ሱፐር ሊግ፡ የአውሮፓ ትልልቅ ክለቦች ለምን የራሳቸውን ሊግ መመስረት ፈለጉ?

የአውሮፓ ትልልቅ የሚባሉት ክለቦች በአዲስ መልክ የሚቋቋመውን የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመቀላለቀል ተስማምተዋል።

ይህ ውድድር ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ እና በአጠቃላይ ትልልቆቹ የዓለም እግር ኳስ ውድድሮችን የሚገዳደር ይሆናል።

ለዚህ ውድድር ትልቁ መነሻ ገንዘብ ይመስላል። የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እንደሚለው ውድድሩ ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ ይሆናል። የሚሳተፉት ቡድኖችም ቢሆኑ ጠቀም ያለ ትርፍ እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በርካታ የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ቀላል የማይባል ጫና ደርሶባቸዋል። ለቡድኖቹ የሚጫወቱት ታላላቅ ተጫዋቾችም ቢሆኑ የሚከፈላቸው ገንዘብ ከፍተኛ ነው።

''አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአውሮፓ እግር ኳስ አካሄድ በወረርሽኙ ምክንያት ክፉኛ መጎዳቱን ተከትሎ ነው ይህ አዲስ ሊግ የመመስረቱ ሀሳብ ወደፊት የመጣው'' ብለዋል 12ቱ መስራች ክለቦች ዕሁድ ዕለት ባወጡት የጋራ መግለጫ።

''አዲሱ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ለክለቦች ከፍተኛ የሆነ የገቢ ምንጭ ከማስገኘቱ በተጨማሪ በረጅም ጊዜ ለአውሮፓ እግር ኳስ እድገትም ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ይኖረዋል'' ሲል አክሏል መግለጫው።

አርሰናል፣ ቼልሲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል እና ቶተንሀም በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመሳተፍ የተስማሙ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቡድኖች ናቸው።

ከጣልያን ኤሲ ሚላን፣ ኢንተር ሚላን እና ጁቬንቱስ ለመቀላለቀል ወስነዋል። ከስፔን ደግሞ ሪያል ማድሪድ፣ ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ ይቀላቀላሉ።

የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እንደገለጸው መስራች ቡድኖቹ የሳምንቱ ግማሽ ላይ ጨዋታዎቹን ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን የአገራቸው ሊግ ጨዋታ ላይ ግን መሳተፋቸውን አያቆሙም።

አክሎም ''የመጀመሪያው የውድድር ዓመት እቅዱ ተግባራዊ መደረግ ሲችል ወዲያውኑ ይጀመራል። ሶስት ተጨማሪ ቡድኖች ደግሞ ሊጉን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል'' ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የወንዶቹ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ከተጀመረ በኋላ የሴቶች ሱፐር ሊግም እንደሚጀመር ተገልጿል።

እሁድ ዕለት የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ዜና መሰማቱን ተከትሎ የዩናይትግ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ውሳኔውን አውግዘውታል።

የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪው ፊፋ በበኩሉ ቀደም ብሎ ለመሰል ውድድሮች እውቅና እንደማይሰጥና በውድድሩ የሚሳተፉ ተጫዋቾች በዓለም ዋንጫ ላይ ላይሳተፉ እንደሚችሉ አስታውቋል።

የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ዜና ከተሰማ በኋላ ፊፋ እንደማይቀበለው አስታውቋል። ''ለእግር ኳስ ሲባል በዚህ ውሳኔ ላይ የተሳተፉት አካላት በሙል የተረጋጋ፣ ጠቃሚና ሁሉንም የሚጠቅም ውይይት ሊያደርጉ ይገባል'' ብሏል።

የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ደግሞ በመግለጫው ''ወደፊት መስራች ክለቦቹ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና ፊፋ ጋር አብሮ መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት ያደርጋሉ'' ብሏል።

