የዓሳ ጥሬ ሥጋ እንደ በሬ ቁርጥ የሚቸበቸብባት ሐዋሳ

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የዓሳ ጥሬ ስጋ ፍቅር በሐዋሳ

መስፍንና ኃይለእየሱስ ገና ፀሐይ ጡንቻዋን ሳታሳይ ነው ወደ ሐዋሳ ሐይቅ ዓሳ ለመገገብ የሚመጡት።

ሊመገቡ የመጡት ዓሳ ለብለብ አይደለም፤ ጥብስ ወይም ዱላትም አያሰኛቸውም፤ በጠዋቱ አጥንታቸውን በዓሳ ሾርባ ሊያጠነክሩ ነው የመጡት ብለው ከገመቱም ተሳስተዋል።

መስፍንና ኃይሌ የጥሬ ዓሳ ወዳጆች ናቸው።

በተለይ መስፍን "የበሬ ስጋ ለምኔ" ከሚሉት መካከል ነው። ኃይሌን በጥሬ ዓሳ ሥጋ ፍቅር ያስጠመደውም እሱ ነው።

ወደ ሐይቁ ዞረው ከተደረደሩት ሱቆች ጀርባ አንድ ዓሳ አስጋሪ በንጋት ካጠመዳቸው ለጋ አሳዎች መካከል ለጥሬ ሥጋ ይሆናሉ ያላቸውን መልምሎ ለጉርሻ እያመቻቸ ነው።

ጓደኛሞቹ ደግሞ ደረታቸውን ለሐይቁ ሰጥተው ማዕዱን በጉጉት ይጠባበቃሉ።

ጥሬው የዓሳ ሥጋ በመልክ በመልኩ ተሰድሮ በሚጥሚጣና በደረቅ የበቆሎ ቂጣ ታጅቦ መጣ። እጃቸውን ታጥበው በተጠንቀቅ ሲጠብቁ የነበሩት መስፍንና ኃይለእየሱስ ወደ ማዕዱ ተሰማሩ።

የዓሳ ጥሬ ሥጋ መብላት ለሐዋሳ ሰው ብርቁ አይደለም። በተለይ ከሐይቁ በትኩሱ የተጠመደ 'ፍሬሽ' ዓሳ ከተገኘ ፈላጊው ብዙ ነው።

በርካታ ወጣቶችም ይህን ገበያ ተገን አድርገው ቀጥኖ በረዘመ እንጨት ጫፍ ላይ የዓሳ ማጥመጂያ ሰክተው በንጋት ከሐይቁ ዳርቻ ተቀምጠው ሲያጠምዱ ይታያሉ።

መስፍን "የዓሳ ጥሬ ሥጋ መብላት ከጀመርኩ ዓመት ከምናምን ሆነኝ" ይላል።

"ይጣፍጣል?"

"ከምነግርህ በላይ! እኔ ምን የመሰለ የበሬ ቁርጥ ልጋብዝህ ከምትለኝ የዓሳ ጥሬ ሥጋ ብትለኝ በጣም ደስ ይለኛል። ጣዕሙ ልዩ ነው።"

ለጥሬ ሥጋ የሚቀርቡት ብዙዎቹ ዓሳዎች የዕድገት ዑደታቸውን የጨረሱ አይመስሉም። ተፈላጊነታቸው የሚጨምረውም እንዲህ ዕንጭጭ ሲሆኑ ነው።

የአሳ ጥሬ ስጋ

ዓሳ አስጋሪዎች ዓሳዎቹን በአንድ ገመድ አጣምረው አምጥተው ከ100 እስከ 200 ብር ይሸጡታል። እርግጥ ነው ዋጋው እንደ ገዢና ሻጭ ግንኙነት ይለያያል።

"እንደው ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሬ የዓሳ ሥጋን ስትበላ ምን ተሰማህ?" ለመስፍን የሰነዘርኩት ጥያቄ።

"ለነገሩ እኔ ጥሬ ሥጋ እወድም ስለነበር ብዙም አልከበደኝም። እንደውም የዓሳ ሥጋ ልስልስ ያለና ጣዕሙ ለየት ያለ ነው" ሲል ጉርሻውን እያመቻቸ ነገረኝ።

