ሳይንስ ፡ ጃፓን ከእንጨት ሳተላይት እየሠራች ነው

አንድ የጃፓን የቴክኖሎጂ ኩባንያ እና ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ በዓለማችን ታሪክ የመጀመሪያው ይሆናል ብለው ያሰቡትን ከእንጨት ብቻ የተሠራ ሳተላይት በአውሮፓውያኑ 2023 ለማምረት አቅደዋል።

ሱሚቶሞ የተባለው በዛፎች ላይ የሚሠራው ድርጅት ከምድር ውጪ ዛፎች እንዴት ባለ ሁኔታ እንደሚበቅሉ እና ምን እንደሚያስፈልጋቸው ለማወቅ ከወዲሁ ምርምር እያደረገ እንደሆነ አስታውቋል።

ይህ ድርጅት እና ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ በጥምረት በሚያካሂዱት ምርምር በመጀመሪያ የተለያዩ የዛፍ አይነቶችን በዓለማችን ላይ በሚገኙ እጅግ አስቸጋሪ ቦታዎች ላይ በመትከል ሙከራቸውን ይጀምራሉ ተብሏል።

የመንኮራኩሮችና ሳተላይቶች ስብርባሪ ሕዋ እያጨናነቀው የሚገኝ ሲሆን፤ አገራት በየዓመቱ የሚልኳቸው መንኮራኩሮች ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።

ከእንጨት የሚሠሩት ሳተላይቶች ግን ምንም አይነት ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ወደ ከባቢ አየር ሳይለቁ ከምድር ለቀው ከወጡ በኋላ የሚፈለግባቸውን ተግባር ፈጽመው ተቃጥለው ይጠፋሉ። ወደ ምድር የሚመለስም ሆነ ሕዋ ላይ የሚቀር ስብርባሪ አይኖርም ማለት ነው።

''ወደ ምድር የሚመለሰው የመንኮራኩር ክፍል አንዳንድ አካላቱ አየር ላይ ይቃጠላሉ። ይህ ደግሞ ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ወደ አየር እንዲገቡ ያደርጋል። በጣም አሳሳቢ ነገር ነው፤ በቀላሉ የሚታይ አይደለም'' ይላሉ በኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የሕዋ ሳይንስ ተመራማሪው ታካዎ ዶዪ።

''በአጭር ጊዜ ባይሆንም በጊዜ ብዛት ከፍተኛ ጉዳት አለው። ቀጣዩ ስራችን የሚሆነው የሳተላይቱን አጠቃላይ ገጽታ በንድፈ ሀሳብ ማስቀመጥ ነው። በመቀጠል ለሙከራ የሚሆን ሳተላይት እንሠራለን'' ሲሉ አክለዋል ታካዎ ዶዪ።

ሱሚቶሞ የተባለው በዛፎች ላይ የሚሰራው ድርጅት የአየር ጸባይን መቋቋምና ከፍተኛ የጸሀይ ሙቀትን ተቋቁመው ማደግ የሚችሉ የዛፍ ዝርያዎችን ለመለየትና ለማሳደግ እየሠራ እንደሆነ አስታውቋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች በሕዋ ላይ እየተንሳፈፉ የሚገኙ የሳተላይት ስብርባሪዎች ምናልባት የሆነ ወቅት ላይ ወደ ምድር መውደቅ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ።

በአሁኑ ሰአት የተለያዩ ሳተላይቶች ለቴሌኮሚዩኒኬሽን፣ ቴሌቪዥን፣ አሰሳ እና የአየር ጸባይ ትንበያ ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ይህ ተከትሎ የሚመጣው ስብርባሪ ግን አስካሁን መፍትሄ አልተገኘለትም።

በምድር አናት ላይ የሚሽከረከሩ 6 ሺ አካባቢ ሳተላይቶች እንደሚገኙ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ያወጣው መረጃ ያሳያል። ከነዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አገልግሎታቸውን የጨረሱ ናቸው።

ዩሮኮንሳልት የተባለው የምርምር ተቋም እንደሚለው፤ በየዓመቱ 990 አካባቢ ሳተላይቶች ወደ ሕዋ የሚላኩ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2028 15 ሺ ሳተላይቶች እንደሚኖሩ ይገመታል።

የታዋቂው ሀብታም ኤለን መስክ ኩባንያ የሆነው ስፔስ ኤክስ ብቻውን 900 ሳተላይቶችን አምጥቋል። በሚቀጥሉት ዓመታት ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሳተላይቶችን ለማምጠቅ እቅድ አለው።