ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳይ የሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ 'እንዳላየ' ማለፏን ሪፓርት ጠቆመ
ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት በሩዋንዳ ለተከሰተው የዘር ጭፍጨፋ ፈረንሳይ "እጅግ ከፍተኛ ተጠያቂነት" አለባት ሲል በፈረንሳይ የታሪክ ምሁራን የተዘጋጀ አንድ ሪፖርት አመለከተ።
ፈረንሳይ በተፈጠረው ነገር እጇ እንደነበረበት የሚጠቁም መረጃ ግን ምሁራኑ አላገኙም።
ሪፖርቱ የቀረበው ለፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ነው። በሪፖርቱ መሠረትም ፈረንሳይ የዘር ጭፍጨፋውን "እንዳላየ" አልፋለች።
በወቅቱ ሁቱዎች፤ ቱትሲዎችን እንዲሁም ለዘብተኛ የሚባሉ ሁቱዎችን ጨፍጭፈዋል። ቢያንስ 800,000 ሰዎች የተገደሉበት አሰቃቂ የዘር ጭፍጨፋ ነው።
የታሪክ ምሁራኑ ጥናት ያደረጉት በፈረንሳይን ይፋዊ መዛግብት ላይ ነው።
ሩዋንዳ በዘር ጭፍጨፋው ፈረንሳይ ተባባሪ ነበረች ስትል ትከሳለች። በታሪክ ምሁራኑ የወጣውንም ሪፖርት ተቀብላዋለች።
የሩዋንዳ መንግሥት "በቱትሲዎች ላይ በተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ የፈረንሳይ ሚና ምን እንደነበር የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሪፓርቱ አንድ እርምጃ ነው" ሲል ገልጿል።
እአአ ከግንቦት 1994 እስከ ሰኔ 1994 ድረስ ሩዋንዳ በሁቱ መሪ ሥር ነበረች። ከዚያም በቱስሲዎች የሚመራው አማጺው የሩዋንዳን ፓትርዮቲክ ፍሮት (አርፒኤፍ) አመራሩን ከሥልጣን አስወግዷል።
አርፒኤፍ ያኔ ይመራ የነበረው በአሁኑ የሩዋንዳ ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ ነው።
ሪፖርቱ የያኔው የፈረንሳይ ፕሬዘዳንት ፍራንሷ ሚትራን ሩዋንዳን በተመለከተ ያራምዱት የነበረው ፖሊሲ "የከሸፈ" ነበር ይላል።
ፈረንሳይ ሩዋንዳን ይመሩ ከነበሩት ሁቱዎች ጋር ስለነበራት ግንኙነት ለዓመታት ምንም ነገር በግልጽ ባይነገርም፤ አሁን ሪፖርቱ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።
ጥናቱ የተካሄደው 15 አባላት ባሉት ኮሚሽን ሲሆን፤ ኮሚሽኑን ከሁለት ዓመት በፊት ያዋቀሩት ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ናቸው።
ኮሚሽኑ ፕሬዘዳንታዊ መረጃ፣ የዲፕሎማሲ ሰነዶች እንዲሁም ወታደራዊና የደኅንነት መዛግብትን እንዲፈትሽ ተፈቅዶለታል።
የያኔው የፈረንሳይ ፕሬዘዳንት ሁቱ ከነበሩት ፕሬዘዳንት ዡቬናል ሀቢያሪማና ጋር ቅርብ ግንኙነት እንደነበራቸው መዛግብት ያሳያሉ።
እአአ ግንቦት 6/1994 ሀቢያሪማና እና የብሩንዲውን ሲፒሪን ናታኒያሚራን የያዘ አውሮፕላን ተመቶ መውደቁን ተከትሎ ነበር የዘር ጭፍጨፋው የተቀሰቀሰው።
ኤኤፍፒ እንደዘገው፤ ጥናቱን ባካሄደው ኮሚሽን ውስጥ ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ ሲባል ሩዋንዳውያን ተመራማሪዎች አልተሳተፉም።
ሆኖም ግን በአይሁዳውያን ላይ በናዚ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት [ሆሎካስት] ላይ ጥናት የሠሩ፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት የተጨፈጨፉ አርመናውያን ላይ ጥናት ያደረጉና ሌሎችም በዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ የታወቁ ምሁራን ተካተዋል።
ቪንሰንት ዱሴለርት በተባሉ የታሪክ ምሁር ነው ካውንስሉ የተመራው።
እአአ በሰኔ 22/1994 የተባበሩት መንግሥታት የፈረንሳይ ኃይልን በሩዋንዳ ደቡብ ምዕራብ ግዛት አሰማርቶ ነበር።
ይህ ተልዕኮ 'ቱርክዌስ' የተባለው ስምሪት አከራካሪ ነበር።
የፈረንሳይ ሰብዓዊ አገልግሎት ክፍል ጥቂት ሰዎችን ከግድያ ታድጓል። ሆኖም ግን እነዚህ የፈረንሳይ ኃይሎች በቦታው የደረሱት እጅግ ዘግይተው እንደነበር እና ገዳዮቹ መጠለያው ውስጥ ተደብቀው እንደነበር ተነግሯል።
2015 ላይ የያኔው ፕሬዘዳንት ፍራሷ ሆላንዲን ሩዋንዳና በተመለከተ የተሰበሰቡ መረጃዎች ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ተናግረው ነበር።
ሆኖም ግን አንድ አጥኚ ሰነዶቹን ከመረመሩ በኋላ የፈረንሳይ የሕገ መንግሥት ካውንስል መረጃው በምስጢር እንዲያዝ ውሳኔ አሳልፏል።
የሩዋንዳ መንግሥት እንዳለው፤ ከፈረንሳይ የታሪክ ምሁራን ሪፖርት ጋር አብሮ የሚሄድ ሪፖርት በቅርቡ ይፋ ያደርጋል።