ሊጉ 20 ተሳታፊ ብድኖችን የሚያካትት ሲሆን 12ቱ መስራች ክለቦች እና እስካሁን ስማቸው ያልተጠቀሰው ሶስት ክለቦች በፍጥነት ይቀላቀላሉ። ከአገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች ደግሞ አምስት ቡድኖች ተወዳድረው የአውሮፓ ሱፐር ሊግን ይቀላሉ።

በእቅዱ መሰረት የአውሮፓ ሱፐር ሊግ በየዓመቱ ነሀሴ ወር ላይ የሚካሄድ ሲሆን ጨዋታዎቹም የሳምንቱ አጋማሽ ላይ ይደረጋሉ። ተሳታፊዎቹ 20 ቡድኖችም በሁለት ምድቦች ተከፍለው በደርሶ መልስ ጨዋታ ይፋለማሉ።

በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ክለቦች አሁን በሚሳተፉባቸው ውድድሮች ከሚያገኙት ገቢ አንጻር ይሄኛው በእጅጉ የተሻለ ገቢ እንደሚያስገኝላቸው ተገልጿል። በመጀመሪያዎቹ የውድድሩ ወራትም እስከ 10 ቢሊየን ዩሮ ድረስ ሊያስገኝ ይችላል።

እንደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እና የጣልያን ሴሪ አ ያሉ የአውሮፓ ሊጎች በመላው ዓለም ከፍተኛ ተከታታይ አላቸው። አዲሱ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ደግሞ የእነዚህን ሊጎች ተወዳጅነትና ገቢ እንዳይቀንሰው ተፈርቷል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርም ቢሆን እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ በአውሮፓ ሱፐር ሊግ የሚሳተፉ ተጫዋቾች ከሁሉም የአገር ውስጥ ውድድሮች ሊታገዱ እንደሚችሉ ያስታወቀ ሲሆን በአውሮፓም ሆነ በዓለም መድረክ ከብሄራዊ ቡድን ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጿል።

ነገር ግን በዚህ ውድድር ለመሳተፍ የተስማሙት ክለቦች የቀረበላቸው ከፍተኛ የገቢ አማራጭ ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽን ጋር ተደምሮ የማይተዉት አማራጭ አድርጎባቸዋል።

መስራቾቹ ክለቦች በኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ምከንያት ለደረሰባቸው ኪሳራና ያላቸውን መሰረተ ልማት ለማሳደግ ከአውሮፓ ሱፐር ሊግ 3.5 ቢሊየን ዩሮ ያገኛሉ።

''12ቱ ክለቦች በዚህ ወሳኝ ሰአት አንድ ላይ የመጡት የአውሮፓ እግር ኳስን ለማዘመንና ለመቀየር ነው። የምንወደውን እግር ኳስ ቀጣይነት እንዲኖረውም ለማድረግ ነው'' ብለዋል የጣልያኑ ጁቬንቱስ እግር ኳስ ክለብ ኃላፊና የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ምክትል ሊቀመንበር አንድሪያ አግኔሊ።

ምንም እንኳን የእንግሊዝ፣ ጣልያን እና የስፔን ትልልቅ ክለቦች በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመሳተፍ ቢስማሙም የፈረንሳይ እና የጀርመን ክለቦች ግን እስካሁን ምንም አላሉም።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በአዲስ መልክ 36 ክለቦችን የሚያሳትፍ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድርን ዛሬ ይፋ እንደሚያደርግ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን አዲሱን ሊግ የመሰረቱት 12ቱ ክለቦችን ግን በተጀመረው የለውጥ ሂደትና ፍጥነቱ ደስተኞች አይደሉም።

የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ፕሬዝደንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ የመጀመሪያው የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ኃላፊ ሲሆኑ ''በሁሉም ደረጃ እግር ኳስን እንደግፋለን'' ብለዋል።

''እግር ኳስ በዓለማችን ላይ ከ4 ቢሊየን በላይ አፍቃሪዎቹ ያሉት የስፖርት ውድድር ነው። የዚህ ስፖርት አድናቂዎችን ፍላጎትና ምኞች ማሳካት ደግሞ የእና የትልልቆቹ ክለቦች ኃላፊነት ነው።''

