ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ሆነው ተሾሙ

ከእስር የተፈቱት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ሆነው ተሾሙ።

የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በማህበራዊ ትስስር ገፁ በዛሬው ዕለት ባወጣው መረጃ የክልሉ ርዕሰ መስታድር አገኘሁ ተሻገር ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞን የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ አድርገው መሾማቸውን ነው።

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥትና ከአማራ ክልል ባለስልጣናት ግድያ ጋር ተያይዞ አንደኛው ተጠርጣሪ ነበሩ።

ከሰኔ 15 ክስተት በፊት የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ የነበሩ ሲሆን የነ ዶክተር አምባቸውና ሌሎች ባለስልጣናት ግድያ ጋር ተያይዞም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱ ይታወሳል።

ብርጋዴር ጄኔራሉ ከተጠረጠሩበት ክስም ነጻ ሆነው ከወራት እስር በኋላ ተፈትተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪም ለሌሎች ጄኔራሎችና ከፍተኛ የጦር መኮንኖችም ልዩ ልዩ የፀጥታ ተቋማትን እንዲመሩ መመደባቸውም ተጠቁሟል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በተጨማሪ ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ልዩ ረዳት ሆነው መሾማቸውን ዘግቧል።

ጄኔራል አዳምነህ የትግራይ ጦርነት እስከተከሰተበት ወቅት የመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥ ነበሩ።

ርዕሰ መስተዳደሩ የክልሉን ጸጥታ መዋቅር ለማጠናከር ከብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ እና ከጄነራል አዳምነህ መንግሥቴ በተጨማሪ ሌሎች ሰባት ሰዎችን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ መሾማቸው ተገልጿል።