የሲሚንቶ ግብይት መመሪያ ተነስቶ ወደ ነፃ ገበያ አሰራር እንዲገባ ተወሰነ

በሲሚንቶ ግብይት ላይ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታትና፣ የዋጋ ንረት እንዳይከሰትና የተረጋጋ የሲሚንቶ ግብይት እንዲኖር ለማድረግ በሚል ወጥቶ የነበረው የሲሚንቶ ግብይት መመሪያ ላልተወሰነ ጊዜ መነሳቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

መንግሥት የሲሚንቶ አቅርቦት እና ግብይት መመሪያን ማውጣቱን ተከትሎ ከፌደራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ በገበያው ላይ የዋጋ ቁጥጥር ሥራን እንዲሁም ያለውን ተደራሽነት ክትትል ይሰራ ነበር።

ከረቡዕ ሐምሌ 7/2013 ዓ.ም ጀምሮ የወጣው መመሪያና ከዚያ ጋር ተያይዘው የወጡ የሰርኩላር ማስፈጸሚያ ደብዳቤዎች እንዲነሱና ወደ ቀደመው የግብይት ሥርዓት፣ የነፃ የገበያ አስራር እንዲመለስ ተወስኗል ተብሏል።

የሲሚንቶ ግብይትን በተመለከተ ከዚህ በፊት መንግሥት ከፌደራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ያለውን የተደራሽነትና የዋጋ ቁጥጥር ተቋርጦ ፋብሪካዎች ራሳቸውና በሰንሰለቱ የሚገኙ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎችን በመቆጣጠር ራሳቸው ማስፈፀም እንደሚችሉ ከፋብሪካ ባለቤቶችና ሥራ አስኪያጆች ጋር ስምምነት መደረሱም ተገልጿል።

የፋብሪካዎች የምርት መሸጫ ዋጋ ከሚኒስቴሩ ጋር በመተባበር በተጠና መልክ እንዲሆን ስምምነት ላይ መደረሱ ተነግሯል።

"ፋብሪካዎች የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋቸውን ከመሥሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገር በተጠናና ባልተጋነነ ዋጋ እንዲወስኑና እንዲያቀርቡ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን ሙሉ ኃላፊቱን ለፋብሪካዎችና በተለያየ ደረጃ ላይ ላሉ የንግድ አካላት እየተቆጣጠሩ እንዲያሰሩ ተወስኗል" ብለዋል በሚኒስቴሩ የንግድ እቃዎች ዋጋ ጥናት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት።

ቀድሞ በነበረው የግብይት ሥርዓት እንዲሆን የተወሰነበትንም ምክንያትም አቶ ካሳሁን አስረድተዋል።

በክረምት ወቅት የግንባታ ሁኔታ ዝቅተኛ ስለሚሆን የሲሚንቶ ፍላጎትም ማነስ ስለሚከሰት፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ሲሚንቶ ባልተጋነነ ዋጋ ለመሸጥ በመስማማታቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፋብሪካዎች የበኩላቸውን ቁጥጥር ከደንበኞቻቸው ጋር እንደሚያደርጉ ስምምነት ላይ በመደረሱ እንዲሁም በአቅርቦትና በፍላጎት ያለውን ክፍተት ለመሸፈን በአገር ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎችን አቅም አሁን ካለው በበለጠ በማጠናከር ምርታቸውን እንዲጨምሩ በማድረግና በተለይም እንደ አስፈላጊነቱ ከውጭ ተጨማሪ የሲሚንቶ ምርት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መንግሥት በመወሰኑ ነው።

መመሪያው ከነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የነበረ ሲሆን የአምራች፣ የአስመጪ፣ የአከፋፋይ፣ የቸርቻሪ ግዴታዎችን የያዘ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የተከለከሉ ተግባራትንም በዝርዝር አስቀምጧል።

የሲሚንቶ አምራቾች ያለበቂ ምክንያት ከእቅድ በታች ማምረት፣ ከመደበኛው የግበይት ሰንሰለት ውጪ የሲሚንቶ ምርትን ማከፋፈል፣ አከፋፋይ ለአከፋፋይ እና ለቸርቻሪ የሚደረግ የጎንዮሽ ግብይትን ይከለክል ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ማድረግ፣ የሲሚንቶ ምርትን መደበቅ፣ ማከማቸት እና በሕገ ወጥ መንገድ ማዘዋር፣ በዝምድና የሚከናወን የሲሚንቶ ንግድንም ይከለክልም ነበር።

ከዚህ ቀደም መንግሥት ካስቀመጠው የሲሚንቶ የዋጋ ተመን በላይ የሚሸጡ አከፋፋዮች እንዲሁም ምርት በመደበቅ፣ በማከማቸት፣ አየር በአየር በመሸጥ፣ ከንግድ አድራሻ ውጪ በመሸጥ፣ እንዲያከፋፍሉ ወይም እንዲሸጡ ከተፈቀደላቸው ውጪ ለሌላ አካል በመሸጥ የተገኙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደተወሰደ ይታወሳል።