ትግራይ ውስጥ ሦስት የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ሠራተኞች ተገደሉ

በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ባልደረባ የሆኑ ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

በህክምና አገልግሎት ላይ የተሰማራው ቡድኑ ባወጣው መግለጫ እንዳለው በሠራተኞቹ ላይ በተፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ግድያ በእጅጉ ማዘኑን ገልጿል።

ማንነታቸው ባልታወቁ ጥቃት ፈጻሚዎች የተገደሉት የእርዳታ ድርጅቱ ሠራተኞች ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ አንዷ ደግሞ የስፔን ዜግነት ያላት ናት።

የእርዳታ ሠራተኞቹ ባለፈው ሐሙስ በትግራይ ክልል ውስጥ በጉዞ ላይ እንዳሉ የነበራቸው ግንኙነት መቋረጡን የጠቀሰው ድርጅቱ ከዚያ በኋላ ነው መገደላቸው የታወቀው።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የሁለቱ ኢትዮጵያውያንና የስፔናዊቷ አስከሬን አርብ ጠዋት ይጓዙበት ከነበረው መኪና ጥቂት ሜትሮች ራቅ ብሎ መገኘቱንም የድንበር የለሽ ሐኪሞች ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

በጥቃቱ የተገደሉት የህክምና እርዳታ ድርጅቱ ባልደረቦች በየካቲት ወር ላይ በድርጅቱ በረዳት አስተባባሪነት ሥራ የጀመረው የ31 ዓመቱ ዮሐንስ ሃለፎም፣ በግንቦት ወር ለግብረ ሰናይ ድርጅቱንመሥራት የጀመረው የ31 ዓመቱ ሹፌር ቴድሮስ ገብረ ማሪያም እና ለዓመታት የድንገተኛ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪዋ የ34 ዓመቷ ስፔናዊት ማሪያ ኽርናንዴዝ ናቸው።

የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ግድያውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ "ይህንን ዘግናኝ ጥቃት በተመለከተ የተሰማንን ሐዘን፣ ድንጋጤና ቁጣ በትክክል የሚገልጹ ቃላት የለንም" በማለት በባልደረባቸው ሞት ጥልቅ ሐዘን ውስጥ መሆኑን ገልጿል።

መግለጫው ጨምሮም "ዮሐንስ፣ ቴድሮስና ማሪያ ትግራይ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ድጋፍ እየሰጡ የነበሩ ሠራተኞች ሲሆኑ፤ በዚህ ሥራቸው ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው" ብሏል።

በሦስቱ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ግድያውን ማን እንደፈጸመ አስካሁን ከገለልተኛ ወገን የተሰጠ ማረጋገጫ የለም።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግድያውን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ የተሰማውን ሐዘን ገልጾ፤ ጥቃቱ የተፈጸመው አቢ አዲ ተብሎ በሚጠራ "ህወሓት በሚንቀሳቀስበት አካባቢ" መሆኑን አመልክቷል።

ጨምሮም እንዲህ አይነቱን "ኃላፊነት በማይሰማው ቡድን የሚፈጸምን ጥቃት ለማስቀረት የእርዳታ ድርጅቶች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ወታደራዊ እጀባ እንዲደረግላቸው መንግሥት ያቀረበው ጥሪ ትክክል መሆኑን ያመለክታል" ብሏል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት በመደገፍና በማቋቋም እንዲሁም የህክምና ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች እርዳታን እያደረገ ያለ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።

ከጥቅምት ወር ማብቂያ ጀምሮ በተቀሰቀሰውና ላለፉት ስምት ወራት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶችና በተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲከሰሱ ቆይተዋል።

በዚህ ሳምንት በክልሉ ውስጥ ከባድ ውጊያ እየተደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በሳምንቱ መጀመሪያ አካባቢ በተፈጸመ አየር ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች እንደተጎዱ ሪፖርቶች ቢያመለክቱም መንግሥት ግን ኢላማው አማጺያኑ እንደሆኑ ገልጿል።