የጁቬንቱሱ ኃላፊ አንድሪያ አግኔሊ ደግሞ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት እራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን አሁን ደግሞ የአውሮፓ ሱፕ ሊግ ምክትል ሆነዋል።

የማንቸስተር ዩናይትዱ ጆዌል ግሌዘር በበኩሉ '' የዓለማችንን ታላላቅ ክለቦች አንድ ላይ ማምጣትና በአንድ ሊግ ላይ እንዲወዳደሩ ማድረግ ለአውሮፓ እግር ኳስ አዲስ በር የሚከፍት ነው። በዚህ ውድድር ላይ ክለቦች የተሻለ የእግር ኳስ መሰረተ ልማት ያገኛሉ፤ መጨረሻ ላይ የሚያገኙተ ገቢም ቢሆን ጠቀም ያለ ነው'' ብለዋል።

አዲሱን የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እንደሚቀላቀሉ የሚጠበቁት የጀርመኑ ታላቅ ክለብ ባየርን ሙኒክ እና የፈረንሳዩ ፒኤስጂ በበኩላቸው እሁድ ዕለት የአውሮፓ ክለቦች ማህበር የጠራውን ድንገተኛ ስብሰባ ተሳትፈዋል።

ምን አይነት አስተያየት ተሰጠ?

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአገራቸው ክለቦች እስካሁን ምንም አለማለታቸውን በጥሩ ጎን እንደሚመለከቱትና እንደሚደግፏቸው ገልጸዋል።

የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስተር ቦሪስ ጆንሰንም ቢሆኑ በዚህ ውድድር ሀሳብ እንደማይስማሙና እግር ኳስን እንደማይጠቅም አስታውቀዋል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር፣ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር፣ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ፣ የስፔን እግር ኳስ ፌደሬሽን፣ ላ ሊጋ፣ የጣልያን እግር ኳስ ፌደሬሽን እና የጣልያን ሴሪ አ ሁሉም በአንድ ድምጽ አዲሱን ውድድር ለማስቆም በህብረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የሊቨርፑልና የቶተንሀም የቀድሞ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የነበረው ዳኒ መርፊ ከቢቢሲ ስፖርት ጋር ባደረገው ቆይታ በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ሀሳብ ደስተኛ አለመሆኑን ገልጿል።

የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ አምበል ጋሪ ኔቪል በበኩሉ በውሳኔው ''በጣም ተበሳጭቻቸለው'' ብሏል። ሌላኛው የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ ተከላካይ ሪዮ ፈርዲናንድ ደግሞ ውሳኔው በይበልጥ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችን እንደሚጎዳ ገልጿል።

የበርካታ የእንግሊዝ ክለቦች ደጋፊዎች ማህበራትም ቢሆን በውሳኔው ደስተኞች እንዳልሆኑና ቡድኖቹ ቆም ብለው እንዲያስቡበት እየጠየቁ ይገኛሉ።

አሁን ላይ ግን 12ቱ መስራች ክለቦች ከዚህ በኋላ ወደኋላ የሚሉ አይመስልም። እንደውም እርስ በርሳቸው እየተደጋገፉና በቶሎ ውድድሩን ለማስጀመር ደፋ ቀና እያሉ ነው።

በአሁኑ ሰአት በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርና የአገር ውስጥ ሊጎች የሚያደርሱባቸውን ጫና እና ተቃውሞ ተቋቁመው ይቀጥሉበት ይሆን? ቀሪዎቹ ሶስት ክለቦች እንማን ናቸው? ባየርን ቡኒክ እና ፒኤስጂ አዲሱን የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ይቀላቀሉ ይሆን?

የእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ በጉጉት የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ነገር ግን አሁን ላይ በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመሳተፍ የተስማሙት 12ቱ ክለቦች ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ግንኙነት ስራ ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ከጅምሩ የታየው ምላሽ ተስፋ ሰጪ የሚባል አይደለምና።