የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሦስት ዓመታት ጉዞ፡ ከኖቤል ሽልማት እስከ ትግራይ ግጭት

በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭትና ተቃውሞች መበራከታቸውን ተከትሎ 'የመፍትሄው አካል ለመሆን' በሚል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን ለቀቁ።

በዚህም ምክንያት መጋቢት 24/2010 ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ተሾሙ። በተመሳሳይ ቀን ባደረጉት 35 ደቂቃ የፈጀ የመጀመሪያ ንግግራቸው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በውጪ ግንኙነት [ከኤርትራ ጋር 20 ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነት ማደስን ጨምሮና በማኅበራዊ ጉዳዮች መጠነ ሰፊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ቃል ገቡ።

በዚህ ንግግራቸው "የሃሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም" ያሉት ዐቢይ "በተለያየ ጊዜ መስዋዕትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ በቅጡ ሳይቦርቁ ህይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጉዳት ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ።" ሲሉም ተደምጠዋል።

ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ በመስጠት ህዝባችንን እንክሳለንም ሲሉ ገልጸዋል። ይህ ሁሉ ከሆነ ዛሬ ሶስት ዓመታት ተቆጠረ። እናም ያለፉትን ሶስት ዓመታት ከተለያዩ ጉዳዮች አንጻር በወፍ በረር እንቃኘው።

የሚዲያ ነጻነት እና የፖለቲካ እስረኞች

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያዎቹ የስልጣን ወራቶች በፖለቲካዊ ምክንያቶች የታሰሩ ግለሰቦች ከእስር ተፈትተዋል። ከሀገር ውጪ ነፍጥ አንግበው ሲታገሉ የነበሩና 'በአሸባሪነት' የተፈርጁ ፓርቲዎች 'ከአሸባሪነት መዝገብ ተፍቀው' ወደ ሃገር እንዲገቡ ተደርገዋል። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩን 'መልካም አደረጉ፣ አበጁ!' ያስባላቸው ነበር።

በመገናኛ ብዙሃን ነጻነትም እንዲሁ። ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ከለላ ተቋም (CPJ) እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 ባወጣው ሪፖርት ከመገናኛ ብዙሃን አንጻር በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ 'ተአምራዊ' ሲል ነበር የገለጸው። ተቋሙ ከ14 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምንም አይነት ጋዜጠኛ በእስርቤት የለም ሲል አሳውቆ ነበር።

ከ260 በላይ የታገዱ ድረ ገጾች እንደተለቀቁና ውጪ የነበሩ መገናኛ ብዙሃን ወደ አገር ቤት እንዲገቡ መደረጉን ገልጾ ይህም አበረታች እርምጃ ነው ብሎት ነበር። በተመሳሳይ ዓመት ኢትዮጵያ በዓለም የፕሬስ ነጻነት ያላትን ቦታ 40 ደርጃዎችን አሻሽላ ከ150ኛ ወደ 110ኛ ከፍ ያለችበት ነበር።

ሆኖም ነገሮች እንደመጀመሪያው የቀጠሉ አይመስልም። ወደሃገር ተመልሶ የነበረው OMN አሁን ላይ አዲስ አበባ ላይ የነበረው ቢሮው ተዘግቷል። በተለያዩ ወቅቶች ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል።

ድምበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሞጋች (Reporters without borders) አሁን ላይ በኢትዮጵያ መረጃ የማግኘት መብት ጥስት ጋር በተያያዘ በርካታ ሪፖርቶችን እየተቀበለ እንደሆነ ገልጾ ይህም ያለፉትን አስመስጋኝ እርምጃዎች 'አደጋ ላይ' የሚጥል ነው ብሎታል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡ በጥቂት ወራት የፖለቲካ እስርኞችን በመፍታታቸው እንደተመሰገኑ ሁሉ አሁን ላይ በእስር ላይ አሉ በሚባሉት ፖለቲከኞች ወቀሳም ይቀርብባቸዋል።

