የ118 ዓመቷ ጃፓናዊት ኮቪድን ለሌሎች እንዳይስተላልፉ በመስጋር ከኦሊምፒክ ችቦ ቅብብል ራሳቸውን አግልለዋል

ምድራችን ላይ ብዙ ዓመታት በመኖር ወደር ያልተገኘላቸው ጃፓናዊት ኮቪድን ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፉ በመስጋት በኦሊምፒክ መድረክ ተገኝቼ ችቦ አላበራም ብለዋል።

ካኔ ታናካ የ118 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው። የሚኖሩት ደግሞ የአዛውንቶች ማቆያ ውስጥ ነው።

ታናካ በደቡብ ጃፓን ፉኮካ ተገኝተው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ችቦን መቀበል ነበረባቸው። ነገር ግን በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደማይሳተፉ አሳውቀዋል።

ባለፈው መጋቢት የጀመረው የችቦ ቅብብል ግን በኮሮናቫይረስ ምክንያት እክል ገጥሞታል። ከቅብብሉ ጋር ግንኘነት አላቸው የተባሉ 8 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

ባለፈው ወር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደ አዲስ ያገረሸባት ጃፓን እንደ ቶኪዮና ኦሳካ ባሉ ዋና ዋና ከተሞች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላለች።

በችቦ ቅብብሉ መሳተፍ የነበረባቸው በርካታ ታዋቂ ሰዎችም በኮቪድ-19 ምክንያት ይቅርብን ብለዋል።

በፈረንጆቹ 1903 የተወለዱት ታናካ የዓለም ድንቃድንቅ ጉዳየችን በሚመዘግበው ጊነስ ዎርልድ ሬከርድስ የዓለማችን በዕድሜ ትልቋ ሴት ተብለው ተመዝግበዋል።

የሚኖሩበት የአዛውንቶች ማቆያ ያሉ ሰዎች እንዳሉት የታናካ ቤተሰቦች ለውድድሩ አዘጋጆች ስለጉዳዩ በኢሜይል አሳውቀዋል።

"ከችቦ ቅብብሉ መውጣት የፈለጉት ኮሮናቫይረስ ይዘው መጥተው በማቆያው እንዳያሰራጩት በመስጋት ነው" ብለዋል።

ጃፓን በቶኪዮ፣ ኦሳካ. ኪዮቶ እንዲሁም ሂዮጎ ከተሞች የአስቸኳይ ጊዜ ጥላለች። አዋጁ ከአምስት ቀናት በኋላ በፈረንጆቹ ግንቦት 11 ሊነሳ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

ነገር ግን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም እያሰበ ነው ሲሉ ዘግበዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመጪው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል የሚለው እስካሁን ግልፅ አይደለም።

በፈረንጆቹ 2020 ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞለት በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአንድ ዓመት የተራዘው ቶኪዮ 2020 በቀጣይ ሐምሌ ይጀምራል።