ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኖርድ ስትሪም 2፡ አሜሪካና ጀርመን በአወዛጋቢው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ላይ ከስምምነት ደረሱ
አሜሪካ አወዛጋቢው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦን በተመለከተ ከጀርመን ጋር ስምምነት ላይ የደረሰችው ሩሲያ በአውሮፓ ላይ ኖርድ ስትሪም 2 ከተባለው የነዳጅ ማስተላለፊያ የምታገኘውን የፖለቲካ ትርፍ ለመከልከል ነው ብላለች።
አሜሪካ ኖርድ ስትሪም 2 የተሰኘው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ሩሲያ በአውሮፓ አገሮች ላይ ተጽዕኖዋ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት አላት።
በመጠናቀቅ ላይ ያለውና በባልቲክ ባህር ሥር የሚያልፈው ይህ ቱቦ 1 ሺህ 230 ኪሎሜትር ርዝመት አለው።
የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦው ሩሲያ ለጀርመን የምታቀርበውን ነዳጅ በእጥፍ ያሳድገዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣን ቪክቶሪያ ኑላንድ " በጣም መጥፎ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ነው፤ ነገር ግን ስምምነቱ ሩሲያ ዩክሬንን ለማስፈራራት ከሞከረች ከሞከረች፤ በሞስኮ ላይ የታሰበውን ማዕቀብ ለመጣል ያስችላል" ብለዋል።
የነዳጅ ቱቦ ማስተላለፊያ የሆነችው ዩክሬን በበኩሏ ኖርድ ስትሪም 2 የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ የአገር ውስጥ ደህንነቴ ስጋት ሆኗል ብላለች።
አገሪቷ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በምስራቅ ከሚኖሩና በሩሲያ ከሚደገፉ ተገንጣዮች ጋር እየታገለች ነው።
ሩሲያም በ2014 የክሬሚያን ሰርጥ ከዩክሬን ወስዳለች። ዩክሬን ኖርድ ስትሪም 2 አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሩሲያ ወረራ ታደርግብኛለች የሚል ስጋት አላት።
ዩክሬን በጋዝ ማስተላለፊያ ክፍያ በዓመት የምታገኘውን 3 ቢሊየን ዶላርም ታጣለች።
ፖላንድም በባልቲክ ባህር ሥር ከሩሲያ ቪይቦርግ ተነስቶ ጀርመን ሉብሚን የሚደርሰውን ማስተላለፊያ ቱቦውን ትቃወማለች።
ፖላንድ ይህ በ10 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው ፕሮጀክት የመካከለኛውና ምስራቅ አውሮፓ ደህንነት ስጋት ነው ብላለች።
ሩሲያ ግን ፕሮጀክቱ ሁሉንም የሚሳተፉ አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ስትል ስጋቱን አልተቀበለችውም።
በአሜሪካና በጀርመን ስምምነት መሠረት ዩክሬን በአረንጓዴ የኃይል ቴክኖሎጂ 50 ሚሊየን ዶላር ታገኛለች። እስከ 2024 ድረስም የነዳጅ ማስተላለፊያ ክፍያ ዋስትና እንደምታገኝ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ግንቦት ወር ላይ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን አስተዳደር፤ ከሪፐብሊካን ሕግ አውጭዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ቱቦውን እየገነባ ባለው ድርጅት ላይ ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ አንስቷል።
ኖርድ ስትሪም ፕሮጀክት 2 እየተባለ የሚጠራውን ይህንን ግንባታ እየመራ የሚገኘው የቭላድሚር ፑቲን አጋር እንደሆነ የሚነገርለት ተቋም ነው።
የባይደን አስተዳደር ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጉዳዩን ለኮንግረንስ ካቀረበ በኋላ ነበር።
የማዕቀቡን መነሳት በሚያትተው የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጫ ላይ፤ የነዳጅ መስመሩን ሲገነባ በቆየው ተቋምና ዋና ሥራ አስጻሚው ላይ የተጣለው ማዕቀብ ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ሲባል መነሳቱን መግለፁ ይታወሳል።
ኖርድ ስትሪም 2 ልክ አሁን አገልግሎት እየሰጠ እንዳለው ትዊን ኖርድ ስትሪም በዓመት 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ የመያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