የኦነግ፣ የኦፌኮ፣ የባልደራስና የኦብነግ አመራሮች 'አባሎቻችን ታስረውብናል'፣ 'ቢሮዎቻችን ተዘግተውብናል'፣ 'ወከባና ማስፈራሪያ ይደርስብናል' የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ያቀርባሉ። በተለይ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እስርኞች ቁጥር ከፍ ብሏል የሚለው ደግሞ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች ነው።

ክስ ሳይመሰረትባቸው እስር ላይ የሚገኙ እንዳሉም ገልጿል። ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያየ ወቅቶች ባወጣቸው መግለጫዎች ፍርድ ቤቶች የሚያሳልፉት ውሳኔዎች [በተለይ የፓለቲካ ተሳትፎ ያላቸውን እስረኞችን በተመለከተ] ያልተከበሩባቸውን ጊዜያት ጠቅሶ ችግሩ እንዲታረም በተደጋጋሚ አሳስቧል።

ሰላምና መረጋጋት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ባሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ንጹሃንን ዒላማ ያደረጉ በርካታ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል።

ከአራት ወራት በፊት [ኅዳር 21-2013] በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ማዕከላዊ መንግስቱና ህወሃት የገቡበትን ግጭት ሳይጨምር በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በድምሩ 113 ግጭቶች [ከትግራይ ክልል በስተቀር] መከሰታቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ግጭቶች የሰው ህይወት የጠፋባቸውና ንብረት ያወደሙ እንደነበሩም ጠቁመዋል።

"በእያንዳንዱ ሳምንት የጦርነት ድግስ ነበር። የመንግሥት ስራ እዚህ ማልቀስ መቅበር - እዚህ ማልቀስ መቅበር! ከአንደኛው ለቅሶ ሳይነሳ ወደ ሌላው ለቅሶ መሄድ ነበር።" ሲሉም ተደምጠዋል።

ለዚህም ተጠያቂው ህወሓት እንደሆነ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ ህወሓት አቅሙ እንደተዳከመ ከተገለጸ በኋላም ንጹሃን ላይ ያተኮር ጥቃት ተፈጽሟል። በቤንሻንጉል ጉሙዝ በመተከል ድባጤ ወረዳ ከሁለት ወራት በፊት [ጥር 4-2013] 82 ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን በወቅቱ እማኞች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

ከዚህ ጥቃት አንድ ወር ቀደም ብሎ ደግሞ በተመሳሳይ ዞን ቡለን በተባለ ወረዳ 207 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በተለያየ ወቅት ሰላማዊ ዜጎችን ኢላማ ያደርጉ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ከትግራይ ግጭት በፊት በነበሩ አለመረጋጋቶችም እንዲሁ በርካታ ንጹሃን ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል።

ለአብነት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ የተፈጠረውን ቀውስ በተመለከተ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን 'መንግስት ያለ አይመስልም ነበር' በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ከአርቲስቱ ግድያ በኋላ በነበሩት 3 ቀናት ብቻ 123 ሰዎች በጸጥታ አካላትና በሁከቱ በተሳተፉ ሰዎች መገደላቸውን አትቷል።

በአማራ ክልል በተለያዩ ወቅቶች በተከሰቱ ግጭቶችም የሰው ህይወት ጠፍቷል። ከዓመት በፊት በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ በተቀሰቀሰ ግጭት የ9 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተዘግቦ ነበር።

ሲዳማን በክልል ከመደራጀት ጋር ተያይዘው በተነሱ ግጭቶችም የሰዎች ህይወት ጠፍቷል አካል ጎድሏል ንብረት ወድሟል። በደቡብ ክልል በጌዲዮ፣ በወላይታ፣ በኮንሶና በጉራጌ ዞኖች በተለያየ መነሻ የተፈጠሩ ግጭቶች የንጹኀንን ህይወት ቀምተዋል። በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች እንዲሁ።

ከዚህም ባለፈ ወታደራዊና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት የተገደሉትም ዐቢይ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ነው። በተለያዩ ወቅቶችም ከክልል በታች ያሉ መንግስታዊ መዋቅር አመራሮችም የተገደሉባቸው ወቅቶች ነበሩ።

