ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጆ ባይደን የአርመን ጅምላ ግድያ የዘር ጭፍጨፋ ነበር አሉ
ጆ ባይደን በአርመኖች ላይ በአውሮፓውያኑ 1915 የተፈፀመው የጅምላ ግድያ የዘር ጭፍጨፋ መሆኑን ተናገሩ።
ይህንን በይፋ በማለትም የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል።
የጅምላ ግድያው የተከሰተው በቀድሞዋ ኦቶማን ኢምፓየር ወይም የአሁኗ ቱርክ እየተዳከመች በነበረችበት ወቅት ነው።
ሁኔታው ለአመታት አወዛጋቢ ሆኖ የቆየ ሲሆን ቱርክ የጅምላ ግድያዎች ተፈፅመዋል ብላ ብታምንም "የዘር ጭፍጨፋ" የሚለውን ግን አልተቀበለችውም ነበር።
የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ በያዝነው ሳምንት ቅዳሜ እንዳሉት አገራቸው የአሜሪካን ውሳኔ "ፍፁም አትቀበለውም" ብለዋል።
"ከማንም ቢሆን ስለ ታሪካችን መማር አንፈልግም" በማለት በትዊተር ገፃቸው ሃሳባቸውን አስፍረዋል።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁ በአገሩ የሚገኙትን የአሜሪካ አምባሳደር ጠንካራ መልዕክት እንዲያስተላልፉ ጠርቷቸው ነበር።
ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሜሪካ መሪዎች የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አገሮች ድርጅት (ኔቶ) አጋር የሆነችው ቱርክ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያበላሸል በሚል ስጋት "የዘር ጭፍጨፋ" የሚለውን ቃል በይፋ ከመጠቀም ተቆጥበው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1915 ምን ተከሰተ?
ኦቶማን ቱርኮች በሩሲያ ኃይል መሸነፋቸውን ተከትሎ ለዚህ ደግሞ ክርስቲያን አርመኖችን በመወንጀል ወደ ሶሪያ በረኃና ሌሎች ቦታዎችም በአስገዳጅ በግዞት ይልኳቸው ጀመር።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርመኖችም ተጨፍጭፈዋል፣ በረሃብ ሞተዋል ወይም በምግብ እጦት እንዲሞቱ ተደርገዋል።
በወቅቱ የነበረውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ የአይን እማኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶችና የሃይማኖት ልዑካን መዝግበውታል።
የሞቱ ሰዎች ቁጥርም ምን ያህል እንደሆነ አጨቃጫቂ ሆኗል፤ አርመኖች 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል ይላሉ።
ቱርክ በኩሏ የሟቾች ቁጥር 300 ሺህ ነው ትላለች። አለም አቀፉ የዘር ጭፍጨፋ ላይ ያተኮሩ ምሁራን ማህበር በበኩሉ የተገደሉ አርመናውያን ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንደሆነ አስታውቋል።
ምንም እንኳን የቱርክ ባለስልጣናት የጅምላ ግድያዎች ተፈፅመዋል ቢሉም ክርስቲያን አርመናውያን ከምድረገፅ ለማጥፋት ሙከራም ሆነ የተዘረጋ ስርዓት አልነበረም ይላሉ።
በዚህ አንደኛው አለም አቀፍ ጦርነት ወቅት በርካታ ቱርክ ሙስሊሞችም ሞተዋል የሚሉ መከራከሪያዎችን ቱርክ ታቀርባለች።
ባይደን ምን አሉ?
አርመኖች የዘር ጭፍጨፋ መታሰቢያን በሚያከብሩበት በመጀመሪያዋ ቀን ባይደን ባወጡት መግለጫ "በኦቶማን አገዛዝ ወቅት በዘር ጭፍጨፋ የሞቱ አርመናውያንን ህይወት እናስባለን። እንዲህ አይነት ጭፍጨፋም እንዳይደገም ጠንክረን እንሰራለን" ያሉት ፕሬዚዳንቱ
አክለውም "በየትኛውም አይነት የሚመጡ ጥላቻዎችንና ሊያደርሱት የሚችለውንም ጫና ጠንቀቅ ብለን እናያለን" ብለዋል።
ጆ ባይደን ይህንን መግለጫ ሲሰጡ ለመወንጀል ወይም ጣት ለመጠቆም ሳይሆን "መቼም ቢሆን እንዳይደገም ለማድረግ ነው" ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ የአርመን ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሽንያን እንዳሉት የጆ ባይደን ቃል " ለሞቱት ክብር ሰጥቷል" በማለት በትዊተር ገፃቸው ያሰፈሩ ሲሆን አክለውም "አሜሪካ ለሰብዓዊ መብት ጥበቃና አለም አቀፋዊ እሴቶች ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው" ብለዋል።
ቱርክ በበኩሏ መግለጫውን አውግዛ ይህ የሆነው "ፅንፈኛ በሆኑ የአርመን ቡድኖችና ፀረ-ቱርክ በሆኑ አካላት ጫና ነው"ስትል ተናግራለች።
ይህም ሁኔታ የሃገራቱን ግንኙነትና ወዳጅነት እንደሚያጠለሸውም አስጠንቅቃለች።