ከእስራኤል ጦር ጋር የሚፋለመው ሃማስ ማነው?

ሃማስ ጋዛን የሚያስተዳድር የፍልስጥኤም የሚሊሻ ቡድን ነው። ከበርካታ የፍልስጥኤም ሚሊሻ ቡድንም ትልቁ ሃማስ ነው።

መጠሪያውን ያገኘው ከመጀመሪያ 'ኢንቲፋዳ' በኋላ ነው። እአአ 1987 ላይ ፍልስጥኤማውያን የእስራኤልን በዌስት ባንክና ጋዛ ሰርጥ ሰፈራ ተቃውመው የመጀመሪያውን ኢንቲፋዳ ቀሰቀሱ።

ሃማስ በመቋቋሚያው ቻርተር ላይ "ለእስራኤል መውደም ሳልታክት እሰራለሁ" የሚል አንቀፅ አስፍሯል።

ሃማስ ሲመሰርት ሁለት ዓላማዎች ነበሩት። አንደኛው በጦር ክንፉ እስራኤል መውጋት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ኢዘዲን አል-ቃስም በሚሰኘው ማዕቀፉ ለፍልስጤማውን ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት ነው።

እአአ 2005 ላይ እስራኤል ጦሯን እና ሰፋሪዎቿን ከጋዛ ስታስወጣ፤ ሃማስ በፍልስጤም ፖለቲካ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ጀመረ። ከአንድ ዓመት በኋላ በተካሄደ ምርጫም ሰፊ ድምጽ ማግኘት ችሎ ነበር።

የሃማስ ተዋጊዎች ከእስራኤል ጋር ሦስት ጦርነቶችን ተዋግተዋል። የሃማስ የጦር ክንፍ በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና በዩናይትድ ኪንግደም አሸባሪ ቡድን ተብሎ ተፈርጇል።

የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ጥቃቶች

እአአ 1990 መጀመሪያዎች ላይ በርካታ ፍልስጥኤማውያንን በሚወክለው የፍልስጥኤማውያን ነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) እና በእስራኤል መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አልቀበልም ካለ በኋላ ሃማስ ተጽእኖ ፈጣሪነቱ እየጨመረ መጣ።

ሃማስ በሚያደርሳቸው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃቶች በርካታ እስራኤላውያንን ገድሏል።

እአአ 1995 የሃማስ ቦምብ ሰሪ የነበረው ያሃያ አይሻ መገደልን ተከትሎ ሃማስ በወሰደው የአጸፋ እርምጃ አጥፍቶ ጠፊዎች ከ60 በላይ እስራኤላውያንን ገድለው ነበር።

በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል ሰላም ለማውረድ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል።

በኦስሎ ሁለቱ አካላት የደረሱት ስምምነት፤ ሃማስ በሚያደርሳቸው ተደጋጋሚ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃቶች እስራኤል በስምምነቱ እንዳትገዛ ሲያደርጓት ቆይተዋል።

የወቅቱ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተንም የሁለቱን ኃይሎች መሪዎች አሜሪካ አስጠርተው ቢመክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ሃማስና የእስራኤል ጦር ሁለተኛው ኢንቲፋዳ ተብሎ ወደ ሚጠራው ግጭት ገቡ። ይህ ግጭት እአአ ከ2000 እስከ 2005 የዘለቀ ነው።

በዚህ የግጭት ወቅት ሃማስ ዝነኝነቱ እየጨመረ ሄደ። ውጤታማ ያልሆነው የፍልስጤም አስተዳደር ለሕዝቡ ማድረስ ያቀታውን መሠረተ ልማት ሃማስ ለሕዝቡን ማድረግ ቻለ።

እአአ 2004 ላይ የሃማስ መሪ ሼክ አሕመድ ያሲን እና መሪውን ይተካሉ ተብለው የነሩት አብዱል አዚዝ በእስራኤል የሚሳኤል ጥቃት ጋዛ ውስጥ ተገደሉ። በተመሳሳይ ዓመት የፒኤልኦ መሪ ያሲር አረፋት አረፉ። በዚህ መካከል የአሁኑ ሞሐሙድ አባስ የፍልስጤም መሪ ሆነው ብቅ አሉ።

