ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያውያን የደመቁበት የቶኪዮ ኦሎምፒክ ማጣሪያ
በኔዘርላንድስ ሄንግሎ በተካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ማጣሪያ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልኡካን ቡድን እሁድ ምሽት ወደ ውድድር ስፍራው ተጉዞ ውድድሮችን አካሂዷል።
በዚህ በሄንግሎ በተካሄደው የማጣሪያ ውድድር በቶኪዮ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከ800 ሜትር እስከ 10 ሺህ ሜትር እንዲሁም 3000 ሜትር መሰናክልን ጨምሮ በአምስት ውድድሮች በሁለቱም ፆታ አገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶች በውጤታቸው መሰረት ተሰላፊዎቹና ተጠባባቂዎቹ ይለያሉ፡፡
በዚህም መሰረት በ10 ሺ ሜትር የሴቶች ማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ከሁለት ቀናት በፊት በሲፋን ሀሰን ተሰብሮ የነበረውን የ10 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር አሸናፊ መሆን ችላለች።
ለተንሰበት ውድድሩን በ29 ዲቂቃ ከ1.03 ሰከንድ በመግባት አጠናቃለች።
ለተንሰንበትን ተከትላ ሁለተኛ የወጣችውን ፅጌ ገብረሰላማን ደግሞ ከአንድ ደቂቃ በላይ በሆነ ሰዓት ነው ቀድማ ውድድሯን የጨረሰችው።
በአጠቃላይ ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ቦታ የያዙት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ጸሀይ ገመቹ ሶስተኛ፣ የዓለምዘርፍ የኋላው አራተኛ እንዲሁም ቦሰና ሙላቴ አምስተኛ ሆነው ማጠናቀቅ ችለዋል።
ከስድስተኛና ስምንተኛ ደረጃዎች ውጪ ደግሞ እስከ 14ኛ ደረጃዎችን አሁንም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደያዙት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን መረጃ ያሳያል።
በወንዶች 10ሺህ ሜትር ማጣሪያ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ የያዙ ሲሆን አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ26 ደቂቃ 49 ሰከንድ ከ51 ማይክሮሰከንድ በሆነ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችሏል።
እሱን በመከተል ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ሀጎስ ገብረህይወት ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
በሴቶች 5 ሺ ሜትር ማጣሪያም ቢሆን የኢትዮጵያውያን የበላይነት የታየበት ነበር። ከአንድ እስከ ስምንተኛ ያሉትን ደረጃዎች ኢትዮጵያውን የተቆጣጠሩት ሲሆን አትሌት ጉድፍ ጸጋዬ ውድድሩን በ14 ደቂቃ 13 ሰከንድ 32 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰአት በአንደኝነት ጨርሳለች።
እሷን በመከተል አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ሁለተኛ እንዲሁም አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል። ፋንቱ ወርቁ፣ መስከረም ማሞ፣ ፋንታዬ በላይነህ፣ ሀዊ ፈይሳ እና ሚዛን ዓለም ደግሞ እስከ ስምነተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
በወንዶች 5 ሺ ሜትር ማጣሪያ አትሌት ጌትነት ዋለ ውድድሩን በ12 ደቂቃ 53 ሰከንድ 28 ማይክሮ ሰከንድ አሸናፊ ሆኗል። ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃም ቢሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተቆጣጥረውታል።
በዚህም መሰረት ንብረት መላከ፣ ሚልኬሳ መገሻ፣ ሙክታር ድሪስ፣ ያሲን እና ሰለሞን በሪሁ ከሁለት እስከ ስድስት ያሉትን ቦታዎች ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።
