጩ ቤተ መንግስት ውይይት ካካሄዱ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።
በአሁኑ ሰአት ከ2 ሺ 500 በላይ የአሜሪካ ወታደሮች በኢራቅ የሚገኙ ሲሆን ዋነኛ ስራቸውም በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የአይኤስ አባላትን ለሚዋጉ ወታደሮች ድጋፍ መስጠት ነው።
የኢራኑ ትልቅ ጀነራል ቃሲም ሶሊማኒ እና በኢራን የሚደገፈው ሺያ ሙስሊም ሚሊያ መሪ በዋና ከተማዋ ባግዳድ በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ በኢራቅ የአሜሪካ ወታደሮች መኖር በአካባቢው ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል።
ምንም እንኳን የሱኒ ጂሃዳዊ ቡድኖች ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉና ስጋት እየፈጠሩ ቢሆንም ከኢራን ጋር ቁርኝት ያላቸው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ቁልፍ ሰዎች አሜሪካ አይኤስ ለመዋጋት በሚል ያስገባቻቸውን ወታደሮች እንድታስወጣ ጫና ሲያደርጉ ነበር።
በሌላ በኩል የሺያ ሚሊሻዎች የአሜሪካና ጥምር ወታደራዊ ኃይሎች በፍጥነት እንዲወጡ ለማድረግ በካምፖቻቸው ላይ የሮኬት፣ ሞርታር እና ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት እያደረሱ ነው በሚል ተወንጅለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በቀድሞው ፕሬዝደንት ጆርጅ ቡሽ አስተዳደር የተጀመሩ ሁለት ጦርነቶችን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም እየሰሩ ነው። ከአፍጋኒስታን ቀጥሎ ይሄኛው ሁለተኛው ነው።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በነጩ ቤተ መንግስት የኢራቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ባነጋገሩበት ወቅት ''በኢራቅ የሚገኘው የጸረ ሽብር ትብብራችን ወደ አዲስ ምእራፍ እየተሸጋገርንም ቢሆን ይቀጥላል'' ብለዋል።
የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው ''ዛሬ ላይ ግንኙነታችን ከምን ጊዜውም በበለጠ ጠንካራ ነው። ትብብራችን ለኢኮኖሚው፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ባህል እና ሌሎችም ድረስ ነው'' ካሉ በኋላ በአገራቸው የውጭ ወታደሮች መኖር እንደሌለባቸውም አስረድተዋል።
በአሜሪካ የሚመሩ ወታደሮች በአውሮፓውያኑ 2003 የወቅቱን ፕሬዝዳንት ሳዳም ሁሴን ከስልጣን ለማባረር በሚል ነበር ኢራቅን የወረሩት።
በወቅቱም ሳዳም ሁሴን ሚሊየኖችን ሊያጠፋ የሚጥችል ከባድ መሳሪያ እያበለጸጉ ነው በሚል ነበር ወረራው የተካሄደው። ነገር ግን ከወረራው በኋላ ምንም አይነት መሰል መሳሪያ ሊገኝ አልቻለም።
ከጊዜ በኋላ በአውሮፓውያኑ 2011 ላይ የአሜሪካ ወታደሮች ለቅቀው ወጥተው ነበር። ነገር ግን የኢራቅ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ከሶስት ዓመት በኋላ ሽምቅ ተዋጊዎችን ለመፋለም ተመልሰው ገብተዋል።
2017 ላይ የአይኤስ ተዋጊዎች በጦርነት ቢሸነፍም የአሜሪካ ወታደሮች ግን ቡድኑ ተመልሶ እንዳያንሰራራ እና የኢራቅን መንግሥት ለመደገፍ በሚል እዛው እንዲቀሩ ተደርጓል።