በኮሎራዶ አንድ ግለሰብ ፍቅረኛውን ጨምሮ ስድስት ሰዎችን ተኩሶ ገደለ

በአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት አንድ የታጠቀ ግለሰብ ትላንት እሁድ በተካሄድ የልደት ድግስ ላይ ስድስት ሰዎችን ከገደለ በኋላ ራሱን አጠፋ።

"ከሟቾቹ መሃል የገዳዩ የፍቅር ጓደኛ ትገኝበታለች። መጀመሪያ እያሽከረከረ ወደ ቦታው መጣ። ራሱን ከማጥፋቱ በፊት በልደት ዝግጅቱ ላይ እየታደሙ የነበሩ ሰዎች ላይ በዘፈቀደ ተኩስ ከፈተ" ሲል የኮሮሎራዶ ስፕሪንግ ፖሊስ ገልጿል።

ገዳዩ ይህንን ድርጊት ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

የጥቃቱ ሰለባዎች በሙሉ አዋቂዎች ቢሆኑም በድግሱ ላይ ግን ህፃናትም ታድመው ነበር። ፖሊስ የሟቾች ማንነትን እስከ አሁን ድረስ ይፋ አላደረገም።

"በድግሱ ላይ ህጻናት ታድመው የነበረ ቢሆንም ከመሃላቸው ማንም አልተጎዳም። ነገር ግን በዚህ አሰቃቂ ተግባር የስድስት ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል" ሲሉ አንድ የአካባቢው ፖሊስ ገልፀዋል።

ፖሊስ የድረሱልኝ የሰልክ ጥሪ ሲደርሰው ወደ ቦታው ቢያመራም የስድስት ሰዎች ህይወት ካለፈ በኋላ መድረሱ ታውቋል። እንዲሁም አንድ ሰው ከባድ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ ህይወቱ አልፏል።

የከተማዋ ከንቲባ ድርጊቱን "ትርጉም አልባ ጥቃት" ሲሉ ገልፀውታል። "ዛሬ ስለሞቱት ሰዎች በከባድ ሃዘን ውስጥ ሆነን እንዲሁም ቤተሰባቸውን ላጡ እና ጉዳት ለደረሰባቸው እየፀለይን እንገኛለን" ሲሉ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ግዛት ቡልደር ከተማ ከሁለት ወራት በፊት የ10 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ጥቃት በአንድ መደብር ውስጥ ተፈጽሞ ነበር። ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ውሎ በ 10 የግድያ ወንጀሎች ተከሷል።