የሃማስ ቻርተር

የሃማስ የ1988 ቻርተር የፍልስጤም ግዛት አሁን እስራኤል ያለችበት ቦታን እንደሚያጠቃልል ያትታል። መሬቱ የእስላም ምድር ነው ከአይሁድ አገር ጋርም ምንም አይነት ሰላም ሊኖር አይችልም ይላል።

በእስራኤል ወታደሮችና በፍልስጤም ታጣቂዎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በሁለቱም ወገኖች በኩል ሞትና በርካታ ጉዳቶችን ያስከተለ ሲሆን በቀላሉ ላይበርድ የሚችልበትም ዕድል ከፍተኛ ነው።

እስራኤል በጣም ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ አቅም ያላት አገር ናት፤ የአየር ኃይሏም ቢሆን በዓለም ተወዳዳሪ ነው።

ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የተለያዩ መረጃ መሰብሰቢያ መንገዶችን በመጠቀም እስራኤል ቀላል የማይባሉ የጋዛ አካባቢዎችን አጥቅታለች።

ነገር ግን ጥቃቱን የፈጸምኩባቸው አካባቢዎችና ህንጻዎች ሃማስ እና እስላማዊ አክራሪዎች የሚጠቀሙባቸው ስለሆኑ ነው እንጂ ንጹሀን ዜጎችን ኢላማ አላደረኩም ትላለች እስራኤል።

ምንም እንኳን ሃማስ እና ኢስላማዊ ጂሃድ ቡድኖች ከእስራኤል ወታደራዊ አቅም አንጻር ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸውቢሆንም እስራኤልን ለማጥቃት ግን በቂ መሳሪያዎች አሏቸው። እስካሁንም የተለያዩ ጥቃቶች ሰንዝረዋል።

የእስራኤል ወታደሮች በቅርቡ መሳሪያ የታጠቀ ሰው አልባ አውሮፕላን ከጋዛ ወደ እስራኤል ለመግባት ሲሞክር ተኩሰው ጥለዋል።

አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ ደግሞ ‘’ከፍተኛ ስልጠና የወሰዱ የሀማስ አባላት የውስጥ ለውስጥ ቱቦዎችን በመጠቀም ወደ ደቡባዊ እስራኤል ለመግባት መሞከራቸውን ገልጸዋል። ቀድሞ መረጃ የደረሰው የእስራኤል መከላከያም ወደ እስራኤል ከመድረሳቸው በፊት መንገዳቸውን አፈንድተውባቸዋል።

ነገር ግን ፍልስጤማውያን ከታጠቋቸው መሳሪያዎች መካከል በርካታ ዓይነቶች ያሉት ከመሬት ወደ መሬት የሚተኮስ ሚሳኤል በጣም ወሳኙ ነው። አብዛኛዎቹም በግብጽ በኩል በሲናይ በረሃ በተቆፈሩ ጉድጓዶች በኩል በድብቅ የገቡ ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛዎቹ ሀማስ እና ኢስላማዊ ጂሃዲስቶች የሚጠቀሟቸው ዘመናዊና ረቀቅ ያሉ መሳሪያዎች የሚመረቱት እዛው የጋዛ ሰርጥ ውስጥ በሚገኙ ሚስጥራዊ ቦታዎች ነው።

እስራኤልና ሌሎች የውጭ ምንጮች ደግሞ እነዚህ መሳሪያዎች የሚመረቱት በኢራን ድጋፍ እንደሆነ ያምናሉ። በዚህም ምክንያት ነው እስራኤል መሳሪያዎቹ ይመረቱበታል ብላ የምታስባቸውን አካባቢዎች በአየር ድብደባ ጥቃት እየፈጸመች የምትገኘው።

በሀማስ በኩል ያለው የመሳሪያ ክምችት ምን ያክል እንደሆነ እስካሁን አይታወቅም። ነገር ግን ሃማስ የተለያየ አይነት ጥቅምና አቅም ያላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የጦር መሳሪያዎች እንዳሉት ይታመናል።

