ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊው 'የልጄን አመድ ፖሊስ በትኖታል' ሲል ከሰሰ
አሜሪካዊው ግለሰብ የልጁ አመድ ያለበትን ማሰሮ የመሰለች ማስቀመጫ ፖሊስ በሕገ ወጥ መንገድ ወስዷል በማለት ከሷል።
ሜት የተባለው አደንዛዥ ዕፅ አለበትና እመረምራለሁ በሚል "ፖሊስ የልጄን አመድ በትኖታል" ይላል ለፍርድ ቤት የቀረበው ክስ።
ዳርታቪየስ ባርነስ የተባለው ግለሰብ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ሲያውለው የሚያሳየው ቪዲዮ ወጥቷል። ቪዲዮው እንደሚያሳየው ግለሰቡ ታስሮ ፖሊሶች ከመኪናው ውስጥ የልጁ አመድ ያለበትን እቃ ሲወስዱ ያሳያል።
ዳርታቪየስ ፖሊስንም የልጁን አመድ "አበላሽተውታል፤ አቆሽሸውታል" ሲልም ከሷል።
አመዱ የሁለት አመት ህፃን ልጁ ስትሆን የሞተችውም ከሁለት አመታት በፊት ነበር።
የፍርድ ቤት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፖሊስ ምንም ስህተት አልሰራሁም ይላል።
ዳርታቪየስ ፖሊስን ብቻ ሳይሆን የከተማዋንም አስተዳዳሪዎች ከሷል። የልጁን አመድ በሕገወጥ መንገድ መውሰዳቸው ብቻ ሳይሆን እቃውን ከፍተው የተወሰነ አመድ መሬት ላይ በትነዋል እንዲሁም አደንዛዥ ዕፅ እንመረምራለን በሚልም ውርደት ፈፅመዋል ብሏል።
ልጁ ታንጃ ከሁለት አመት በፊት ሕይወቷ ያለፈው በረሃብና እንክብካቤ በማጣት ነበር። እናቷ ትዋንካ ዴቪስ ልጇን ገድላለች በሚል ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆና ስላገኛት የ20 አመት እስር ፈርዶባታል።
ባለፈው አመት ዳርታቪየሰስ በፍጥነት መኪና በመንዳትና የትራፊክ ሕጎችን በመጣስ ነበር ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለው።
ቪዲዮው ላይ እንደሚታየው ፖሊሶች ከመኪናው ጀርባ አድርገው ሲያስሩትም ሆነ ሲፈትሹት ተባባሪ ነበር። ፖሊሶች መኪናውን ከመፈተሻቸው በፊት መኪናው ውስጥ ያለውን ነገር ሲጠይቁት ዕፀ ፋርስ እንዳለ ተናግሯል።
መኪናው ውስጥም 80 ግራም ዕፀ ፋርስ የተገኘ ሲሆን ይህም በግዛቲቱ ከሚፈቀደው ሦስት እጥፍ ነው።
በመቀጠልም ፖሊሶቹ የልጁ አመድ ያለበትን እቃ ያሳዩት ሲሆን "ሜት ወይም ኤክስታሲ የሚባሉ አደንዛዥ ዕፅ አለበት" አሉት።
"በጭራሽ፣ በጭራሽ አይደለም፤ ወንድሜ ልጄ ናት" በማለት በብስጭት የጮኸ ሲሆን " ያንን መልስልኝ። ልጄ ናት። ልጄን እባክህ መልስልኝ! እጄ ላይ አድርግልኝ። እያዋረዳችኋት ነው እባካችሁ ወንድሞቼ!" ሲልም ተማፅኗል።