ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን የዳርፉር የጦር ወንጀል ተከሳሾችን ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አሳልፋ ለመስጠት ተስማማች
ሱዳን በዳርፉር ግዛት ውስጥ በተፈፀሙ የጦር ወንጀሎች የሚፈለጉ የቀድሞ ባለሥልጣናቷን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) አሳልፋ እንደምትሰጥ አስታወቀች።
ነገር ግን እስካሁን ድረስ ለፍርድ ቤቱ ተላልፈው ይሰጣሉ የተባሉት ግለሰቦች እነማን እንደሆኑ ስማቸውን ይፋ አላደረገችም።
ቀደም ሲልም የአገሪቱ መሪዎች በግጭቱ ወቅት በስልጣን ላይ የነበሩትን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽርን ለማስረከብ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ይህ ተግባራዊ አልሆነም።
አልበሽር እኤአ በ2019 በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተቃውሞ ሰልፎችን ካደረጉ በኋላ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ከስልጣን የተወገዱ ሲሆን አሁን በሙስና ወንጀል ተከሰው እስር ላይ ይገኛሉ።
በዳርፉር የተደረገው ጦነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ላይ ከታዩ እጅግ አስከፊ የሰብዓዊ ቀውሶች መካከል እጅግ አሰቃቂ ከሚባሉት አንዱ ነው።
በመንግሥት እና በአማፂያን መከከል እኤአ በ2003 ዳርፉር ውስጥ በተነሳው ግጭት ቢያንስ 300 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል፣ ሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ወደ ተፈናቃይ ካምፖች ገብተዋል።
ይህንን ውሳኔ ማሳካት የቻሉት ተሰናባቿ የአይሲሲ ዋና ዐቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ ሱዳንን ከጎበኙ ከሳምንታት በኋላ ነው። በጉብኝታቸውም አልበሽርን ጨምሮ 77 ተፈላጊ ግለሰቦች ለአይሲሲ ተላፈው እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
አልበሽር በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አይሲሲሰ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበባችው ሰው ናቸው።
ሌሎች በአይሲሲ ከሚፈለጉ የቀድሞ ባለሥልጣናት መካከል የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር አብዱራሂም ሙሐመድ ሁሴን እና የቀድሞው የአገር ውስጥ ሚኒስትር አህመድ ሐሩን ይገኙበታል።
የፌዴራል መንግሥት ሚኒስትር ቦታይና ዲናር ባሳፍነው ቅዳሜ እንዳሉት ካቢኔው ይህንን አሳልፎ የመስጠት ውሳኔ በሙሉ ድምፅ ያሳለፈው ሲሆን በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያለመ ነው ብለዋል።
የሱዳን መንግሥትም አማፂያን ቡድኖች የሰላም ሂደቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል።