ኮሮናቫይረስ፡ በሕንድ ኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ300ሺህ አለፈ

ከኮቪድ-19 ተህዋሲ ጋር በተያያዘ በሕንድ የሟቾች ቁጥር በድምሩ ከ300ሺህ ማለፉን መንግሥት ይፋ አደረገ።

የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው ይህ አሐዝ በቅርብ ወራት ውስጥ በአያሌው ሊጨምር እንደሚችል ይተነብያሉ።

ይህም ብቻ ሳይሆን የሟቾች ቁጥር መንግሥት ይፋ ካደረገውና በቅጡ ካመነው በበለጠ እንዲያውም በሦስት እጥፍ እንደሚሆን ግምት ሰጥተዋል።

በሕንድ በተህዋሲው በድምሩ 300ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ መሆኑ ይፋ ሲደረግ፤ በተህዋሲው የተያዙ ሰዎች ደግሞ 26 ሚሊዮን እንደሆኑም ተመላክቷል።

ይህም አሐዝ ሕንድን ከአሜሪካ ቀጥሎ በዓለም ብዙ ዜጎቿ በተህዋሲው በመያዝ ብልጫ ያላት 2ኛዋ ትልቅ አገር ያደርጋታል።

በሟቾች ብዛትም ከሄድን ሕንድ በዓለም ከአሜሪካና ብራዚል ቀጥላ በርካታ ዜጎቿን በተህዋሲው ያጣች 3ኛዋ አገር ናት።

የሚገርመው ሕንድ ከ100ሺህ ሰዎች ሞት ወደ 300ሺህ ዜጎች ሞት የተሸጋገረችው አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ መሆኑ ነው።

ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ በሕንድ የተከሰተው ባለፉት ሳምንታት ሲሆን ተህዋሲው እጅግ በሚያስደነግደጥ ፍጥነት የብዙዎቹን ሕንዳዊያንን ቤት አንኳኩቶ የ200ሺህ ዜጎችን ሕይወት ነጥቋል።

ሆስፒታሎች በህሙማን መጨናነቃቸው ሳያንስ የሟቾችን አስከሬን ለማስወገድ እንኳ ፈተና ሆኖ በወንዞች ዳርቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ አስክሬኖች መገኘታቸው ዓለምን ያነጋገረ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል።

የአስክሬን ማቃጠያ ቦታዎች እጥረት በመከሰቱም ጊዜያዊ የአስክሬን ማቃጠያ ድንኳኖችን በፓርኮች ውስጥ መትከል አስገድዶ ነበር።

በሕንድ ድህነት ክንዱን ባበረታባቸው ገጠራማ ቀበሌዎች የሞት ምዝገባ የሚታወቅም የሚታሰብም ጉዳይ አይደለም።

ይህን እውነታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕንድ በተህዋሲው የሞቱት ሰዎች ቁጥር መንግሥት ካመነው በብዙ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል።

አንዳንድ የሟቾችን ቁጥር በሌሎች ዘዴዎች ግምት ለማግኘት የሞከሩ ባለሙያዎች እንደሚሉት በሕንድ በኮቪድ-19 ምክንያት ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሰው ሳይሞት አልቀረም።