ፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊውን ግለሰብ በጥይት የመታው 'በስህተት ነው'

በአሜሪካዋ ሚኒሶታ ግዛት ፖሊስ አንድ ጥቁር አሜሪካዊን ክፉኛ በጥይት ከመታ በኋላ 'ክስተቱ የተፈጠረው በስህተት ነው' ብሏል።

ጥቁር አሜሪካዊው የ20 ዓመት ወጣት ዶነቴ ራይት ብሩክሊን ሴንተር በተሰኘችው ከተማ ነው በፖሊስ ጥይት ተመትቶ የሞተው።

የፖሊስ አለቃ ቲም ጋኖን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ዶንቴን በጥይት የመታችው ፖሊስ ሽጉጥ ሳይሆን ማደንዘዣ መተኮስ ነበር ዓላማዋ።

ኪም ፖተር የተባለችው ፖሊስ በብሩክሊን ሴንተር ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ለ26 ዓመታት አገልግላለች።

የዶንቴ ራይት ሞትን ተከትሎ በከተማዋ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ የሰዓት እላፊም ተጥሏል።

ሰኞ ምሽት ተቃዋሚዎች ሰዓት እላፊውን ጥሰው በብሩክሊን ሴንተር ፖሊስ ጣቢያ ዋና መሥሪያ ቤት ደጃፍ ተሰባስበው ድምፃቸውን አሰምተዋል።

የዓይን እማኞች እንዳሉት ፖሊስ ሰልፉን ለመተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙን ተከትሎ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ርችትና ጠርሙሶች ወርውረዋል።

በሌላ በኩል የብሩክሊን ሴንተር ጎረቤት የሆነችው ሚኒያፖሊስ ከተማ በፖሊስ የተገደለው ጆርጅ ፍሎይድን የፍርድ ውሎ እያስተናገደች ትገኛለች።

ተቃውሞው ወደ ሚኒያፖሊስ ከተማ እንዳይዛመት ተፈርቷል።

ዶንቴ ራይት ባለፈው እሑድ ነው የትራፊክ ሕግ ጥሰሃል ተብሎ በፖሊስ እንዲቆም የተደረገው።

ሰኞ ዕለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከፖሊሷ ካሜራ ላይ የተወሰደ ቪድዮ ለዕይታ ቀርቦ ነበር። በዚህ ቪድዮ ላይ ፖሊሶች ዶንቴን ሊያስሩት ሲሞክሩ ግለሰቡ ደግሞ ወደ መኪናው ለመመለስ ሲጥር ይታያል።

አንድ የፖሊስ መኮንን "ማደንዘዣ፣ ማደንዘዣ፣ ማደንዘዣ" የሚል ድምወፅ ታሰማለች። ይሄን ዶንቴ ወደ መኪናው ገብቶ ሲሄድ እንዲሁም ማደንዘዣ ስትል የነበረችው ፖሊስ "ተኮስኩበት" ስትል ትደመጣለች።

በጥይት ክፉኛ የተመታው ዶንቴ ራይት ጥቂት ከተጓዘ በኋላ መኪናው ተጋጭቶ ይቆማል።

የፖሊስ አለቃው ጋኖን "ፖሊሶች ማደንዘዣ ሊተኩሱበት አስበው ነው በአንድ ጥይት የመቱት ብዬ ነው የማምነው " ብለዋል።

"ሕመሙን ለማቅለል የምለው ነገር የለኝም" ሲሉ አክለዋል የከተማዋ ፖሊስ ኃላፊ።

የፖሊስ መኮንኗ ለጊዜው በግዳጅ እረፍት እንድትወጣ ተደርጋለች።

የብሩክሊን ሴንተር ከተማ ከንቲባ ማይክ ኤሊዬት በተቻለው መጠን "ለዶንቴ ራይት ፍትህ ለማምጣት" እንደሚጥር ተናግሯል።

የጥቁር አሜሪካዊው ዶንቴ ራይት ሞት ከተሰማ በኋላ ሰንበት ምሽት ከተማዋ በተቃውሞ ታምሳለች።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የዶንቴን ስም እየጠሩ በዋና ፖሊስ ጣቢያው ፊት ድምፃቸውን አሰምተዋል።

ወደ 20 ገደማ በፖሊስ ጣቢያው አቅራቢያ የሚገኙ ሱቆች ውስጥ ሰዎች ገብተው ንብረት መዝረፋቸውን ስታርትሪቢውን ጋዜጣ ዘግቧል።

ይህንን ተከትሎ የከተማዋ አስተዳዳሪዎች እሁድ ምሽቱን ሰዓት እላፊ ጥለዋል።

ጎረቤቶቹ ሚኒያፖሊስና ሴይንት ፖል ከተማ ከንቲባዎችም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግገዋል። ከምሽት አንድ ሰዓት እስከ ንጋት 12 የሚዘልቅ ሰዓት እላፊም ጥለዋል።

ጆርጅ ፍሎይድን ገድሏል ተብሎ የተከሰሰው ፖሊስ ፍርድ ሂደትን እንዲጠብቅ የተላከው ብሔራዊው ዘብ [ናሽናል ጋርድ] ወደ ብሩክሊን ሴንተር ከተማ ተልኳል።

የተለያዩ የስፖርት ጨዋታወች ተሰርዘው ወደ ሌላ ጊዜ እንዲራዘሙም ተደርጓል።

የዶንቴ ራይት እናት ኬቲ የልጇን ሞት ከሰማች በኋላ "ልቤ አንድ ሺህ ቦት ተሰባብሯል። እጅግ እናፍቀዋለሁ" ስትል ተሰምታለች።

"ሕይወቴ ነበር። ከእንግዲህ ላገኘው አልችልም" ስልት እናት ምሬቷን አሰምታለች።

"ልጄን በስህተት ልጣው?፤ ልጄን በስህተት ልጣው?"

እናት ልጇ በፖሊስ ጥይት ከመሞቱ በፊት እንደደወለላትና የመኪናው መስታወት ላይ በተጠንጠለጠለ ሽቶ ምክንያት ፖሊሶች እንዳስቆሙት እንደነገራት ተናግራለች።

ከትንሽ ቆይታ በኋላ ስደውል በመኪናው የፊት ወንበር ተቀምጣ የነበረው የፍቅር ጓደኛው ልጇ በጥይት ተመትቶ እንደሞት እንደነገረቻት እናት ታወሳለች።