ፖሊስ የኮቢ ብሪያንት አሟሟት አሰቃቂ ምስሎችን አሳይቷል ስትል ባለቤቱ ከሰሰች

ኮቢና ልጁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በባለፈው አመት በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወቱን ያጣው ታዋቂው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ኮቢ ብሪያንት ባለቤት የአሟሟቱን ሁኔታ የሚመለከቱ አሰቃቂ ምስሎችን አውጥቷል ስትል ፖሊስን ከሳለች።

አሰቃቂ ምስሎች አውጥተዋል ያለቻቸውን የሎስ አንጀለስ ግዛት ፖሊሶች ስምም ጠቅሳለች።

ፖሊሶች በቸልተኝነትና የግል ኑሯቸውን በጣሰ መልኩ እነዚህን ፎቶዎች አውጥተዋል በማለት የግዛቱን የፖሊስ ኃላፊዎች የከሰሰችው።

"በሚዲያ የፍርድ ሂደቱ እንዲካሄድ ስለማንፈልግ ምንም ነገር ከማለት ተቆጥበናል" በማለት የፖሊስ ኃላፊው ምላሽ ሰጥተዋል።

ስመ ጥሩው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ኮቢና ልጁን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች በባለፈው አመት በደረሰ የሄሊኮፕተር አደጋ መሞታቸው የሚታወስ ነው።

በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ቫኔሳ አሰቃቂ ፎቶን አውጥተዋል ያለቻቸውን አራት የፖሊሶች ስም በኢንስታግራም ገጿ አስፍራለች።

ቫኔሳ እንደምትለው ፖሊሶቹ የዘጠኙን ሰዎች አስከሬን ፎቶዎች ካነሱ በኋላ አንደኛው ፖሊስ በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ የኮቢን ፎቶ እያሳየ ነበር ብላለች።

ሌሎቹ ደግሞ ህፃናት ያሉበት፣ ወላጆቻቸውንና አሰልጣኞቻቸውን አሰቃቂ ፎቶዎች ለበርካቶች ሲያሳዩ ነበር ብላለች።

የሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ በየካቲት ወር ላይ ውስጣዊ የፖሊስ የምርመራ መዝገብን ጠቅሶ ፖሊሶች የሟቾችን አሰቃቂ ፎቶዎች አጋርተዋል ብሏል።

ቫኔሳ እንደምትለው የ13 አመት ልጇ ጂያና የአስከሬን ፎቶ ሳይቀር "ለአሉባልታ ብቻ" ለዕይታ ውሏል ብላለች።

የፖሊሶቹ ስም ይፋ እንዳይወጣ ባለፈው ሳምንት ለፍርድ ቤት ጥያቁ ቢቀርብም ዳኛው በበኩላቸው ስማቸው ይፋ እንዲሆን አዟል።

የሎስ አንጀለስ ግዛት ፖሊስ ኃላፊ አሌክስ ቪላኑቫ የቫኔሳን ትዊተር አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ የፍርድ ቤቱን ምላሸ እንጠብቃለን ብለዋል።

ቫኔሳ ስምንት ፖሊሶች ለራሳቸው ጥቅም እንዲውል በሚል በርካታ ፎቶዎች ያነሱ ሲሆን አንደኛው ግለሰብም ከ25-100 ፎቶዎችን አንስቷል ብላለች።