በሴቶች 800 ሜትር በተካሄደው ማጣሪያም ቢሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሰባተኛ ያሉትን ቦታዎች ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።
በዚህም አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው ውድድሩን በ2 ደቂቃ ከ20 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰአት ጨርሳለች።
ከሁለተኛ ጀምሮ ቀጣዮቹን ደረጃዎች የያዙት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደግሞ ሀብታም ዓለሙ፣ ወርቅነሽ መሰለ፣ ነጻነት ደስታ፣ ማህሌት ሙሉጌታ፣ አያል ዳኛቸው እና ቅሳነት ዓለም ናቸው።
በወንዶች 800 ሜትር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ቦታ ይዘው ነው ያጠናቀቁት።
የሞሮኮው ኤልሀሳኔ ሙጃሂድ አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን አትሌት ባጫ ዋርካ ደግሞ የሁለተኛ ደራጃውን ይዞ ጨርሷል። ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ተማም ቱራ፣ አዲሱ ግርማ እና ኤፍሬም መኮንን ከሶስት እስከ ስድስት ያለውን ቦታ ይዘዋል።
በሴቶች 1500 ሜትር አሁንም የበላይነታቸውን በማሳየት ከአንድ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ውድድሩን በ3 ደቂቃ 57 ሰኮንድ ከ33 ማይክሮ ሰከንድ በማስመዝገብ ያሸነፈች ሲሆን ድርቤ ወልተጂ፣ ለምለም ኃይሉ፣ ትእግስት ከተማ እና ሂሩት መሸሻ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።
በወንዶች 1500 ሜትር ማጣሪያ ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ ያሉት ቦታዎች ኡንም በኢትዮጵያውያን ተይዘዋል።
ውድድሩን አትሌት ታደሰ ለሚ በ3 ደቂቃ 31 ሰከንድ 90 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰአት ያጠናቀቀ ሲሆን የአገሩ ልጆች ሳሜኤል አባቴ፣ ሳሙኤል ተፈራ እና መለሰ ንብረት እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በሴቶች 3 ሺ ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ውድደርም ቢሆን ኢትዮጵያውያን ከአራተኛው ደረጃ በስተቀር ከአንድ እስከ ስምንት ያሉትን ቦታዎች ይዘው ጨርሰዋል።
አትሌት መቅደስ አበበ በ9 ደቂቃ 13 ሰከንድ ከ63 ማይክሮ ሰከንድ ውድድሩን ያሸነፈችበት ሰአት ነው።
አትሌት ሎሚ ሙለታ ደግሞ ሁለተኛ ስትሆን አትሌት አገሬ በላቸው ሶስተኛ ሆና ጨርሳለች።
የኡጋንዳዋ አትሌት ፔሩዝ ቼሙታይ አራተኛ ሆና ያጠናቀቀች ሲሆን ቀሪዎቹን ደረጃዎች ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ ብርቱካን አዳሙ፣ ብርሀን ገብረጊዮርጊስ፣ አስማረች ነጋ እንዲሁም ወይንሸት አንሳ ይዘውታል።
በወንዶች 3 ሺ ሜትር መሰናክል ማጣሪያም ኢትዮጵያውያን የበላይነት በመውሰድ ከአንድ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይው ማጠናቀቅ ችለዋል።
በዚህም መሰረት አትሌት ቢቂላ ታደስ ውድድሩን በ8 ደቂቃ 09 ሰከንድ ከ37 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰአት ማሸነፍ ችሏል።
በመቀጠል ደግሞ አብራሀም ስሜ፣ ኃይለማርያም አማረ፣ ሳሙኤል ፍሬው እና ተገኑ መንግስቱ ከሁለት እስከ አምስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በማጣሪያው ተሳትፈው ጥሩ ሰአት ያስመዘገቡ አትሌቶችን በአምስቱም ውድድሮች ይፋ ያደርጋል።
ኮሚቴው አትሌቶቹ ያስመዘገቡትን ሰአት፣ ወቅታዊ ብቃት እንዲሁም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የመቋቋም ብቃታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከነተጠባባቂ እስከ አራት የሚደርሱ አትሌቶችን በቅርቡ ምናልባትም በዚህ ሳምንት ይፋ ሊያደርግ እንደሚችል ይጠበቃል።