ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታዋቂው የአይስክሬም ኩባንያ በእስራኤል በተያዙ የፍልስጥኤም ግዛቶች ሸያጭ ሊያቆም ነው
ታዋቂው የአይስክሬም ኩባንያ 'ቤን ኤንድ ጄሪ' በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባሉት የፍልስጥኤም ግዛቶች ዌስት ባንክና ምስራቅ ኢየሩሳሌም ሽያጭ ሊያቆም መሆኑን አስታውቋል።
ኩባንያው እንዳለው 'የቤን ኤንድ ጄሪ' አይስክሬም በተያዙ የፍልስጥኤም ግዛቶች ውስጥ መሸጥ ማለት ከእሴቶቻችን ጋር የማይጣጣም ነው" ብሏል።
ዌስት ባንክ እና ምስራቅ ኢየሩሳሌም ከአውሮፓውያኑ 1967 ጀምሮ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ናቸው።
አይስክሬም ሰሪው ኩባንያው እርምጃው የ "ደንበኞች እና የታመኑ አጋሮች" ስጋቶች ምላሽ ነው ብሏል።
ኩባንያው በትዊተር እና ኢንስታግራም ገጾች ባጋራው መግለጫ የተሰጠው ፈቃድ በዓመቱ መጨረሻ ጊዜው እንዲያልፍ በማድረግና ለማደስ ፈቃደኛ አይደለሁም ብሏል።
ነገር ግን ኩባንያው ምርቶቹ እንዲሸጡ የማይፈልጋቸው ቦታዎች መድረስ እንዴት እንደሚያቆም ይፋ አላደረገም።
ቤን እና ጄሪ ለምን ይህንን ውሳኔ በአሁኑ ወቅት እንዳሳለፈ ማብራሪያ ባይሰጥም ለአመታት ግን ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጫና ገጥሞታል።
ኩባንያው በእስራኤል ውስጥ አንድ ፋብሪካ ያለው ሲሆን "ፋብሪካችን ከእስራኤል ጋር የረዥም ጊዜ አጋርነት አለው። በመላው አገሪቱም እያሰራጨን እንገኛለን" ብሏል።
ነገር ግን በመጪው አመት ፋብሪካው የተሰጠውን ፈቃድ እንደማያድሱ አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በካትሲርና በደቡባዊ ቴልአቪቪቭም የአይስክሬም መሸጫ መደብሮች አሉት።
በእስራኤል ከዚህ በኋላ በምን ሁኔታ ይሸጣል የሚለውንም ዝርዝር እናሳውቃለን ብሏል ኩባንያው።
ሆኖም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ውሳኔውን በመንቀፍ ቤን እና ጄሪ "ከሞራል አንፃር የተሳሳተ ነው" ብለዋል።
እስራኤል ላይ የሚደረገው ማዕቀብ በዲሞክራሲ ስም የሚደረግ ሽብር ነው። ማዕቀቡ አይሰራም፤ ሊሰራም አይችልም። በምንችለው ሁሉ እንታገለዋለን" ብለዋል
እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 ጦርነት በተቆጣጠረቻቸው የፍልስጥኤም ግዛቶች፤ ከ 440 ሺህ በላይ የሚሆኑ የእስራኤል ሰፋሪዎች በዌስት ባንክ ውስጥ ወደ 3 ሚሊዮን ከሚጠጉ ፍልስጤማውያን መካከል ይኖራሉ።
ፍልስጥኤማውያን እነዚህ ግዛቶች የመጪዋ ፍልስጥኤም አገር ሆና መመስረት ማዕከል ናቸው ይላሉ።አብዛኛዎቹ ሀገሮች እስራኤል በፍልስጥኤም መሬት ላይ መስፍሯን እንደ ህገ-ወጥ ይቆጥሩታል። እስራኤል ይህንን አትቀበለውም።