እናም የዚህ ሁሉ ድምር መንግስት ባለፉት ሦስት ዓመታት የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅና ሰላምና መረጋጋትን ከማስፈን አኳያ በተለያዩ አካላት ክፉኛ አስተችተውታል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥቅምት 24-2013 በነበራቸው መደበኛ ስብሰባ ባልተለመደ መልኩ በእንባና በቁጣ ታጅበው መንግሥት የዜጎቹን ደህንነት እንዲጠብቅ አሳስበው ነበር።

ከብልጽግና ምስረታ እስከ ትግራይ ግጭት

30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በስልጣን ላይ የነበረው ኢህዴግ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ የቆየው ዘጠኝ ወራት ብቻ ነው።

ከህወሃት በስተቀር ስምንቱን ክልሎች የሚያስተዳድሩ ገዢ ፓርቲዎች ከስመው ብልጽግና የተሰኘ ፓርቲ ተመሰረተ። ፓርቲው በተለይ ክልሎች ላይ ያለው መዋቅር ከቀድሞ በምን እንደሚለይ ግልጽ አይደለም የሚል አስተያየት ይቀርብበታል።

ታዲያ የፓርቲው መመስረት ህወሓት ቀድሞ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር የነበረውን የሻከረ ግንኙነት ይበልጥ እንዳካረረው ይነገራል።

የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ከፓርቲ ውህደት በፊት ሊታዩ የሚገቡ አንገብጋቢ ጉዳዮች እንዳሉና የውህደት ሂደቱም ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዳልተፈጸመ ገልጸው ነበር።

በሌላ በኩል የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ በድምፀ ወያኔ ቴሌቪዥን ቀርበው "አገሪቱ ወደማይሆን ጣጣ እየገባች ባለችበት ሁኔታ ስለውህደት ብቻ ማውራት ምናልባት የሀገሪቱን ሁኔታ የመዘንጋት ስለሃገሪቱ ሁኔታ ያለመጨነቅ ነገርን ነው የሚያሳየው" ብለው በዚህም ምክንያት ህወሃት የተለየ አቋም መያዙን ገልጸዋል።

ይህ ከሆነ ከወራት በኋላ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ምርጫ 2012 እንዲራዘም በህዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሲወሰን ሃሳቡን የትግራይ መንግሥት ባለመቀበል በክልሉ ምርጫ ለማድረግ ወሰነ። ምርጫውም ተደርጎ ህወሃት እንዳሸነፈ ተገለጸ። ይህም የሁለቱን አካላት የሻከረ ግንኙነት ይበልጥ አጋጋለው።

"ትግራይ ክልል የሚደረገው የጨረቃ ምርጫ ነው።... ልክ እንደጨረቃ ቤት ነው ህጋዊ አይደለም። ..." ያሉት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነበሩ። የሁለቱ አካላት በቃላት ጦርነት የታጀበ መቃቃር በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ወደ ግጭት ተሸጋገረ።

የትግራይ መንግሥት ለፌዴራሉ መንግሥት እውቅና ሲነፍግ የፌዴራሉ መንግስት ደግሞ ለክልሉ የሚሰጠውን በጀት ማቋረጡን አስታወቀ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ደግሞ ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ሁለቱ አካላት ወደለየለት ወታደራዊ ግጭት አመሩ። በግጭቱ የተሳተፉ አካላት በሙሉ የከፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ማድረሳቸውን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ገልፀዋል።

ግጭቱን ተከትሎ በማይካድራ ከ600 በላይ ዜጎች በህወሓት ኃይሎች ለሞት እንደተዳረጉና በሌላ በኩል ከ100 በላይ ሰዎች በአክሱም በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ ወቅቶች ገልጿል።

ይህ ግጭት በርካቶችን ለአካላዊ ጉዳት፣ ለስደትና መፈናቀል ዳርጓል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉልህ ሚና የነበራቸውን አንጋፋ ፖለቲከኞችን ለሞትና ለእስርም የተዳረጉበት ነው።

