ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በግብጽ የሞት ቅጣት በሦስት እጥፍ ሲያሻቅብ የአረብ አገራት ቀዳሚ ሆነዋል
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 2020 ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሞት ፍርድ ቅጣት ከፈፀሙ አምስት አገራት ውስጥ አራቱ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ናቸው ሲል አምነስቲ ገለፀ።
ኢራን፣ ግብጽ፣ ኢራቅ እና ሳዑዲ አረቢያ በዓመቱ ከተፈፀሙ 483 የሞት ፍርድ ጣቶች ውስጥ 88 በመቶ የሚሆነው በግዛታቸው ውስጥ መፈፀሙን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም አስታውቋል።
ተቋሙ አገራቱ የኮሮናቫይረስ ባለበት ወቅት እንዲህ ያለ ጭካኔ በዜጎቻቸው ላይ አሳይተዋል ሲልም ከሷል።
በግብጽ የታየው የ300 በመቶ የሞት ፍርድ ቅጣት ማሻቀብ ዓለም አቀፉ መሻሻል ላይ ጫና ነበረው። ግብጽ 107 ሰዎችን በሞት ፍርድ ቅጣት በመቅጣት በዓለም ሦስተኛዋ የሞት ፍርድ ቅጣትን በተደጋጋሚ የምትፈጽም አገር ሆናለች። ከዚህ ውስጥም 23ቱ ከፖለቲካ አመጽ ጋር በተያያዘ ወንጀል የተፈረደባቸው ነበሩ።
አምነስቲ ግለሰቦቹ ያለፉበት የክስ ሂት በከፍተኛ ደረጃ ኢ-ፍትሃዊ ከመሆኑም ባሻገር በሐሰት ምስክሮች እና ሌሎች ጥቃቶች ላይ የተመሰረተ ሂደትም ነበር ሲል አውግዞታል።
በተጫማሪም ከአል-አቅራብ እስር ቤትን ሰብሮ ለመውጣት የተደረገ ያልተሳካ ሙከራን ተክተሎ 57 ሰዎች መገደላቸው ለቁጥሩ መጨመር አስተዋፅኦ አድርጓል። በሙከራው በርካታ የፖሊስ ባልደረቦች እና የሞት ፍርድ እየተጠባበቁ የነበሩ እስረኞች መሞታቸው ይታወሳል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለፈው ዓመት የተመዘገበው የሞት ፍርድ ቅጣት ቁጥር በአስር ዓመት ውስጥ ዝቅተኛው ቢሆንም፣ በቻይና የተፈፀሙ የሞት ፍርድ ቅጣቶችን አላጠቃለለም።
ቻይና በዓመት በሺዎች የሚቆጠሩ የሞት ፍርድ ቅጣቶችን እንደምትፈጽም ቢታመንም ትክክለኛው የሞት ፍርድ ቅጣት ቁጥር ግን ብሔራዊ ምስጢር ተደርጎ ስለሚወሰድ ለማወቅ አዳጋች ነው።
በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚፈፀሙ የሞት ፍርድ ቅጣቶች ከ579 ነው ወደ 473 ያሽቆለቆሉት።
ለቁጥሩ መቀነስም በተለይም በሳዑዲ አረቢያ የታየው የ85 በመቶ መሻሻል ከፍተኛ ሚና የነበረው ሲሆን በአጠቃላይ ሳዑዲ በዓመት ውስጥ 27 ሰዎችን በሞት ፍርድ ቀጥታለች።
እንዲሁም በኢራቅ የ50 በመቶ ማሽቆልቆል የታየ ቢሆንም 45 የሞት ቅጣቶች ተፈፅመዋል።
ከቻይና በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኢራን በዓመቱ 246 የሞት ፍርድ ቅጣቶችን ፈፅማለች። ኢራን የዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ ሦስት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን በሞት ፍርድ ቀጥታለች።
አምነስቲ እንደገለፀው የኢራን ባለስልጣናት የሞት ፍርድን እንደ የፖለቲካ መጨቆኛ መሳሪያ እየተጠቀሙበት ነው ሲል ከሷል።
ይህም በተለይ የተቃውሞ ሰልፍ የሚወጡ ሰዎች ላይ እና የአናሳ ጎሳ አባላት ላይ ይበረታልም ሲል ገልጿል።
አምነስቲ ኳታር በአስደንጋጭ ሁኔታ ወደ ኋላ ተመልሳለች ሲልም ወቅሷል። ከ20 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ የኔፓል ዜግነት ያለው ግለሰብ ተተኩሶ መገደሉን አምሰስቲ አስታውሷል።
በሳዑዲ አረቢያ የሞት ፍርድ ቅጣት ከፍተኛ ማሽቆልቆል ያሳየ ሲሆን ይህም ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች የሞት ፍርድ ቅጣት መቋረጥ ምክንያት መሆኑን የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።
አምስቲ በበኩሉ ቁጥሩ መቀስ ትክክለኛው ምክንያት ሳዑዲ የቡድን 20 አገራት መሪ በመሆኗ ትችቶችን ለመቀነስ የታሰበ ሊሆን ይችላል ብሏል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመካከለኛው ምሥራቅ ኃላፊ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ አገራት በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራት የዜጎቻቸውን ህይወት ከገዳይ በሽታ ለመከላከል በሚረባረቡት ወቅት ያለርህራሄ የሞት ፍርድን ፈፅመዋል ሲሉ ወቅሰዋል።