እስራኤል እነዚህ መሳሪያዎች ምን ያክል እንደሆኑና የጉዳት መጠናቸውን ምን ያክል እንደሆን መረጃ እንዳላት ቢታመንም በይፋ ግን ለመግለጽ ፈቃደኛ አይደለችም።

የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይም ቢሆኑ ቁጥሩ ምን ያክል እንደሆነ ባይገልጹም ሀማስ ለረጅም ጊዜ መሰል መሳሪያዎችን በመጠቀም ጥቃቶችን የመሰንዘር አቅም እንዳለውገልጸዋል።

ፍልስጤማውያን በአሁኑ ሰአት የተለያዩ አይነት ሚሳኤሎችን ጥቅም ላይ እያዋሉ ነው። ነገር ግን እስካሁን ድረስ በጣም በተራቀቀ መንገድ የተሰሩ መሳሪያዎችን መጠቀም አልቻሉም። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሚሳኤሎቹ ረጅም ርቀት እንዲጓዙና ከፍተኛ ፍንዳታ መፍጠር የሚችሉበት አሰራር ላይ ትኩረት አድርገዋል።

ምንም እንኳን የእያንዳንዱ ሮኬትና ሚሳኤል አሰራር የተለያየና ግራ የሚያጋባ ቢሆንም ሃማስ በርካታ መሳሪያዎች ግን አሉት።

ለምሳሌም የአጭር ርቀት ተምዘግዛጊው ‘ቃሳም’ አንዱ ሲሆን እስከ 10 ኪሎሜትር ድረስ ብቻ ነው መጓዝ የሚችለው። ‘ቁድስ 101’ የሚባለው 16 ኪሎሜትር ድረስ ተጉዞ ጉዳት ማድረስ የሚችል ሲሆን ‘ሴጂል 55’ የሚባለውደግሞ እስከ 55 ኪሎሜትሮች መጓዝ ይችላል።

ነገር ግን ሀማስ ከዚህም በላይ ርቀት መጓዝ የሚችሉና ዘመናዊ ሚሳኤሎችን ይጠቀማል። ከነዚህ መካከል እስከ 75 ኪሎሜትር ድረስ መጓዝ የሚችለው ‘ኤም-75 አንደኛው ሲሆን ‘ፋጂር’ ደግሞ እስከ 100 ኪሎሜትሮች ተምዘግዝጎ መሄድ ይችላል። ሌላኛው ‘አር-160’ እስከ 120 ኪሎሜትር መጓዝ የሚችል ሲሆን ‘ኤም-320’ የሚባለው ደግሞ እስከ 200 ኪሎሜትር ድረስ ተጉዞ ጉዳት ማድረስ የሚችል ዘመናዊ መሳሪያ ነው።

የእስራኤል መከላከያ እንደሚለው ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ ከ1 ሺ በላይ ሮኬቶች ከፍልስጤም ወደ እስራኤል የተተኮሱ ሲሆን ከነዚህ መካከል ደግሞ 200 የሚሆኑት ያረፉት እዛው ጋዛ ውስጥ ነው። ምናልባትም እዛው ፍልስጤም ውስጥ የሚሰሩት ሮኬቶችና ሚሳኤሎች ውጤታማነታቸው ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

መከላከያ ኃይሉ አክሎም ከፍልስጤም በኩል ከተተኮሱት ሚሳኤሎች መካካል 90 በመቶ የሚሆኑት በእስራኤል ጸረ-ሚሳኤል መሳሪያዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል ብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2014 ላይ ባጋጠመ ተመሳሳይ ግጭት እስራኤል በወሰደችው እርምጃ እስከ 2251 ፍልስጤማውያን ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ከነዚህ መካከል 1462 ንጹሀን ዜጎች ናቸው። በእስራኤል በኩል ደግሞ 67 ወታደሮች የተገዱ ሲሆን ስድስት ንጹሀን ዜጎችም ሕይወታቸው አልፏል።