በትግራይ ባለው ግጭትም የኤርትራ ስም ተደጋግሞ ይነሳል። የኤርትራ ወታደሮች በውጊያ በቀጥታ ከመሳተፍ አልፈው ንጹኀንን በአክሱም 'በአሰቃቂ' ሁኔታ መግደላቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገልጿል። ሌሎች አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ደግሞ ቁጥሩን ከዚህም ከፍ ያደርጉታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም በመጨረሻው የተወካዮች ምክር ቤት ቆይታቸው 'ኤርትራ ባለባት የብሄራዊ ደህነነት ስጋት ' ምክንያት ወታደሯቿ 'የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው' እንደሚገኙ ከገለጹ ከቀናት በኋላ ኤርትራ ወታደሮቿን ለማስወጣት መስማማቷ ተሰምቷል።

ኢኮኖሚ: የዋጋ ግሽበቱ ከስት ዓመታት በላ ሲቃኝ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በያዙ የመጀመሪያው [ሚያዚያ 2010] ማዕከላዊ ስታቲክስ ባወጣው መረጃ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 13.7 በመቶ ነበር። ይኸው ተቋም ባወጣው ሪፖርት ከሶስት ዓመታት በኋላ የባለፈው ወር [የካቲት 2013] አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 20.6 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በያዙ የመጀመሪያ ወራት ኢትዮቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ 13 የስኳር ፋብሪካዎች፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ድርጅቶችን እንዲሁም ሌሎች በመንግሥት ይዞታ ስር ያሉ የልማት ተቋማትን በከፊል ለማዞር መወሰኑ ተሰማ። ይህም የተለያዩ ግብረ መልሶችን አስከተለ።

አንደኛው ወገን መልካም እርምጃ ነው የሚል ሲሆን ሌላኛው ግን "ያለ በቂ ጥናት የተደረገና የተጣደፈ ነው "የሚል ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮ ቴሌኮም ከሌሎቹ የልማት ድርጅት በተለየ የተወሰነውን ድርሻ ለመሸጥ የሚኣስችለው ሂደት በፍጥነት እየተከናወነ ነው። ሂደቱንም የሚከታተል የኮሚኒኬሽን ባለስልጣን የተባለ ተቆጣጣሪ ተቋም ተመስርቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን የተወሰነ ድርሻ ወደ ግል የማዞሩን ሃሳብ መንግሥት 'ለጊዜው እንደተወው' ገልጿል። የስኳር ፕሮጀክትና የባህር ሎጀስቲክስ የተወሰነ ድርሻን የመሸጥ ሂደት እንደቀጠለም የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ከወራት በፊት ገልፀው ነበር። የተቀሩትን ተቋማት በተመለከተ ግን የተባለ ነገር የለም።

ኤርትራ፡ ለዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ምስጋናና ወቀሳ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተሾሙ የመጀመሪያ ቀን ለኤርትራ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸው በበርካቶች ያልተጠበቀ ነበር።

"በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነታችንን በጋራ ለመፈታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ፣ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለው።" ሲሉ ከምክር ቤቱ አዳራሽ 'ሞቅ' ያለ ጭብጨባ ተቀባላቸው።

ይህንን ካሉ ከአራት ወራት በኋላ ወደ አሥመራ አቀኑ። ይህም ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ኤርትራን የጎበኙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሪ አደረጋቸው።

በርከት ያለ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ተቀበላቸው። የአየር መንገድና የስልክ አገልግሎቶች ዳግም ተጀመሩ። ከሳምንት በኋላ ደግሞ ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ ሲገቡ ተመሳሳይ አቀባበል ተደረገላቸው።

በጦርነቱ ምክንያት ረጅም ዘመናት ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦች ተገናኙ። ድንበሮች ተከፈቱ። ይህም ዐቢይን እጅግ አስመሰገናቸው የተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት አድናቆታቸውን ገለጹ።

