ኮሮናቫይረስ፡ የአስትራዜንካን ክትባት ተጠቀሙ- የዓለም ጤና ድርጅት

በርካታ የአውሮፓ ሃገራት የኮሮናቫይረስ መከላከያ የሆነውን አስትራዜንካ ክትባት ማገዳቸውን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርቧል።

ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያንና ስፔይንን ጨምሮ ሌሎች አገራት የኦክስፎርዱ አስትራዜንካ ክትባት ደም መርጋት በተያያዘ ችግር አለበት በሚል ክትባቱ እንዳይሰጥ አግደውታል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ደም መርጋት ስለማስከተሉ ምንም አይነት ማስረጃ የለም ይላል።

የድርጅቱ የክትባት ደህንነት ልሂቃንም በዛሬው ዕለት ተሰብስበው ስለ ክትባቱ ይመክራሉ ተብሏል።

የአውሮፓ መድኃኒት ኤጀንሲም እንዲሁ ስለ ክትባቱ በዛሬው ዕለት የሚወያዩ ሲሆን በያዝነው ሃሙስም የደረሱበትን ማጠቃለያ ለህዝብ ያሳውቃሉ ተብሏል።

ሆኖም ኤጀንሲው ክትባቱን ተጠቀሙ ብሏል።

በአውሮፓ ክትባቱን ከተከተቡ በኋላ የደም መርጋት ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች አሉ ብሏል።

ነገር ግን ባለሙያዎቹ እንደሚሉት በአጠቃላይ ከህዝብ ብዛቱ ጋር ሲነፃፀር የደም መርጋት ያጋጠማቸው ሰዎች ድንገተኛ መጨመር አላሳየም ይላሉ ።

በአውሮፓ ህብረት አባላት አገራትና ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 17 ሚሊዮን ሰዎች የአስትራዜንካ ክትባትን መከተባቸውና ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ 40ዎቹ የደም መርጋት ችግር እንዳጋጠማቸው አስትራዜንካ አስታውቋል።

እየተወሰዱ ያሉ ጥንቃቄዎች

ይህንንም ተከትሎ የጀርመን ጤና ሚኒስቴር በያዝነው ሳምንት ሰኞ ዕለት አስትራዜንካ ክትባት መስጠት በአስቸኳይ እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፏል። ክትባቱ የአዕምሮ ደም መርጋት ወይም ሴሬብራል ቬይን ቶርምቦሲስ ችግር ጋር መገናኘቱን አይተናል ብለዋል።

የጤና ሚኒስትሩ ጄንስ ስፋን እንዳሉት ውሳኔ "ፖለቲካዊ" እንዳልሆነ ነው። "ሁላችንም ቢሆን ይህ ውሳኔ ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት እንረዳለን። በቀላሉም የደረስንበት አይደለም" ብለዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እንዲሁ የአውሮፓ መድኃኒት ኤጀንሲ ውሳኔውን እስኪያሳውቅ ድረስ አገራቸው ክትባቱን ታግዳለች ብለዋል።

"ቀለል ያለ መመሪያ ነው ያለን፤ ሳይንስንና በዘርፉ ላይ ዕውቀት ያላቸውን የጤና ባለስልጣናት ምክር ነው የምንከተለው፤ ይህም የአውሮፓ ስትራቴጂ ምን መምሰል አለበት የሚለውን የሚጠቁም ይሆናል" ብለዋል።

የጣልያን መድኃኒት ኤጀንሲም እንዲሁ የአውሮፓ መድኃኒት ኤጀንሲ የሚደርስበትን ማጠቃለያ እጠብቃለሁ በማለት አግዳዋለች።

የስፔን ጤና ሚኒስትር ካሮሊና ዳሪያስ በበኩላቸው ክትባቱ ለመጪው ሁለት ሳምንት ይታገዳል ብለዋል።

አየርላንድ፣ ፖርቹጋል፣ዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ቡልጋሪያ፣ አይስላንድ፣ ስሎቬኒያ ክትባቱን በጊዜያዊነት ያገዱ ሲሆን ዲሞክራቲክ ኮንጎና ኢንዶኔዥያ የክትባት መስጪያ ጊዜያቸውን አራዝመውታል።

ኦስትሪያን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገራት ለጥንቃቄ ሲሊ ቢያግዱትም ቤልጂየም፣ ፖላንድና ቼክ ሪፐብሊክ ክትባቱን እየሰጡ ነው።

የቤልጂየም ጤና ሚኒስትር ፍራንክ ቫንደንብራውኬ እንዳስታወቁት ቤልጂየም ካላት ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ ህሙማን ቁጥርን በማየት ክትባቱን አለመስጠት አትችልም ብለዋል።

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በበኩላቸው አስትራዜንካን ጨምሮ በአገሪቱ እየተሰጡ ያሉ ክትባቶች ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን የጤና ባለስልጣናቱ ነግረውኛል ብለዋል።