ምርጫ 2013፡ ምርጫው ውስንነቶች ቢኖሩትም ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ መካሄዱን የአፍሪካ ህብረት ገለፀ

ሰኞ ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም የተካሄደውን የኢትዮጵያ 6ኛ አገራዊ ምርጫ የታዘበው የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን ውስንነቶች ቢኖርትም ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ ተካሂዷል አለ።
የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን የምርጫውን አካሄድ ከታዘበ በኋላ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን አውጥቷል።
በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ማጠቃለያ ሃሳብ ላይ ሕብረቱ የተካሄደው ምርጫ የሎጂስቲክ እና የደህንነት እጥረቶች፣ የፖለቲካ ፈተና እና የኮቪድ-19 ጥንቃቄ ጉድለቶች ውጪ ቅድመ ምርጫው እና የድምጽ መስጫ ዕለት የተከናወኑት ተግባራት ስርዓት ባለው፣ ሰላማዊ እና ተዓማኒነት በሆነ ሁኔታ ተከናውነዋል ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣን ተቀብሎ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢ ቡድኑን በቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ይመራል።
ታዛቢ ቡድኑ በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ የምርጫ ትዝብቶቹን፣ ምክረ ሃሳቡን እና ማጠቃለያ ሃሳቡን አጋርቷል።
የአፍሪካ ሕብረት ምን ታዘበ?
የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ በምርጫው 46 የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን አስታውሶ በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በምርጫ ለለመሳተፍ መወሰኑ በክልሉ በርካታ ቦታዎች ውድድር ያልታስተዋለባቸው አድርጎታል ብሏል።
ከድምጽ መስጫ ቀን በፊት የነበረው የምረጡኝ ቅስቀሳ በተወሰነ መጠን የፖለቲካ ፓርቲዎች በጸጥታ ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ቢገታም በአመዛኙ ሰላማዊ ነበር ብሏል።
ምርጫ ታዛቢ ቡድኑ በምርጫው የሴቶች ተሳትፎን በተመለከተ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገበው ጠቅላላ ቁጥር 45.7 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብሏል።
በምርጫ ጣቢያዎች ከሚመደቡት አምስት የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች መካከል በአማካይ ሁለቱ ሴቶች መሆናቸውን ታዝቤያለሁ ብሏል የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢ ቡድን በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ።
የኢትዮጵያን 6ኛ አገራዊ ምርጫ ላይ በአብዛኛው አሉታዊ ተጽእኖ ካሳደሩት መካከል ትልቁን ስፍራ የሚይዘው የጸጥታው ጉዳይ እንደሆነም ሕብረቱ አስፍሯል።
በምርጫ ዝግጅት ወቅት በአማራ እና ኦሮሚያ የሚገኙ በርካታ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤቶች እንዲወድሙ መደረጉ ጥቃቱ በተፈጸመባቸው ቦታዎች የምርጫው ሂደት ላይ አሉታዊ ተጸእኖ ማሳደሩንም ጠቁሟል።
የጸጥታ ስጋት ያለባቸው ስፍራዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጉዳዩን የተቆጣጠሩበት መንገድ የሚደነቅ ነው ያለው ታዛቢ ቡድኑ፤ የተወሰደው እርምጃ በአብዛኛው ቦታ የምርጫ ዕለት ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አግዟል ብሏል።
የምርጫ ቀን ትዝብቶች
የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን ታዛቢዎቹን ወደ አምስት ክልሎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች መላኩን አስታውቋል።
ታዛቢ ቡድኑ በተሰማሩባቸው ስፍራዎች ምርጫ ጣቢያዎች ሲከፈቱ፣ የድምጽ አሰጣጥ፣ ምርጫ ጣቢያዎች ሲዘገቤ እና ድምጽ ሲቆጠር ታዝበዋል።
የሕብረቱ ምርጫ ታዛቢ ቡድን 22 ምርጫ ጣቢያዎች ሲከፈቱ መታዘቡን ገልጾ ከእነዚህ መካከል 13 የሚሆኑት በጊዜ አልተከፈቱም።
ምርጫ ጣቢያዎች በጊዜ ሳይከፈቱ የቀሩት የምርጫ ታዛቢዎች እና ቁሳቁሶች መዘግየት እንዲሁም ለምርጫ ቀን የተደረገው ደካማ ቅድመ ዝግጅት ዋና ዋና ምክንያት እንደሆኑም አስቀምጧል።
የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እጥረት ተከስቶ ነበር ያለው ሕብረቱ ሆኖም የድምጽ መስጫ ሳጥኖች በትክክል ታሽገው እንደነበርም ታዛቢዎቹን ዋቢ አድርጎ አስፍሯል።
ድምጽ አሰጣጥ
ቡድኑ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን በ249 ምርጫ ጣቢያዎች መታዘቡን አመልክቷል።
ቡድኑ ከታዘባቸው ምርጫ ጣቢያዎች 79.9 በመቶ በሚሆኑት ረዣዥም ሰልፎች ሪፖርት ተደርገዋል ያለ ሲሆን የድምጽ አሰጣጡ በአመዛኙ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እንደተከናወነም ጠቅሷል።
ሕብረቱ ተዘዋውሮ ከተመለከታቸው ምርጫ ጣቢያዎች 86.4 በመቶ የሚሆኑት ለአካል ጉዳተኞች እና አቅመ ደካሞች በቀላሉ ገብተው ድምጽ መስጠት የሚችሉባቸው ነው ብሏል።
የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢዎች በጋምቤላ ክልል የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች እጥረት በማጋጠሙ የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱ ተቋርጧል ሲል በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ላይ አመላክቷል።
የድምጽ ቆጠራ
የሕብረቱ ታዛቢ ቡድን በ18 ምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ አሰጣጥ እና የድምጽ ቆጠራ ታዝቧል። ምርጫ ቦርድ የድምጽ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ እንዲቀጥል ከወሰኑ በኋላ ድምጽ ሰጪዎች እስከ እኩለ ለሊት ድረስ ድምጽ ሲሰጡ እንደነበረም በሪፖርቱ አካቷል።
የኮቪድ-19 ጥንቃቄ
የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን በአጠቃላይ የኮቪድ-19 በሽታ ስርጭት ለመከላከል አካላዊ እርቀት መመሪያ አልተከበረም ብሏል።