የዚህ ሁሉ ድምር እንደ አውሮፓውያኑ የ2019 የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ አደረጋቸው። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ግን ግልጽ ባልሆነ መንገድ የሁለቱ አገራት ድንበሮቹ ዳግም ተዘጉ።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት 'ግልጽ መርህ የለውም' የሚል ወቀሳም ተከተለ።

በአንድ ወቀቅ ትግራይ ቲቪ ላይ ቀረበው ስለሁለቱ ሃገራት ግንኙነት አስተያየት የሰጡት አምባሳደር ስዩም መስፍን ግንኙነቱ 'የጠላቴ ጠላት ወደጄ ነው' በሚል መርህ የቆመ ነው ሲሉ ገልጸው ነበር።

ይህ ግንኙነት ለሁለቱ አገራት ህዝቦች የፈየደው ነገር የለም ሲሉም ተናግረዋል። በሌላ ቀን ደግሞ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እንዲጥሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፈቅደዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

በተቃራኒው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተያዘው ዓመት መግቢያ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሁለቱ አገራት ግንኙነት መርህ የሌለውና ህወሓትን ለማጥቃት የዋለ ነው ይባላል የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ ይህንን የሚሉ አካላት ማምጣት ያልቻሉትን የዲፕሎማሲ ድል አግኝተናል፣ የዚህ ድል ትርፍ ደግሞ ሰላም ነው ብለዋል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ደግሞ በቅርቡ በሰጡት ቃለ መጠይቅ "በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ የቻልነውን ያህል ለማበርከት እየሞከርን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ግጭት በተጀመረ ሰሞን ሱዳን ወደ ኢትዮጵያን ግዛት ዘልቃ መግባቷ ተሰምቷል። እነዚህ ሁለቱ ሀገራት ከበርካታ አመታት በኋላ የከፋ ዲፕሎማሲያዊ ግጭት ውስጥ ሲገቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ይህም ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በተመለከ የእርሳቸውን ድርሻ የተቃረኑ ገጾች እንዲኖሩት ያደረገ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በሱዳን ያለው የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ባደረጉት አስተዋጾ በ'ባለውለታነት' ሲነሱ ድንበር አከባቢ ባለው ውጥረት በተለየ አይን ይታያሉ።

ግብጽ፣ ሱዳንና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፉት ስት ዓመታት

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሁለት መልኩ ነው አስተያየት ይቀርብባቸዋል።

በግንባታው ሂደት በበጎ ሲነሱ በድርድሩ ግን ስህተቶችን ሰርተዋል ተብለው ይወቀሳሉ።

የግድቡን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችን ይዞ የነበረውና ለግንባታው መጓተት ምክንያት እንደነበር ሲጠቀስ የነበረው ሜቴክ በግንባታው የነበረው ጉልህ ተሳትፎ የተቋረጠው እርሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነው።

"ፕሮጀክቱ በነበረው አመራር በነበረው አካሄድ ቢቀጥል ምንም አትጠራጠር እንኳን ዘንድሮ በሁለት ሶስት ዓመታት ውሃውን መያዝ አይችልም። ግድቡም አይገደብም ስራውም አይሰራም" ብለውም ነበር። እናም ተደረጉ በተባሉ ማስተካከያዎች ባለፈው ዓመት ግደቡ 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ያዘ። ይህም ዐቢይን ያስመሰገናቸው ነበር።

በዚያው ዓመት ግን በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና ግብጽ መካከል ሲደረግ በነረው ድርድር የአሜሪካን ገንዘብ ሚኒስቴርና የዓለም ባንክን ተሳትፎ መፍቀዳቸው ክፉኛ ሲያስተቻቸው ነበር።

ታዛቢ የተባሉት አካላት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጻረር ስምምነት እንዲፈርም ጫና ማሳደራቸውን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ስምምነቱን ባለመቀበሏ ለማዕቀብ ተዳርጋለች።

ድርድሩ ኢትዮጵያ ከግብጽና ሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነትንም እንዳሻከረው ይገለጻል።