"የመጀመሪያ ቀን ትንሽ ከብዶኝ ነበር። ከዚያ በኋላ እየጣፈጠኝ መጣ። አሁንማ ሱስ ይዞኛል። አንተም ብትቀምሰው ደስ ይለኛል [ጉርሻውን እያመቻቸ]"

የመስፍንን ትሁት ጥያቄ በፈገግታ አልፌ ወደ ኃይለእየሱስ ዞርኩኝ። ኃይሌ ጥሬ የዓሳ ሥጋ መመገብ ከጀመረ ቢሰነባብትም እንደ መስፍን ልምድ አላካበተም።

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው ኃይሌ የዓሳ ጥሬ ሥጋን ከለምድኩ ወዲህ ጠዋት ጠዋት ጊዜ ሲኖረኝ ሮጬ መምጣት ጀምሬያለሁ ይላል።

"ለሌላ ሰው ጥሬ የዓሳ ሥጋና የተጠበሰ ብታቀርብለት እጁን ወደተጠበሰው ነው የሚሰድደው። እኔ ግን ጥሬውን እመርጣለሁ።

ኃይሌ ጥሬ የዓሳ ሥጋ ለጤናም ጥቅም ስላለው ነው አብዝቼ የምወደው ባይ ነው።

"በአትክልት ከምናገኘው ቫይታሚን ይልቅ ከዓሳ የምናገኘው ይበልጣል ብዬ አስባለሁ።"

ጥሬ የዓሳ ስጋ
የምስሉ መግለጫ, ጥሬ የዓሳ ስጋ

እውን ጥሬ ዓሳ መመገብ ለጤና ጠቃሚ ነው?

ይህን ጥያቄ ይዤ 'ኒውትሪሽን ፎር ኤዱኬሽን' የተሰኘ ተቋም ወደሚሠሩት የሥነ ምግብ ባለሙያዋ ናርዶስ ወንዳፍራሽ ስልክ መታሁ።

ባለሙያዋ እርግጥ ነው ዓሳ ብዙ ስብ የሌለው ነገር ግን ብዙ ጥቅሞች ያሉት ሥጋ ነው ይላሉ።

"እርግጥ በባሕላችን ጥሬ ሥጋ መብላት የተለመደ ነው። ቢሆንም እንደ ጤና ባለሙያ ጥሬ ሥጋ መመገብ በምግብ ለሚተላፉ በሽታዎች ሊያጋልጥ እንደሚችል ማሳሰብ እንወዳለን።"

ሙያተኛዋ ያክሉና የተሻለ ማለት ቢከብድም ጥሬ የበሬ ሥጋ ከመገገብ እንደ ሳልመንና ቱና ያሉ ጥሬ የዓሳ ሥጋዎችን በመመገብ ኦሜጋ 3 የተሰኘውን ጠቃሚ ንጥረ ነገር ልናገኝ እንችላለን ይላሉ።

ነገር ግን ዓሳን በተገቢው መጠን አብስሎ መመገብ የተሻለ አማራጭ ነው ይላሉ።

ናርዶስ ጥሬ ዓሳን መመገብ ለሚወዱ ሰዎች ያላቸው አንድ ምክር ቢያንስ ከውሃ ከወጣ በኋላ ማቀዝቀዣ [ፍሪዘር] ውስጥ ትንሽ ቢቆይ የሚል ነው።

"ዓሳው ከወንዝ ወይም ከሐይቅ ከወጣ በኋላ ማቀዝቀዣ ውስጥ ቢቀመጥ ውስጡ ያሉ ባክቴሪያዎች ሊሞቱ ይችላሉ። ነገር ግን ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ዓሳ ማቀዝቀዣ ውስጥ ከሁለት ቀናት በላይ እንዳይቆይ ነው።"

የሥነ ምግብ ባለሙያዋ ዓሳ የሚሰጠውን ጥቅም ያክል በጥሬው መመገብ መዘዝ ሊኖረው ስለሚችል ነብሰ ጡር እናቶች፣ ሕፃናትና አረጋዊያን ሊመገቡት እንደማይገባ ያሰምራሉ።

መስፍንና ኃይሌ ግን ከጥሬ ዓሳ ፍቅር የሚለያቸው ያለ አይመስልም።

"ሰዎች ባክቴሪያ አለው እያሉ ይፈራሉ። ነገር ግን ባክቴሪያ የሌለበት ነገር አለ እንዴ?" ሲል ይጠይቃል ኃይሌ።